ከኢትዮጵያውያን ስደተኞች የጅምላ መቃብር ጋር ተያይዞ የማላዊ የቀድሞ ፕሬዝዳንት የእንጀራ ልጅ በቁጥጥር ስር ዋለ

የጅምላ መቃብር

የፎቶው ባለመብት, Malawi Police

የሰላሳ ስደተኞች አስክሬን ካለበት የጅምላ መቃብር ጋር በተያያዘ የማላዊ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ፒተር ሙታሪካ የእንጀራ ልጅ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአገሪቱ ፖሊስ አስታወቀ።

በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ያሉበት የ30 ሰዎች አስክሬኖች የጅምላ መቃብር የተገኘው ባለፈው ጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ ነበር።

ምዚምባ በተባለ የማላዊ ግዛት ውስጥ በተገኘው በርካታ ስደተኞች በሽምላ ከተቀበሩበት መቃብር ጋር በተያያዘ ፖሊስ ነው ታዲኪራ ማፉብዛን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።

የማላዊ ባለሥልጣናት ማፉብዛን ለቀናት ሲፈልጉት እንደነበር ገልጸው፣ ግለሰቡ በዋና ከተማዋ ሊሎንግዌ ውስጥ እጁን መስጠቱንም ገልጸዋል።

የፖሊስ ቃለ አቀባይ በሰሜናዊ ማላዊ ከተገኘው የጅምላ መቃብር ጋር ማፉብዛ ግንኙነት እንዳለው ጠንካራ ማስረጃ እንዳላቸው አስረድተዋል።

ሁሉም አስከሬኖች በድብቅ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲወሰዱ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንደሆነ ተሰምቷል።

የአካባቢው ወጣቶች ደኑ ውስጥ የሚያውክ ሽታ እንዳለ መጠቆማቸውን ተከትሎ ነበር አስክሬኖቹ በቁፋሮ የተገኙት።

ይህ የጅምላ መቃብር ከተገኘ በኋላ በቅርብ ርቀት ሌላ የጅምላ መቃብር ተገኝቶ ተጨማሪ አራት አስክሬኖችን ፖሊስ አውጥቷል።

የማላዊ የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትር ጃን ሴንዴዝ “በጣም የሚያሳዝን ነው። አስከፍቶናል። መንግሥታችን እንዲህ ያለ ድርጊትን በጽኑ ያወግዛል። ትክክል አይደለም። በጎ አይደለም” ሲሉ ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረው ነበር።

የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም፣ ኢትዮጵያ ከማላዊ መንግሥት ጋር በመተባበር ስለ ክስተቱ ምርመራ እያደረገች ነው ሲሉ በወቅቱ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

አምባሳደር መለስ፣ በክስተቱ ሐዘን እንደተሰማቸው ገልጸው፣ የምርመራውን ውጤት ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርጉም መናገራቸው ይታወሳል።

ያለፈው ሰኔ የመንግሥታቱ ድርጅት ባወጣው መግለጫ በማላዊ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ በርካታ የሕገ ወጥ ሰዎች ዝውውር ሰለባ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙና ብዝበዛ እንደሚደርስባቸው ማስታወቁ አይዘነጋም።

ድዛሌካ በተሰኘው የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ በወንዶች፣ በሴቶች እና በሕጻናት ላይ መጠነ ሰፊ ብዝበዛ እንደሚደርስ ይፋ የተደረገው በተባበሩት መንግሥታት የመድኃኒት እና የወንጀል ጽሕፈት ቤት (ዩኤንኦዲሲ) እና የማላዊ ፖሊስ ባደረጉት የጥምረት ክትትል ነው።

ማላዊ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ከሚፈተኑ አገራት አንዷ ናት።

ከኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ሌሎም የአፍሪካ ቀንድ አገራት ወንዶች፣ ሴቶችና ሕጻናት ጭምር በማላዊ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ አውሮፓ እና አሜሪካ ለማቅናት ይሞክራሉ።

ጉዟቸው ግን በስቃይና በእንግልት የተሞላ ባስ ሲልም ለሞት የሚዳርግ ነው።

ከሁለት ዓመት በፊት የማላዊ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀድሞው የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኡላዲ ሙሳን ከስደተኞች ዝውውር ጋር በተያያዘ የአምስት ዓመት እስራት ፈርዶበታል።