ምርጫ 2013፡ ምርጫ ቦርድ በእስር ላይ ያሉትን እነ እስክንድር ነጋን በዕጩነት ለመመዝገብ እንደሚቸገር አስታወቀ

እስክነድር ነጋ

የፎቶው ባለመብት, facebook

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ሰበር ሰሚ ችሎት እነ አቶ እስክንድር ነጋ በዕጩነት ተመዝግበው መወዳደር እንደሚችሉ ያሳለፈውን ውሳኔ ለማስፈፀም እንደሚቸገር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

ፍርድ ቤት በእስር ላይ ያሉት የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች ፕሬዚዳንቱን አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩምና አስካለ ደምሴ በመጪው ምርጫ በዕጩነት ተመዝግበው እንዲወዳደሩ ብይን ያስተላለፈው ሰኞ እለት ግንቦት 16 ነበር።

ፍርድ ቤቱ በተጨማሪ መርጫ ቦርድ እስከ ግንቦት 19/2013 ዓ.ም ድረስ ተገቢውን ትዕዛዝ ለምርጫ ወረዳዎች አስተላልፎ እንደ ፍርዱ እንዲፈፀም ትዕዛዝ ማስተላለፉን ከምርጫ ቦርድ ከተገኘው መረጃ መረዳት ተችሏል።

ምርጫ ቦርድ በበኩሉ በትናንትናው ዕለት ለባልደራስ እውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በፃፈው ደብዳቤ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ለማሰፈፀም እንደሚቸገር ገልጿል።

ለዚህም እንደ ምክንያትነት ያቀረበው የተወዳዳሪ ዕጩዎች ምዝገባ የካቲት 30/2013 ዓ.ም መጠናቀቁ፣ በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የሚኖረው ስፍራ የሚወስን ሎተሪ መውጣቱ፤ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ህትመትም ተጠናቆ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች የመላኩ ተግባር በቅርብ ጊዜ የሚከናወን በመሆኑ እንደሆነ አስታውቋል።

ከዚህ ቀደም ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በእስር ላይ ያሉ አመራሮቹን በተወዳዳሪ ዕጩነት እንዲመዘገቡለት ምርጫ ቦርድን ጠይቆ በመከልከሉ ከሕግ አግባብ ውጪ ነው ሲል ከሶ ነበር።

ፓርቲው በመከራከሪያነት የሚያነሳውም የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጁን ነው።

"ማንኛውም ሰው በሕግ ወይም በፍርድ ቤት ውሳኔ የመምረጥ ወይም የመመረጥ መብቱ ያልተገፈፈ እንደሆነ በዕጩነት ተወዳድረው መመዝገባቸው ሊከለከሉ አይገባም ብሎ ነበር።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዕጩነት ተመዝግበው መወዳደር ይችላሉ የሚለውን ውሳኔ ተከትሎ የባልደራስ አመራሮች ባሉበት ሆነው የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ እንዲችሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀው ነበር።

ነገር ግን የምርጫ ቦርድ ውሳኔን ተከትሎ ባልደራስ በማኅበራዊ ትስስር ገፁ ባወጣው መግለጫ "ምርጫ ቦርድ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ አላከብርም አለ" በማለት ያሰፈረ ሲሆን አስቸኳይም ስብሰባ መጥራቱን አስታውቋል።