በቱርክ ምርጫ አብላጫ ድምፅ ያገኘ ዕጩ ባለመኖሩ ሁለተኛ ዙር ምርጫ ሊደረግ ነው

ፕረዝዳንት አርዶዋን ከደጋፊዎቻቸው ጋር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን በሁለተኛው ዙር ምርጫ የማሸነፍ ዕድል እንዳለቸው እየተነገረ ነው

ኃያሉ የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን በእሁዱ ምርጫ የበላይነት የሚሰጣቸውን ድምጽ ባለማግኘታቸው ከተቃዋሚው ተፎካካሪያቸው ጋር ለሁለተኛ ዙር ምርጫ እንደሚወዳደሩ የአገሪቱ የምርጫ ጠቅላይ ምክር ቤት አረጋገጠ።

የምክር ቤቱ ሊቀምንበር እንዳስታወቁት ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን በመጀመሪያው ዙር ምርጫ የ49.51 በመቶ የመራጮች ድምጽ አግኝተዋል።

ምንም እንኳን ተፎካካሪያቸው ከማል ኪሊችዳሮግሉ የ44.88 በመቶ መራጮችን ድምጽ በማግኘት በኤርዶዋን ቢበለጡም ሁለቱም ዕጩዎች ለአሸናፊነት የሚያበቃውን ከግምሽ በላይ ድምጽ አላገኙም።

ሁለተኛው ዙር ምርጫ ከሁለት ሳምንት በኋላ የሚካሄድ ሲሆን፣ በዚህም ኤርዶዋን የማሸነፍ ዕድል እንዳላቸው እየተነገረ ነው።

የአገሪቱ ምርጫ ምክር ቤት ሁለተኛ ዙር ምርጫ እንደሚካሄድ ከማሳወቁ ቀደም ብሎ፣ ተቃዋሚው ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር “ተስፋ መቁረጥ እንደሌለባቸው” በማሳሰብ በቀጣይ ምርጫ በመሳተፍ አሸናፊ ለመሆን እንዲዘጋጁ ጥሪ አቅርበዋል።

ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን በቱርክ የመሪነት የሥልጣን መንበር ላይ መጀመሪያ በጠቅላይ ሚኒስትርነት፣ ቀጥሎ በፕሬዝዳንትነት ከ20 ዓመታት በላይ ቆይተዋል። በአውሮፓውያኑ 2016 የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተደርጎባቸው አክሽፈው የሥልጣን ዘመናቸውን አራዝመዋል።

የተቃዋሚ ፓርቲው ዕጩው መሠረተ ሰፊ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ትብብርን መፍጠር በመቻላቸው፣ ፕሬዝዳንቱን ከሁለት አስርት ዓመታት የሥልጣን መንበራቸው በምርጫ ሊያሸንፏቸው ይችላሉ የሚል ግምት በስፋት ሲነገር ነበር።

የምርጫ ምክር ቤቱ እንዳለው እሁድ ዕለት ድምጽ የተሰጠባቸው ሁሉም ሳጥኖች ተከፍተው የተቆጠሩ ሲሆን፣ በምርጫው ለመሳተፍ ከተመዘገበው ሕዝብ 88.92 በመቶው መርጧል።

ነገር ግን ከቱርክ ውጪ የተሰጡ ድምጾች አስካሁን ያልተቆጠሩ መሆናቸውም ተነግሯል። ነገር ግን አስካሁን ባለው ውጤት ላይ የጎላ ለውጥ የሚያስከትሉ አይደሉም።

ዓለም አቀፍ የምርጫ ተቆጣጣሪ ቡድን (ኦኤስሲኢ) ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን እና ፓርቲያቸው “ተገቢ ያልሆነ ተጠቃሚነትን” አግኝተዋል በማለት በምርጫው ሂደት ያጋጠሙ በርካታ እንከኖችን ጠቁሟል።