የቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን በቀጥታ የቴሌቪዥን ቃለ መጠይቅ ወቅት በመታመማቸው ሥርጭት ተቋረጠ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ራሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን ጤና መጓደል ቱርካዊያኑን አሳስቧል።
ፕሬዝዳንቱ ማክሰኞ ምሽት በነበራቸው የቴሌቪዥን ቃለ መጠይቅ የቀጥታ ሥርጭት ላይ ድንገት በመታመማቸው መርሐ ግብሩ እንዲቋረጥ ተደርጓል።
20 ደቂቃዎች ያህል ቃለ ምልልሱ ከተቋረጠ በኋላ ኤርዶዋን ተመልሰው መጥተው የሆድ ሕመም እንደገጠማቸው ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የ69 ዓመቱ ራሲብ ጣይብ ኤርዶዋን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጤናቸው መጓደል እያሳየ፣ ሰውነታቸውም እየዛለ፣ ፊታቸውም መገርጣት እየታየበት እንደሆነ እየተዘገበ ነው።
ኤርዶዋን በቀጥታ ሥርጭት ወቅት ታመው ቃለ መጠይቅ ሲያቋርጡ የማክሰኞ ምሽቱ የመጀመርያቸው አይደለም።
በቱርክ ከሳምንት በኋላ ጠቅላላ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ይጀመራል።
ኤርዶዋን ለፕሬዝዳንትተን ከሚፎካከሯቸው ተቃዋሚው ከማል ኩሉቺተሮሉ ጋር ከባድ ፍልሚያ ይጠበቃቸዋል።
የምርጫ ድምጽ አሰጣጡ በውጭ አገራት በሚኖሩ ሦስት ሚሊዮን ቱርካዊያን ዘንድ ከወዲሁ የተጀመረ ሲሆን ከፍተኛ ቱርካዊያን በሚገኙበት ጀርመን አንድ ሚሊዮን 500ሺህ ዜጎች ድምጽ እየሰጡ ነው።
ኤርዶዋን ታመው ቴሌቪዥን ቃለ መጠይቁን ካቋረጡ በኋላ መልካም ጤንነትን ከተመኙላቸው መካከል የተቃዋሚዎች ኅብረትን በመወከል ለፕሬዝዳንትነት እየተወዳደሩ ያሉት ባላንጣቸው ከማል ኩሉቺተሮሉ አንዱ ናቸው።
የጤና ሚኒስትር ፋህረቲን ኮቻ የኤርዶዋንን መታመም ተከትሎ በሰጡት መግለጫ ‘ኤርዶዋን በመልካም ጤንነት ላይ ናቸው፤ ትንሽ ጨጓራቸው ስላመማቸው ነው፤ የሚያሳስብ ነገር የለም’ ብለዋል።
ቱርካዊያኑ ድምጽ የሚሰጡት ከግንቦት 7 ጀምሮ ነው። በዚህ ምርጫ አብላጫ ድምጽ ያገኘ እጩ ከሌለ ምርጫው ለ2ኛ ዙር ይቀጥላል።
ኤርዶዋን ይህ ማክሰኞ ምሽት ላይ በቴሌቪዥን ሥርጭት ወቅት ያጋጠማቸው ሕመም አሳሳቢ ሊሆን ይችላል የሚሉ ወገኖች ፕሬዝዳንቱ ከዚያ ቀደም ሦስት የምርጫ ቅስቀሳ መርሀ ግብሮችን መሰረዛቸውን ያወሳሉ።
የመጀመርያው ማእከላዊ አናቶሊኣ ረቡዕ ሊደረግ የነበረውን ምርጫ ቅስቀሳ ሳይገኙ ቀርተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ሐኪማቸው ቤት እንዲቆዩ እንደነገሯቸው በመጥቀስ ነው ይህን ቅስቀሳ መታደም ያልቻልኩት ብለዋል።
በነገታውም እንዲሁ የቱርክ የመጀመርያው የኒክሊየር ኃይል ማብሊያ ምረቃ ሥነ ሥርዓት በሜዲትራኒያን ዳርቻ አኩዩ ላይ ሲካሄድ አልተገኙም።
ሆኖም ከሩሲያው ቪላድሚር ፑቲን ጋር በኢንተርኔት ቪዲዮ ሥርጭት መርሐ ግብሩን ሲመርቁ ፊታቸው ገርጥቶ ታይቷል።
የአኩዩ አራት የኒክሊየር ማብሊያዎች በአብዛኛው የተያዙት በሩሲያ ሮሳቶም ኩባንያ ነው።
ማብሊያዎቹን ለመገንባት ረዥም ዓመታትን የወሰደ ሲሆን የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ከምርጫ መቃረብ ጋር እንዲሆን ተመቻችቶ ነበር የተሰናዳው።
ሆኖም ኤርዶዋን በመታመማቸው መርሐ ግብሩን ሊታደሙ የቻሉት በቪዲዮ ግንኙነት ነው።
ከምረቃው ቀደም ብሎ ፑቲንና ኤርዶዋን በስልክ የተወያዩ ሲሆን የንግድ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ስምምነት ደርሰዋል ተብሏል።
ማክሰኞ ዕለት በነበረው የቀጥታ ሥርጭት ኤርዶዋንን ቃለ ምልልስ እያደረጉ የነበሩ በርካታ ጋዜጠኞች ነበሩ። ጋዜጠኞቹ ኡልኬ ቲቪ እና ቻናል-7 ከሚባሉ ለመንግሥት ቅርብ የሆኑ ሚዲያዎች የተወከሉ ነበሩ።
የቴሌቪዥኑ ስክሪን ድንገት ከመጨለሙ በፊት አንድ ጋዜጠኛ ለኤርዶዋን ጥያቄ እየጠየቀ በድንገት ፊቱ ላይ ድንጋጤ ይታይ ጀመረ። ከዚያ ወዲያ ነው መርሀ ግብሩ የተቋረጠው።
ከአፍታ ቆይታ በኋላ ኤርዶዋን ወደ ሥርጭቱ ተመልሰው በዚህ ቃለ ምልልስ ላለመገኘት እያሰብኩ ነበር፤ ‘ትንሽ ጤንነት እየተሰማኝ አይደለም። እንዲህ ዓይነት ነገር ያጋጥማል፤ በብዙ ሥራ ተጠምደን ነው የምንውለው’ ብለዋል።
ይህ ከሆነ በኋላ ቱርካዊያን በማኅበራዊ ሚዲያ ፕሬዝዳንታቸው የልብ ሕመም እንዳጋጠማቸው በስፋት ሲነጋገሩ ነበር።
የኤርዶጋን ቃል አቀባይ ፋህረቲን አልቱን ግን የሚወራው በሙሉ ውሸት ነው ሲል አስተባብለዋል።
ኤርዶዋን በፈረንጆቹ ሰኔ 2016 መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ከተደረገባቸው ከሳምንት በኋላ በቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ ላይ እንዲሁ በድንገት ታመው ሥርጭት ተቋርጦ ነበር።
በ2011 እና 2012 ዓ/ም ደግሞ የጨጓራና አንጀት ቀዶ ጥገና ተደርጎላቸው ነበር።
ኤርዶዋን በሥልጣን የቆዩት ለ21 ዓመታት ነው።












