ዝቅተኛ የተሽከርካሪዎች ቁጥር ባላት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ ለምን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጋዜጠኛ ፍሬሕይወት ታምሩ ለረጅም ዓመታት ኦቢኤን (ኦሮሚያ ብሮድካስት ኔትወርክ) በተባለ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዜና በማቅረብ ነው የምትታወቀው።
በ2001 ዓ.ም በአዳማ ከተማ በተካሄደው የቁንጅና ውድድር አሸናፊ የነበረችው ፍሬሕይወት፣ በከተማዋ አምባሳደር በመሆን በበርካታ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ ተሳትፋ መልካም አስተዋጽኦ አበርክታለች።
በ2006 ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ ከሥራ ስትምለስ ያጋጠማት አሳዛኝ አደጋ ቤተሰቦቿን እና የሚያውቋትን ሁሉ እጅግ ያስደነገጠ ነበር።
“ሾፌሩ ቀኑን ሙሉ መኪና ሲነዳ ውሎ ደክሞት እያንቀላፋ ስለነበረ መኪናው መንገድ ስቶ በመገልበጡ ነው አደጋው የደረሰብን” ትላለች ክስተቱን ስታስታውስ።
በደረሰባት የትራፊክ አደጋ አንድ እግሯን አጥታለች። የደረሰባት የአካል ጉዳት አምና ለመቀበል ተቸግራ፣ በእንዲህ ያለው አጋጣሚ አካል ጉዳተኛ መሆኗ በወቅቱ ሥነልቦናዋን ጎድቶታል።
“ከዚህ የተነሳ የትራፊክ አደጋ መድረሱን በሰማሁ ቁጥር የደረሰብኝን ያስታውሰኝ እና እደነግጣለሁ። በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ከሚያጡት ሰዎች በተጨማሪ በአደጋ ምክንያት የአካል ጉዳተኛ ሆነው በየቤታቸው የቀሩ ብዙዎች ናቸው” ትላለች።
ጋዜጠኛ ፍሬሕይወት በአደጋው ምክንያት ግራ እግሯን በማጣቷ የማይረሳ ጠባሳ ትቶባታል። ነገር ግን በቤተሰቦቿ እርዳታ ከደረሰባት አካላዊ እና ሥነልቦናዊ ጉዳት በማገገም ወደ ሥራዋ ተመልሳለች።
በአሁኑ ጊዜ በሰው ሰራሽ እግር እየታገዘች ነው የዕለት ከዕለት ሥራዋን የምትከውነው።
አደጋው ከደረሰባት ወዲህ በመገናኛ ብዙኃን፣ በመድረኮች እና በሌሎች አጋጣሚዎች ሁሉ ስለ ትራፊክ አደጋ ትምህርት እና ተሞክሮዋን ታጋራለች።
“እኔ ከአደጋው ተርፌ ለሌላ ሰው መማሪያ ሆኛለሁ። ሰዎች ግን ዛሬም ከአደጋዎች እየተማሩ አይደለም። ከመጠን በላይ መጫን፣ ትራፊክ ፖሊስ ሲያዩ ብቻ ቀበቶ መታጠቅ እና ሌሎች የደንብ ጥሰቶች አደጋው እንዳይቀንስ አድርጎታል” ትላለች።
እንደ ፍሬሕይወት ሁሉ ሌሎች አሳዛኝ የትራፊክ አደጋ ታሪኮች በበርካታ ቤተሰቦች ውስጥ አጋጥሞ ከፍተኛ መመሳቀልን አስከትሏል።
በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ፣ በክልል ከተሞች በየሰዓቱ እና በየቀኑ የሚደርሱ አደጋዎች ልጆችን ወላጅ አልባ፣ ወላጆችን ያለ ጧሪ አስቀርተዋል።
በቅርቡ እንኳ በኦሮሚያ ክልል ባጋጠመ አደጋ 17 የመደ ወላቡ ዩንቨርሲቲ መምህራን ለማስተማር ወደ ሻሸመኔ ካምፓስ በመጓዝ ላይ እያሉ ሕይወታቸው ማለፉ ተሰምቷል።
በአደጋው በዩኒቨርስቲው የሚገኙ የትምህርት ክፍሎች በሙሉ መምህራኖቻቸውን በመጣት ጉዳት ቢደርስባቸውም፣ በተለይ ደግሞ የአካል ብቃት (ስፖርት) ሳይንስ ትምህርት ክፍል ግን ከፍተኛውን ጉዳት ያስተናገደ ሆኗል።
ቁጥሮች ምን ይናገራሉ?
በኢትዮጵያ በየቀኑ በአማካይ 14 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ምክንያት ሕይወታቸውን እንደሚያጡ እና 31 ያህሉ ደግሞ ለከባድ የአካል ጉዳት እንደሚዳረጉ ከመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በአገሪቱ ከሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች 68.3 በመቶ ያህሉ ምቹ በሆኑ መንገዶች ላይ የሚከሰቱ መሆናቸው እና ከሚደርሱት አደጋዎች መካከል 85.9 በመቶ በአሽከርካሪው ስህተት፣ 3.3 በመቶ በተሽከርካሪ የቴክኒክ ብቃት ጉድለት፣ 2.8 በመቶው ደግሞ በእግረኞች ችግር የሚያጋጥሙ ናቸው።
በመንገድ ችግር የሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች 0.7 በመቶ ብቻ መሆናቸውን የመንገድ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ጥናት ያመለክታል፡፡
በኢትዮጵያ በ2014 ዓ.ም በትራፊክ አደጋ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 3,971 ሲሆን፣ በ2013 ዓ.ም ከተከሰተው የሞት አደጋ ጋር ሲነጻጸር በ190 መቀነሱ ይነገራል።
በ5,911 ሰዎች ላይም ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰ የመንገድ ደኅንነት እና የመድህን ፈንድ አገልግሎት አስታውቋል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መረጃዎች እንደሚያሳዩት በ2013 በጀት ዓመት ከ15 ሺህ በላይ የትራፊክ አደጋዎች ያጋጠሙ ሲሆን፣ በአደጋዎቹ ምክንያትም 4,161 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዝቅተኛ የተሽከርካሪ ቁጥር - ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ
በኢትዮጵያ የመንገድ ደኅንነትን በበላይነት የሚመራው የመንገድ ደኅንነት እና መድን ፈንድ አገልግሎት በአገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመው በ2014 ነው።
አቶ ዮሐንስ ለማ በዚሁ ድርጅት የመንገድ ደኅንነት ትምህርት እና አቅም ግንባታ ሥራ አስፈጻሚ ናቸው።
በርካቶች የትራፊክ አደጋ ቁጥር እየጨመረ ነው ቢሉም በአሃዝ ደረጃ ግን መቀነሱን ሥራ አስፈፃሚው ይናገራሉ።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የትራፊክ አደጋ የመቀነስ አዝማሚያ እንዳለው የሚጠቁሙት አቶ ዮሐንስ፣ እንደ አገር በአነስተኛ ተሽከርካሪ ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ እንደሚመዘገብ አመልክተዋል።
“መረጃዎችን መሠረት አድርገን የምናወራ ከሆነ ከ2010 እስከ 2014 ባለው ጊዜ ውስጥ አደጋው በተወሰነ መልኩ የመቀነስ አዝማሚያ እንደሚያሳይ ማየት ይቻላል” ይላሉ።
ቀነሰ ቢሉም እያንዳንዱ በሕይወት፣ በአካልም ሆነ በንብረት ላይ የሚደርሰው አደጋ አሳሳቢ መሆኑንም ያሰምሩበታል።
በተለይም ዝቅተኛ የተሽከርካሪ ቁጥር ላላት አገር [1.4 ሚሊዮን ተሽከርካሪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ ተብሎ ይታመናል] የአደጋው መጠን ከፍተኛ ነው።
ከአቶ ዮሐንስ ያገኘነው አሃዛዊ መረጃ እንደሚያመለክተው በ2010 ብቻ 5,118 ሰዎች በመንገድ ትራፊክ አደጋ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በተመሳሳይ ዓመት የነበረው የአገሪቱ የተሽከርካሪ ቁጥር ከ900 ሺህ እምብዛም የዘለለ አልነበረም።
2014ን ስንመለከት ደግሞ የተሽከርካሪዎች ቁጥር በ500 ሺህ ገደማ ጨምሮ 1.5 ሚሊዮን ደርሷል። በዚሁ ዓመት በደረሰ የትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ግን 3,971 ነበር።
“እዚህ ላይ የምናየው ነገር ከ900 ሺህ ብዙም ያልዘለለ የተሽከርካሪዎች ቁጥር ይዘን ከፍተኛ የሰው ሕይወት ነው ያለፈው። 2014 ላይ የነበረን የተሽከርካሪ ቁጥር በ500 ሺህ ያህል ጨምሮ በመንገድ ትራፊክ አደጋ ያጣናቸው ግን በተወሰነ መልኩ መቀነሱን የሚያሳይ ነው” ይላሉ አቶ ዮሐንስ።
የዓለም አቀፉ የተሽከርካሪ አደጋ መመዘኛ በአስር ሺህ መኪኖች ምን ያህል አደጋ ይደርሳል ሲል ይመዝናል።
በኢትዮጵያ ይህንን መስፈርት ተከትለን ስናየው በ2010 ዓ.ም በአስር ሺህ ተሽከርካሪዎች የደረሰው አደጋ 54 ነበር።
ተመሳሳይ ቁጥር ባላቸው ተሽከረካሪዎች በ2014 ዓ.ም የደረሰው አደጋ ግን 29.7 መሆኑን ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።
“ይህ ቁጥርን መሠረት አድርገን ስንነጋገር ነው። ሆኖም ግን ሰውን መሠረት አድርገን ስንንነጋገር ነው ችግሩ የገዘፈ የሚሆነው። ይህም ‘አንድ ሰው ለቤተሰቡ ለአገሩ ምንድን ነው?’ የሚለው ላይ ይወስደናል” ይላሉ።
የትራፊክ ደኅንነት በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ
ለአቶ ዮሐንስ አብዛኛዎቹ ትራፊክ አደጋዎች መነሻቸው ከአሽከርካሪዎች ጋር የሚገናኝ ነው።
አብዛኛወቹ አደጋዎች የሚከሰቱ ከፍጥነት ጋር በተገናኘ ሲሆን፣ ለእግረኛ ቅድሚያ አለመስጠት በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነገር ነው። የአሽከርካሪን ባህሪ መሠረት ያደረጉ ችግሮችም አሉ።
“ትልቁ ችግር የማሽከርከር አቅም ሳይሆን የባህሪ ችግር ነው። ቸልተኝነት ይበዛል። አደጋ ካልደረሰ አለመማር አለ። አብዛኛው አደጋ የሚደርሰው በአሽከርካሪዎች ስህተት ሲሆን፣ እሱም ባህሪን የሚገለጽ ነው” በማለት ያስረዳሉ።
ይህ ከአሽከርካሪዎች ባህሪ ጋር ተያይዞ የሚጠቀስ ምክንያትም በሌሊት መጓዝን፣ በፍጥነት ማሽከርከርን፣ ጠጥቶ ማሽከርከርን፣ ቅድሚያ አለመስጠትን እና ሌሎችንም እንደሚያካትት መሆኑን ይገልጻሉ።
ከዚህ በተጨማሪም ተሽከርካሪዎች ለመንቀሳቀስ የሚያበቃ የቴክኒክ ብቃት ሳይኖራቸው “አድርሶ ይመልሰኛል” ብሎ በማሰብ ዝም ብሎ የማሽከርከር ሁኔታዎች ይታያሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ የተሽከርካሪ አደጋ በተደጋጋሚ የሚደርስባቸው ቦታዎች አሉ። በሁሉም ክልሎች ለትራፊክ አደጋ ምክንያት ጥቁር ነጥብ ያላቸው ቦታዎችም ተለይተዋል።
እነዚህ በተለይም ረዥም ርቀት ጉዞ የሚደረግባቸው፣ በሌሊት እና በፍጥነት ጉዞ የሚካሄድባቸው ናቸው።
“ደረጃቸው ነው እንጂ የሚለያየው በጥናት የተለዩ በእያንዳንዱ ክልል ተደጋጋሚ አደጋ ሚደርስባቸው ቦታዎች አሉ” ይላሉ አቶ ዮሐንስ።
የመንገድ ደኅንነት እና መድን ፈንድ አገልግሎት እንደ ተቋም በቀርቡ ቢቋቋሙም ከዚህ በፊትም የመንገድ ደኅንነትን ለማረጋገጥ ሥራዎች እየተሠሩ እንደነበር ሥራ አስፈፃሚው ይገልጻሉ።
መንግሥት የትራፊክ አደጋ ችግርን ለመቅረፍ በሚል በአገር አቀፍ ደረጃ የመንገድ ደኅንነት ትምህርት ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል በተለያዩ የትምህርት ዓይነቶች ውስጥ እንዲሰጥ በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ተካቷል።
ለዚህም ምክንያቱ የባህሪ ለውጥን ለማምጣት መሆኑን በመጥቀስ፣ የመንገድ ደኅንነት ትምህርት አሽከርካሪዎች መንጃ ፈቃድ ለማውጣት ሲሉ ብቻ ሲሰጥ ብቻ የነበረ በመሆኑ፣ በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲገባ መደረጉን ሥራ አሰፈጻሚው ተናግረዋል።
“ይህን ታሳቢ በማድረግ እንደ ሙከራ ተጀምሯል። በቀጣይ ተጠናክሮ ይካሄዳል” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።
ትምህርት መስጠት ብቻ ሳይሆን ግንዛቤ ማስጨበጥ እና የቁጥጥር ሥራም ጎን ለጎን እየተካሄደ ነው። የራዳር እና የአሽከርካሪዎችን የአልኮል መጠንን የመለካት ሥራም ይከናወናል።
ከዚህ ጎን ለጎን የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በመገናኛ ብዙኃን እና በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን እየተሠሩ መሆናቸው ተደማምረው “ውጤት እያሳዩ ያሉ ነገሮች አሉ” ይላሉ።
ከህሊናቸው የማይጠፉ አደጋዎች
ከሞጆ መስመር ወደ አዲስ አበባ የሚሄድ አንድ መኪና መነሻው ከሻሻመኔ አካባቢ ነበር። አቶ ዮሐንስ እንደሚሉት መኪናው ሌሊት ላይ ነው ሲጓዝ የመጣው።
“ሞጆ አካባቢ ሲደርስ ከቆመ መኪና ጋር በመጋጨቱ እዚያው ውስጥ ነበሩ በአሥራዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። ቦታው ላይ ተገኝቼ ስለነበር ምን ያህል ዘግናኝ እንደነበረ ያየሁት ነው” በማለት ያስታውሳሉ።
ሌላው አሳዛኝ አደጋ ሱሉልታ አካባቢ ያጋጠመ ሲሆን፣ አንድ መኪና ከቦቴ ጋር ተጋጭቶ ነዳጁ በእሳት በመያያዙ መኪናው ውስጥ የነበሩ ሰዎች በሚዘገንን ሁኔታ ሕይወታቸውን ያጡበት ነበር።












