ዶናት ጋጋሪው፣ የሎሚ ጭማቂ አዟሪው፣ ሰሊጥ ቸርቻሪው ጣይብ ኤርዶዋን ማን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, EPA
ለቱርካውያን ሙስጠፋ ከማል አታቱርክን የሚያህል አገር ያቀና የፖለቲካ-ሰብ የለም።
በከማል አታቱርክ አይደራደሩም።
የታሪክ ሐቅ ሆኖ ግን ከከማል ቀጥሎ ቱርክ ላይ ትልቅ አሻራ ያኖሩት ሰው ጣይብ ኤርዶዋን ሆነዋል።
ላለፉት 20 ዓመታት አገሪቱን መርተዋል።
በብዙ ቢተቹም በብዙ ሠርተዋል። ተጽእኗቸው ዓለም አቀፋዊ ነው። ከአትላንቲክ ወዲህም ወዲያም ይነሳሉ፤ በክፉም በደጉም።
ከሩሲያ ጋር በሶሪያ ጉዳይ ቢለያዩም፣ በንግድ ይተሳሰራሉ። ከፑቲን ጋር ቢጨባበጡም፣ በዩክሬን በከፈቱት ጦርነት ደስተኛ አይደሉም።
ሆኖም ለዜሌንስኪም ለፑቲንም ቅርብ መሆንን አውቀውበታል።
አዘርባጃንን ደግፈው አርሜኒያን ልክ አስገብተዋል።
የኔቶ አባል ቢሆኑም ስዊድን በአባልነት እንዳትገባ ጭንቅ ውስጥ እንደከተቷት አሉ። ፊንላንድም በብዙ ጭንቅ ነው ኤርዶዋን ፈቅደው ኔቶ አባል የሆነችው።
እጃቸው ረዥም ነው። በሊቢያም፣ በሶማሊያም፣ በኢትዮጵያም ተጽእኗቸው ፍዝ ነው የሚል የለም።
ለመሆኑ ዛሬ ለሁለተኛ ዙር ምርጫ የሚወዳደሩት እና ከዓለም ተጽእኖ ፈጣሪ መሪዎች አንዱ የሆኑት የቱርኩ ረሲብ ጣይብ ኤርዶዋን ማን ናቸው?
ድህነት እና ልጅነት
ኤርዶዋን አሁን ሲታዩ አዛውንት ይመስላሉ እንጂ 70 እንኳ አልደፈኑም።
የጥቁር ባሕር ጠረፍ ጠባቂ ወታደር ከነበሩ አባት በፈረንጆቹ 1954 ነው የተወለዱት።
ሰሜን ቱርክ የተወለዱት ኤርዶዋን 13 ዓመት ሲሞላቸው አባታቸው ወደ ኢስታንቡል ይዘው አመጧቸው።
የኤርዶዋን አባት 5 ልጆቻቸውን በተሻለ ሁኔታ ለማሳደግ ነበር ወደ ኢነስታንቡል የመጡት።
ኑሮ ግን በኢስታንቡል የሚቀመስ አልነበረም።
ወጣቱ ኤርዶዋን የሎሚ ጭማቂ መሸጥ ጀመሩ። ሰሊጥ ማዞር ጀመሩ። ቤግል ዶናት መቸርቸር ያዙ። ሳንቲም ለመያዝ ነው ይህ ሁሉ መከራ።
ወጣቱ ኤርዶዋን ከቢዝነሱ ጎን ለጎን ኢስላማዊ መንፈሳዊ ትምህርትር መማር ጀመሩ።
ማርማር ዩኒቨርስቲ ገብተው በሥነ አስተዳደር ዲግሪ ያዙ።
ተቃዋሚዎቻቸው ግን ይሄ ዲግሪ የተጭበረበረ ነው እያሉ ያሟቸዋል። ኤርዶዋን ግን ይህን ያስተባብላሉ።
ወጣቱ ኤርዶዋን እግር ኳስ አፍቃሪ ነበሩ። በከፊል ፕሮፌሽናል ለሆኑ ቡድኖች እስከመጫወት ደርሰዋል። ይህ ታዲያ ድሮ ነው። በፈረንጆቹ 1980ዎቹ አካባቢ።
ይሁንና ኤርዶዋን ከእግር ኳስ ይበልጥ የሚወዱት አንድ ነገር ነበር። ፖለቲካ!
ኤርዶዋን ወጣት ሳሉ በኢስላማዊ የውይይት ክበቦች ንቁ ተሳታፊ ነበሩ።
ኢስላማዊ ዝንባሌ የነበረውን ‘ዌልፌር’ የተባለውን ፓርቲ ተቀላቀሉ።
በ1990ዎቹ ይህ ፓርቲ ስሙ እየገዘፈ መጣ። ኤርዶዋንም ተሰሚነታቸው ከፓርቲው እኩል ጨመረ።

የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE
ለኢስታንቡል ከንቲባነት ፓርቲውን ወክለው ተወዳደሩ። ይህ በፈረንጆቹ 1994 የሆነ ነው። አሸነፉ። ለአራት ዓመታት ኢስታንቡልን በከንቲባነት መሩ።
የቱርክ የመጀመሪያው ኢስላም ዘመም ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ኢርባካን ለአንድ ዓመት አገሪቱን እንደመሩ ነበር በወታደሮች የተገለበጡት።
ኤርዶዋንም በኢስላማዊ አመለካከታቸው ከማንኛውም ሃይማኖታዊ ተጽእኖ ነጻ የሆነውን የቱርክ ፖለቲካ ኢስላማዊ ሊያደርጉ ነው በሚል ተወነጀሉ።
በዚያው ዓመት አንድ ያልተፈቀደ ግጥም በአደባባይ አንብበዋል በሚል ተከሰሱ።
በዚያ ግጥም ውስጥ እንዲህ የሚሉ ስንኞች ይገኙበት ነበር፡
‘መስጊዱ ምሽጋችን፥ ጉልላቱ ቆባችን፣
ሚናራውስ ቢባል አይደለም ወይ ሳንጃችን፤
የእምነታችን የልባችን
ኤርዶዋን በዚህ ግጥም አራት ወራት ታሰሩ። ከዚያም ሲወጡ ብሶባቸው ወደ ፖለቲካ ተመለሱ።
በ1998 በፈረንጆቹ ፓርቲያቸው ታገደ። የፖለቲካ ቡድኑ እስልምናን ፖለቲካ ውስጥ ለማስገባት ሞክሯል በሚል ነው የታገደው።
በነሐሴ 2021 ኤርዶዋን እና ጓደኞቻቸው አዲስ ፓርቲ መሠረቱ። የፍትሕ እና የእድገት ፓርቲ ወይም በእንግሊዝኛ ምሕጻሩ (AKP) ይባላል።
ይህ ፓርቲ ቶሎ ስሙ ገነነ። በተለይ እስልምና ገሸሽ እየተደረገ ነው በሚሉ ቱርካውያን ዘንድ ተወደደ። ኑሮ በከበዳቸው ዜጎች ተሞገሰ።
በ2002 አክፕ ፓርቲ (AKP) በፓርላማ አብላጫ መቀመጫ አሸነፈ። በቀጣዩ ዓመት ኤርዶዋን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ።
ይኸው ያኔ የተቆናጠጡ ሥልጣን ላይ እስከ ዛሬ ድረስ አሉ።
ለሌላ ዙር የአስተዳደር ዘመን እየተፋለሙ አሉ።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ሦስት የሥልጣን ዘመን በጠቅላይ ሚኒስትርነት
ኤርዶዋን ከ2003 ጀምሮ በሦስት የሥልጣን ዘመን ቱርክን በጠቅላይ ሚኒስትርነት መርተዋል።
በአገር ቤት መልካም የሚባል የምጣኔ ሃብት መነቃቃትን የፈጠሩ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ተራማጅ ተደርገው የተወሰዱበት ዘመን ነበር።
መካከለኛ ገቢ ያለው ሕዝብ ቁጥር በእርሳቸው ዘመን ጨምሯል።
ሚሊዮን ቱርካውያን ከድህነት ማጥ ወጥተዋል።
ቱርኮችን ለማዘመን ኤርዶዋን ግዙፍ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት ላይ በማተኮር ይታወቃሉ።
ኤርዶዋን አናሳ ቁጥር ካለው የቱርክ ኩርዲሽ ፓርቲ መራጮች ድጋፍ አግኝተው ነበር በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው።
የኩርዶች ነጻነትም አንጻራዊ በሆነ ሁኔታ ጨምሮ ታይቷል። በመጋቢት 2013 የቱርክ ሠራተኛ ፓርቲ (ፒኬኬ) የሰላም ስምምነት ለማድረግም ተስማምቶ ለኤርዶዋን ትልቅ ድል ተደርጎ ተወስዶ ነበር።
ነገር ግን ስምምነቱ ለሁለት ዓመት ብቻ ነበር የጸናው። ከዚያ በኋላ ለሦስት አሥርታት የቆየው መተላለቅ ዳግም ተመለሰ።
ከ2013 (እአአ) ወዲህ ኤርዶዋን አምባገነን የመሆን አዝማሚያ ያሳዩበት ጊዜ ነው ይላሉ ተቺዎቻቸው።
በዚያ ጊዜ መንግሥት በነዋሪዎች እጅግ የሚወደደውን ኢስታንቡል የሚገኘውን ፓርክ ካልቀየርኩ አለ።
ሕዝብ ለተቃውሞ በነቂስ አደባባይ ወጣ። ኤርዶዋን ፖሊስ ኃይል እንዲጠቀም አዘዙ። ሕዝቡ ባሰበት።
ኢስታንቡል በተቃውሞ ተናጠች። ተቃውሞው መልኩን እየቀየረ መጣ። ኤርዶዋን ተቆጡ።
የፖለቲካ ተንታኞች ይህ ወቅት ኤርዶዋን ከዲሞክራት መሪነት ወደ የቱርክ ሥርወ መንግሥት ሡልጣንነት ያዘመሙበት ወቅት ነው ሲሉ ይገልጹታል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ኤርዶዋን አክራሪ ኢስላማዊ ናቸው?
ኤርዶዋንን ተቃዋሚዎች ቱርክን ወደ ኢስላማዊ መንግሥት ሊመልሷት ነው ብለው ሲሰጉ ኖረዋል።
ይህ የሆነው ከኤርዶዋን አስተዳደግ፣ ትምህርት እና ፖለቲካዊ ፍልስፍና በመነሳት ነው።
ቱርክ ሃይማኖት እና ፖለቲካን ላለማጋባት ጥብቅ መሀላ የገባች አገር ናት።
ዕድሜ ለአባት ሙስጠፋ ከማል አታቱርክ ኢስላማዊ መንግሥት መመሥረት እንደ ነውር የሚታይ ሐሳብ ነው።
ሃይማኖት የግል - መንግሥት የጋራ በሚል ፍልስፍና ያምናሉ።
ኤርዶዋን ግን ኢስላማዊ እሴቶችም አብረው ሊገፉ አይገባም የሚል አቋም አላቸው።
ለምሳሌ ሒጃብን በሥራ ቦታ እና በዩኒቨርስቲ መልበስ ፍጹም ክልክል ተደርጎ ነበር በቱርክ።
ኤርዶዋን “መብታችሁ ነው” ብለው ክልከላውን አነሱት።
ክብርት ባለቤታቸውም በአደባባይ ሒጃብ ለብሰው ይታያሉ።
የኢርዶዋን ተቺዎች አገራችንን ኢስላማዊ ሊያደርጋት ነው ቢሏቸውም፣ እርሳቸው ግን “እኔ የሕዝቤን የእምነት ነጻነት ነው የማስከብረው እንጂ ሃይማኖታዊ ፖለቲካን በቱርክ ልመልስ አልሠራም” ይላሉ።
ይሁንና በተደጋጋሚ የሴቶች ዋና ሚና በማኅበረሰብ ውስጥ “ልጅ ማሳደግ እና መንከባከብ - መልካም ሚስት መሆን እና የመሳሰሉት ናቸው” የሚል ሐሳብን ያንጸባርቃሉ።
የሥነ ጾታ ሥርዓት ተሟጋቾችን (ፌሚኒስት) ሐሳቦችን ኤርዶዋን ያጥላላሉ።
ልውጥ ጾታ፣ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ እና የመሳሰሉ ምዕራቡ በስፋት የሚያንቆለጳጵሳቸውን እሴቶች በአደባባይ ይተቻሉ።
ኤርዶዋን በግብፅ ሙስሊም ወንድማማቾችን በመደገፍ ይታወቃሉ።
በ2020 ኤርዶዋን የኢስታንቡልን ታሪካዊ የሃጊያ ሶፊያ ቅርስ ወደ መስጊድነት መለሱት።
ይህ ድርጊት በመላው ዓለም የሚገኙ ሚሊዮን ክርስቲያኖችን እና ለዘብተኛ ሙስሊም ቱርካዊያንን ያስቆጣ ድርጊት ነበር።
ይህ ግዙፍ ቅርስ ከ1500 ዓመታት በፊት የተገነባ ነው። ሲገነባ ደግሞ ቤተ-ክርስቲያን ነበር።
ኦቶማን ቱርኮች ወደ መስጊድነት ቀየሩት። የቱርክ አባት ከማል አታቱርክ ደግሞ ሙዝየም አደረገው።
ቅርሱ ለብዙዎች በቱርክ የሃይማኖት እና የመንግሥትን መለያየት የሚያጎናጽፍ ተደርጎ ይታይ ነበር። ይህንን ነው ኤርዶዋን ወደ መስጊድነት የቀየሩት።

የፎቶው ባለመብት, AFP
የኤርዶዋን የመጨረሻው የሥልጣን ዘመን?
ኤርዶዋን በ2014 ዳግም ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን መወዳደር ሕገ መንግሥት አልፈቅድላቸው ሲል ፕሬዝዳንታዊ ሥርዓት አሰናዱ።
ይሁንና ይህን ባደረጉ በቀጣይ ዓመት ሁለት ፈተና ተደቀነባቸው። ፓርቲያቸው በፓርላማ አብላጫ መቀመጫዎች መያዙ አበቃ።
በ2016 ደግሞ በቱርክ ታሪክ ሆኖ የማያውቅ ሆነ። መፈንቅለ መንግሥት ተሞከረባቸው።
300 ሰላማዊ ዜጎች ተገደሉ። ኤርዶዋን በስልካቸው ለሕዝባቸው ንግግር አደረጉ። “አትነሳም ወይ” አሉት ሕዝቡን።
ሕዝቡ በነቂስ ወጣና ታንኩን አስቆመላቸው።
ፈቱላህ ጉለን የሚባሉ፣ መኖሪያቸውን አሜሪካ ያደረጉ ሰው ናቸው ያሴሩብኝ አሉ። ከፈቱላህ ጉለን ጋር የሚያያዝ ግብረ ሰናይ ድርጅት ይሁን ትምህርት ቤት በመላው ዓለም ታድኖ ተዘጋ።
ከቡድኑ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ 15 ሺህ የመንግሥት ሠራተኞች ከሥራ ተባረሩ። 50 ሺህ ዜጎች ታሰሩ።
ከእነዚህ መካከል ወታደር፣ ጋዜጠኛ፣ ጠበቃ፣ ፖሊስ፣ መምህር ሳይቀር ከመፈንቅለ መንግሥቱ መከራ በኋላ ከሥራ ተባረሩ፣ ወደ እስር ተጋዙ።
ጄኔራሎች ጦር ፍርድ ቤት ቀረቡ።
ኤርዶዋን ከዚህ መፈንቅለ መንግሥት በኋላ ሌላ ሰው ሆኑ። ለአውሮፓውያንም ፊት መስጠት አቆሙ።
በርካታ ስደተኞችን “ድንበር ከፍቼ ወደ አውሮፓ እለቃቸዋለሁ” ብለው አስፈራሩ። ከዛሬ ነገ የለየላቸው አምባገነን ይሆናሉ ሲባል እዚህ ደረሱ።
አሁን ያሉት እና የዛሬ 20 ዓመት የነበሩት ኤርዶዋን በብዙ ተቀይረዋል።
ጤናቸው አስተማማኝ አይደለም። ከአንድም፣ ሁለት፣ ሦስቴ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ወቅት ሕመም ተሰምቷቸው አቋርጠዋል።
የእርሳቸው ብቻ ሳይሆን የሚመሯት አገርም ታማለች።
በቱርክ የዋጋ ንረቱ ሰማይ ነክቷል። የመሠረታዊ ሸቀጥ ዋጋ አይቀመስም። በዚህ ዓመት የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ 50 ሺህ ሕዝብ ፈጅቶባቸዋል።
ያም ሆኖ የመጀመሪያውን ዙር ምርጫ ተፎካካሪያቸውን በጥቂት የድምጽ ብልጫ መርተዋል፣ ነገር ግን ቁርጥ ያለ አሸናፊ ለመሆን የሚያስችላቸውን የመራጭ ድምጽ አላገኙም።
ነገር ግን ወደቁ ሲባል የሚነሱት፣ በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ ያለፉት ኤርዶዋን ማሸነፍን ግብ አድርገዋል።
ሁለተኛው ዙር ምርጫ ዛሬ ግንቦት 20/2015 ዓ.ም. ይካሄዳል።
ኬክ ጋጋሪው ኤርዶዋን ሌላ የሥልጣን ዘመን አሸንፈው “ቱርኪዬ” በሉኝ ባል ለዓለም አዲስ ስም ላስተዋወቀችው አገራቸው አዲስ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ይጋግሩ ይሆን?












