“በሩዋንዳ ለመኖር እየታገልኩ ነው” ኢትዮጵያዊው ስደተኛ

“ትግሌ በሕይወት ለመቆየት ብቻ ነው” በማለት ፍርሃት በሞላበት እና በሚንቀጠቀጥ ድምጹ ሩዋንዳ ውስጥ የሚኖር ስደተኛ ነገረኝ።
በሩዋንዳዋ ከተማ ኪጋሊ ነው ያገኘሁት። ከሰዎች ዕይታም ለመደበቅ በሚል በዛፎች በተከበበ አካባቢ ነው የተገናኘነው።
መሐመድ እያልን የምንጠራው ኢትዮጵያዊው ስደተኛ ሩዋንዳ የደረሰው ጥገኝነት ለመጠየቅ ነው።
ከአገሩ ወደ ሩዋንዳ ተሰድዶ ነው የመጣው። የኢትዮጵያ የደኅንነት ሰዎች ሊጠልፉት መሞከራቸውንም ይናገራል።
መሐመድ የኪጋሊ ኑሮ ፈታኝ ነው ይላል። ጋዜጠኛን በማናገሩ ሊደርስበት የሚችለውን አጸፋዊ እርምጃን በመፍራት እውነተኛ ስሙን እንዳልገልጽ ጠየቀኝ።
በሩዋንዳ ነዋሪነታቸውን ካደረጉ ጥገኝነት ጠያቂዎች ይፋዊ በሆነ መልኩ እንዲያናግሩን ለቀናት ስንሞክር ነበር።
መጀመሪያ እሺታቸውን ቢገልጹም በኋላ ግን ምስጢራዊ በሆነ ሁኔታ ብቻ ለመነጋገር ፈቀዱ። ብዙዎችም ይህንን ምላሽ የሰጡት “በማኅበረሰብ መሪ” ከተጎበኙ በኋላ ነው።
“ጥገኝነት ጠይቄአለሁ” በማለት መሐመድ ነገረኝ።
“ባለሥልጣናቱ አይሆንም አይሉም። ነገር ግን ሁሉ ነገር የማይሳካ ቀጠሮ ነው። ነገ ወይም በሚቀጥለው ወር ተመለስ ይሉኛል። ይኸው ስመላለስ አንድ ዓመት ሊሞላኝ ነው” ይላል።
በለንደን የሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት የእንግሊዝ መንግሥት አንዳንድ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ያቀደውን አወዛጋቢ ዕቅድን ሕጋዊነት እያጤነ ባለበት ወቅት ነው መሐመድን እያናገርኩ የነበረው።
ሰኞ ዕለትም ዳኞች የእንግሊዝ መንግሥት ፖሊሲ ሕጋዊ እንደሆነ ውሳኔ አሳልፈዋል።
ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ስምምነት ጋር የማይጣረስ ከሆነ ስደተኞችንም ወደ ሌላ ቦታ ማዛወርም ስህተት የለውም ብሏል - ፍርድ ቤቱ።
ዩኬ መንግሥት በአገሪቱ ያሉ ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳያቸውን እንዲጠራ ወደ ሩዋንዳ ለመላክ አቅዷል። ይህም ፖሊሲ በትናንሽ ጀልባዎች ወደ እንግሊዝ የሚገቡ ስደተኞችን እንደሚያቆመውም ተስፋ ተደርጎበታል።
የመንግሥትን ፖሊሲ የተቹት በበኩላቸው ፖሊሲው “ጭካኔ የተሞላበት፣ ለመተግበር አስቸጋሪ እና ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስወጣ ነው” ይላሉ።
ከዚህ ቀደም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂውማን ራይትስ ዋች ሩዋንዳን “የመናገር ነጻነት ጭቆና ያለባት፣ የዘፈቀደ እስራት የሰፈነባት፣ እንግልት እና ማሰቃየት የተንሰራፋባት” በማለት ገልጿታል።
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት በበኩሉ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ባወጣው ግምገማ መሠረት “በመናገር እና በመደራጀት ነፃነት ላይ አንዳንድ ገደቦች ቢኖሩም” ከዩኬ ወደ ሩዋንዳ የሚዛወሩ ስደተኞች እንግልት ይደርስባቸዋል ብሎ እንደማያስብም አስታውቋል።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ ሩዋንዳ “ተደራሽ፣ አስተማማኝ፣ ፍትሃዊ እና ቀልጣፋ የጥገኝነት ሥርዓትን” እንደማታሟላ ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል።
ስደተኞች ስቃይ እና እንግልት ሊደርስባቸው ወደሚችሉ አገሮች እንዲመለሱ የማድረግ ሂደት አሳስቦት ነበር።
የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲ ከጥቂት ወራት በፊት ባወጣው ሪፖርት “የጥገኝነት አሰራር ቅልጥፍ እና ወቅታዊነት አሳሳቢ ነው። በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎች ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት የሚወስዱ መሆኑ ታይቷል” ብሏል።
መሐመድ ሕይወቱ በአጣብቂኝ ውስጥ እንደገባ እንደሚሰማው ይናገራል። አስፈላጊ ሰነዶች ስለሌሉትም በሕጋዊ መንገድ መሥራት አልቻለም።
“ጓደኞቼ እና ዘመዶቼ ይረዱኛል” የሚለው መሐመድ ሲያገኝ ትንንሽ ሥራዎች በመስራት ራሱን ለመደጎም እየሞከረ መሆኑን ይናገራል።
ነገር ግን ባለቤቱ እና ልጆቹን ከመደገፍ ኃላፊነት ጋር ተያይዞ ሸክሙ ከብዶታል።
ከሩዋንዳ መውጣት እንደሚፈልግና “ሰላም ወደሰፈነባቸው እንደ ካናዳ ወይም አውስትራሊያ አይነት አገራት መሄድ እፈልጋለሁ” ይላል።
የዩናይትድ ኪንግደም ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ የማዘዋወር ፖሊሲን ከሚቃወሙ መካከል ቅሬታ ከሚነሳባቸው ጉዳዮች አንዱ አገሪቱ ያላት የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን አያያዟ ይጠቀሳል።
በሩዋንዳ እንደ ሌሎች ጎረቤት አገራት የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ድርጊቶች ሕገወጥ ብቻ አይደሉም። ነገር ግን ሂውማን ራይትስ ዋች ባወጣው ሪፖርት መሠረት ግለሰቦቹ ያለ አግባብ እስር፣ መዋከብ እና ስድብ ይደርስባቸዋል ብሏል።
በስድስት ቀናት ቆይታችን የመንግሥት ባለሥልጣናትን ለማናገር እንዲፈቀድልን ደጋግመን ጠየቅን። የመንግሥት ቃለ አቀባይ ቢቢሲን ለማናገር ቃላቸውን ቢገቡም የተገባው ቃል ፈጽሞ እውን ሊሆን አልቻለም።
ሆኖም ከመንግሥት ቃለ አቀባይ የወጣ ነው የተባለ መግለጫ የተሰጠን ሲሆን በዚህም “በሁሉም መልኩ የሚደረግ የትኛውም መድልዎ በሕገ መንግሥታችን የተከለከለ ነው። ሩዋንዳ ሁሉንም በእኩልነት ትቀበላለች” የሚል መልዕክት ሰፍሯል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከ100 የሚበልጡ ከሊቢያ የመጡ ስደተኞችን ጨምሮ ሌሎች ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ እየላከ ባለበት ወቅት፣ እንደዚህ አይነት ሪፖርት ማውጣቱ የሚቃረን ነው ብሏል።
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ፖሊሲ ሕጋዊ ነው በማለት የለንደኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ የሩዋንዳ መንግሥት በጸጋ ተቀብሎታል።
“ለጥገኝነት ጠያቂዎች እና ስደተኞች ደኅንነታቸው በተጠበቀ መልኩ አዲስ ሕይወት የመገንባት ዕድል ለመስጠት ዝግጁ ነኝ” ብሏል የሩዋንዳ መንግሥት ባወጣው መግለጫ።

በሩዋንዳ የተሳካላቸው ስደተኞችም አሉ። ተክላይ ጣዕመ ከአገሩ ኤርትራ ወደ ሩዋንዳ የመጣው የዛሬ 25 ዓመት ገደማ ነው፤ በአውሮፓውያኑ 1998።
በአሁኑ ወቅት ትልልቅ የጅምላ መደብሮች እና ሱፐር ማርኬቶች አሉት።
እኔ ባገኘሁት ወቅት ሠራተኞቹ ትልልቅ ሳጥኖችን ከመኪና እያወረዱ ወደ አንደኛው መደብር በማስገባት ተጠምደው ነበር።
“ሩዋንዳ ስደርስ ሁሉም ነገር ለእኔ አዲስ ነበር። ነገር ግን ሩዋንዳውያን በጣም ተግባቢ ስለነበሩ ለመቀላቀል እና ለመዋሃድ ብዙ ጊዜ አልፈጀብኝም። በአራት ሠራተኞች ነው ሥራ የጀመርኩት። በአሁኑ ወቅት ከ600 በላይ ሠራተኞች አሉኝ” ይላል - ተክላይ።
ከብዙ ስደተኞች በተለየ መልኩ ተክላይ ንግዱን ለመጀመር የሚያስፈልገው ገንዘብ ነበረው።
“ሩዋንዳ በሕጎቿ እስከተመራሽ ድረስ ለሁሉም ተመሳሳይ ዕድሎችን ትሰጣለች” ይላል።
ተክላይ እንደሚለው ምንም ሳይኖራቸው ሕይወታቸውን ያቃኑ፣ ንግድ የጀመሩ በስደት ሩዋንዳ የመጡ ሌሎች ኤርትራውያንን እንደሚያውቅ ይናገራል።
በዩናይትድ ኪንግደም ያሉ ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ ሩዋንዳ እንዲዛወሩ ከታሰበው ዕቅድ ጋር በተያያዘ ፍርሃትና ስጋት ያጫረባችው ስደተኞችን በተመለከተ ጠየቅኩት።
“ምን እንደሚፈሩ አላውቅም። ነገር ግን እዚህ ምንም መፍራት የሚያስፈልግ አይመስለኝም” ሲልም ምላሹን ሰጥቷል።
ፀሐይ በኪጋሊ ላይ ስትጠልቅ ያለው ዕይታ አስደናቂ ነው፤ ደማቅ ቀይ ፀሐይ ከለምለም አረንጓዴ ኮረብታ ጀርባ ስትጠልቅ ያለ ዕይታ።
ከተማዋም ሆነ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ሥርዓት ያለውና ቀልጣፋ ነው። በዓለም ዙሪያ ያሉ አገሮች የሚቀኑበትም ሊሆን ይችላል።












