የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ

የፎቶው ባለመብት, pm office
ያለፉት 40 ዓመታት ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ በብዙ መልኩ ሊገለጹ ይችላሉ። አንድ አገር ከመሆን ወደ ሁለት ተሸጋግረዋል።
ድንበር፣ ደም፣ ባህል፣ ሃይማኖት እና ሌላም ሌላም የሚጋሩት አገራት ደም እስከ መቃባት ደርሰው ሺህዎችን ቀብረዋል።
ተካስሰዋል፣ የሠላም ስምምነት ፈርመዋል፣ ተፋጥጠው ለዓመታት በዐይነ ቁራኛ ሲጠባባቁ ቆይተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ ግን ነገሮች ተቀይረው፣ ሁሉም ተረስቶ፣ ሁለቱ አገራት ሠላማዊ ግንኙነታቸውን ጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአገራቸው ውስጥ ለውጥ ለማምጣት መውሰድ በጀመሯቸው እርምጃዎች እና በተለይ ከኤርትራ ጋር ሠላም ለማውረድ በወሰዱት እርምጃ 100ኛውን የኖቤል የሠላም ሽልማት አሸናፊ እስከ መሆን ደረሰዋል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ አሥመራ እና አዲስ አበባ በመጓዝ ተደጋጋሚ ጉብኝት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
እነዚህ ጉብኝቶች በተካሄዱባቸው ጊዜያት ሁሉ መሪዎቹ በአገራቱ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩሩ በደፈናው ይጠቀሳል።
ነገር ግን የተደረጉ ውይይቶች እና የተደረሱባቸው ስምምነቶች ዝርዝር መረጃ አይሰጥም።
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት መሠረት
የሰሜን ኢትዮጵያው ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ሠላም ሲወርድ ምዕራባውያን እና ሌሎች ወገኖች አድናቆታቸውን ሲገልጹ የኤርትራን ስም ከመብት ጥሰቶች አንጻር አሁን ድረስ እያነሱ ቀጥለዋል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስም ወደ አዲስ አበባ በተደጋጋሚ ያደርጉት የነበረው ጉብኝት ከቆመ ረጅም ጊዜ ሆኖታል።
ከኤርትራ በኩል ለመጨረሻ ጊዜ ጉብኝት የተደረገው ባለፈው መጋቢት በጄኔራል አብርሃ ካሳ በተመራው ከፍተኛ የጦር እና የደኅንት ባለሥልጣናት ቡድን ነው።
አምባሳደር እውነቱ ብላታ በቻይና፣ በአውሮፓ ኅብረት እና በአሜሪካ ኢትዮጵያን ወክለው በዲፕሎማትነት ሠርተዋል።
ከአስተማሪነት እስከ ሚኒስትርነት፣ ከሚኒስትርነት እስከ ዲፕሎማትነት ሃገራቸውን ያገለገሉት አምባሳደር እውነቱ ከሰሜኑ ጦርነት በፊት የተጠናከረ የሚመስለው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት በአሁኑ ወቅት መላላት ይታይበታል ይላሉ።
ለዚህም ግንኙነቱ የሁለት መሪዎች ነው ከማለት ባለፈ “ድንገት የተጀመረ ነው” የሚሉት አምባሳደር እውነቱ፣ በሕግ ያልታሰረ መሆኑን እንደ ችግር ያነሳሉ
ዩናይትድ ኪንግደም ለንደን ነዋሪ የሆኑት የምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ተንታኝ አብዱራህማን ሰኢድ አቡ ሓሽም፣ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የነበረው ግንኙነት ጥብቅ መሠረት ላይ ያረፈ አይደለም ይላሉ።
ለዚህም ግንኙነቱ በሁለቱ መሪዎች መካከል ያለ እና “ሁለቱም የሚያገኙትን ጥቅም መሠረት አድርጎ እንደ አመቺነቱ የሚቀጥሉበት ነው” ይላሉ።
እንደ አምባሳደር እውነቱ ከሆነ ደግሞ ማኅበረ ምጣኔ ሃብታዊ ግንኙነት እንዲኖር ከመስማማት ባለፈ፣ የአልጀርስ ስምምነትን በመተግበር በአፍሪካ ቀንድ ዙሪያ አብረው ለመስራት ተስማምተው ነበር። ነገር ግን በአብዛኛዎቹ ተግባራዊ አልተደረጉም።
“በሁለት ሉዓላዊ አገራት መካከል የሚደረግ የማይመስለው እና ድብቅ በነበረው ግንኙነት አማካኝነት በትግራይ ጦርነት ተደጋግፈው ለመሰማራት ያሰቡ ይመስላል” ይላሉ።
የሁለትዮሽ ግንኙነት መጠናከር
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከሃያ ዓመታት በላይ ከሚሆን ጊዜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ሐምሌ 07/2010 ዓ.ም ነበር።
ፕሬዝዳንቱ ተዘግቶ የነበረውን የኤርትራ ኤምባሲ መክፈታቸው በሁለቱ አገራት መካከል ተቋርጦ የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መታደሱን በይፋ ያመላከተ ነበር።
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በአዲስ አበባ ብቻ ሳይታጠር ወደ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ጭምር በመጓዝ የተደረጉ ናቸው።
በተመሳሳይም የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ጉዞ ከአሥመራ ባሻገር ሳዋ በመባል የሚታወቀውን የኤርትራ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ማዕከልን ጨምሮ የተለያዩ የኤርትራ አካባቢዎችን ያካተቱ ነበሩ።
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት እየተጠናከረ ለአስርታት የተቋረጠው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ሲጀመር፣ ተዘግተው የቆዩ የድንበር በሮች ተከፍተው ተለያይተው የቆዩት የአገራቱ ሕዝቦች ለመገናኘት በቅተዋል።
ይህ ወዳጅነት ደግሞ የፌደራሉ መንግሥት ከህወሓት ኃይሎች ጋር ጦርነት ውስጥ ሲገባ የኤርትራ ጦር ድጋፍ ከመስጠት ባሻገር በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ተሰማርቶ የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት ጎን ተሰልፎ እስከ መዋጋት የደረሰ እንደነበረ ይታወቃል።
ይህም የኤርትራ መንግሥት ድጋፍ ከዓለም አቀፍ ተቋማት በኩል ከፍተኛ ወቀሳን ያስከተለ ሆኖ ቆይቷል። በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለሠራዊታቸው ከኤርትራ ለተደረገው ድጋፍ በምክር ቤት በይፋ ዕውቅ በመስጠት ማመስገናቸው ይታወሳል።
ደም አፋሳሹ የእርስ በርስ ጦርነትን ያበቃው የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ከኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት ውጪ የሆኑ ኃይሎች ከትግራይ እንዲወጡ መወሰኑን ተከትሎ የኤርትራ ወታደሮች ከበርካታ ቦታዎች መውጣታቸው ተዘግቧል።
ነገር ግን አሁንም የኤርትራ ሠራዊት አባላት በአንዳንድ የትግራይ አካባቢዎች እንዳሉ በትግራይ አስተዳደር በኩል ይነገራል።
ሲጀመር የተሟሟቀ የነበረው የሁለቱ አገራት መሪዎች ግንኙነት፣ በተለይም ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በኋላ እየተቀዛቀዘ ይመስላል።

የፎቶው ባለመብት, pm office
የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ስጋት
በሁለቱ አገራት መካል ያሉ አንዳንድ ልዩነቶች ዋል አደር ያሉ መሆናቸውን የሚጠቅሱት አቡ ሐሽም፣ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከጦርነቱ በፊት በኢትዮጵያ ጉዳይ የማይስማሙበት ጉዳይ እንዳላቸው በግልጽ አስቀምጠዋል ይላሉ።
ለዚህም በኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ተግባራዊ የተደረገው ማንነትን መሠረት ያደረገ የፌዴራል ሥርዓትን በይፋ መተቸታቸውን ያስታውሳሉ።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከዓመት በፊት ለአገራቸው ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ፣ በኢትዮጵያ ለሚስተዋለው ፖለቲካዊ ችግር ምንጩ በህወሓት ተግባራዊ የሆነው ብሔር ላይ ያተኮረ ፖለቲካ መሆኑን ገልጸው ነበር።
አክለውም በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት በተለያዩ ክልሎች ውስጥ የተጠመዱና ጊዜ እየጠበቁ የሚፈነዱ ቦንቦች በመሆናቸው አገሪቱን ወደ ግጭት እና መበታተን የሚወስድ ነው በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ይህም ሁኔታ መዘዙ ከኢትዮጵያ ባሻገር ኤርትራን ጨምሮ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢን ሊያቃውስ ይችላል የሚል ስጋት ሳይፈጥርባቸው ቀረ አይመስልም።
አገራቸውም ይህንን መራር ተሞክሮ በብሪታኒያ ወታደራዊ አስተዳደር እና በትጥቅ ትግሉ ጅማሬ ወቅት ከነበረው ክፍፍል ትምህርት እንደወሰደችበትም አመልክተዋል።
አቡ ሐሽምም በዋናነት የኢሳያስ ስጋት የሆነውን ይህ ፖለቲካዊ አወቃቀር በሁለቱ አገራት መሪዎች መካከል ልዩነት መፍጠሩ አይቀርም ይላሉ።
በትግራይ ውስጥ በተካሄደው ጦርነት የመጀመሪያ ወራት ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከመቀለ እና ከተለያዩ ትግራይ አካባቢዎች ለቆ መውጣቱ “ያልጠበቅነው እና ድንገተኛ ነበር” ሲሉ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ መናገራቸው ይታወሳል።
ይህም ሠራዊታቸውን በአንድ ላይ አሰማርተው በነበሩት ሁለቱ አገራት መካከል አንዳች አይነት ክፍተት ተፈጥሮ እንደነበር እንደማሳያ ጠቅሰዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማሳሰቢያ
በትግራይ ሲካሄድ ከነበረው ጦርነት ጋር በተያያዘ ከባድ ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ የገጠማት ኢትዮጵያ፣ ድጋፍ እና ብድር ይሰጧት የነበሩት ምዕራባውያንም እጃቸውን ከመሰብሰባቸው በተጨማሪ የተለያዩ ጫናዎች ሲያደርጉባት ነበር።
ይህንንም ለመስተካከል ደም አፋሳሹ ጦርነት እንዲቆም እና ሠላም እንዲወርድ የኢትዮጵያ መንግሥት ከህወሓት ጋር ለድርድር መቀመጥ የግድ ነበረበት።
ከዚህ አንጻር ለዘመናት ከምዕራባውያን ጋር ያላት ግንኙነት ቀዝቃዛ የሆነው ኤርትራ ከሚሰነዘርባት ውግዘት ባሻገር ጫናው የጎላ አልነበረም።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ያሉበት ሁኔታ የተለያየ መሆኑን የሚጠቅሱት አቡ ሐሽም፣ “በዐቢይ ላይ ያለው ጫና ቀላል አይደለም። የኢኮኖሚ ማዕቀብ ከተጣለበት [ከኤርትራ ጋር ሲነጻጸር] በኢትዮጵያ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ነው የሚሆነው” ይላሉ።
“በዚህም ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቀላሉ ሊንበረከኩ እንደሚችሉ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ስለሚገባቸው ፕላን ቢ (ሁለተኛ ዕቅድ) ማሰባቸው አይቀርም” በማለት ሊመጣ ለሚችለው ሁኔታ መዘጋጀታቸው እንደማይቀር አመልክተዋል።
በትግራይ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት ቆሞ ስምምነቱ ተግባራዊ መደረግ ሲጀምር በኤርትራ እና በኢትዮጵያ ግንኙነት ላይ ተጽዕኖ ይኖረው ይሆን የሚል ጥያቄ ይነሳል።
ምክንያቱ ደግሞ ኤርትራ በጦርነቱ ከመሳተፏ በላይ ወታደሮቿ ከትግራይ ክልል እንዲወጡ አገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በተደጋጋሚ መጠየቃቸው ነው።
የፕሪቶሪያው ስምምነት “ኤርትራን አላስደሰተም” የሚሉት አምባሳደር እውነቱ፣ “ኤርትራ ሠላም እንዲወርድ ሲሠሩ የነበሩ ዓለም አቀፍ አደራዳሪዎችንም ስትተች ነበር” ይላሉ።
“በግልጽ ግን እንዳልተደሰቱ እና እንደተቆጡ አይናገሩም። ኤርትራን ያስቆጣበት ምክንያት በኋላ ተጠያቂነት እንደሚመጣ ስለሚያውቁ ነው” ብለዋል አምባሳደር እውነቱ።
አክለውም በስምምነቱ “የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ እንዲወጣ ያዛል፤ ነገር ግን አስካሁን ሙሉ ለሙሉ አልወጣም። ይህም ስምምነቱን ለማደናቀፍ የሚደረግ ነው” ብለዋል።
የኤርትራ ወታደሮች ትግራይ ውስጥ አሉ የሚባለው ጉዳይ ለፌዴራል መንግሥቱ ቢተው ይሻላል የሚሉት አቡ ሓሽም ደግሞ “ከዚያ ውጪ የሠላም ሂደቱ በቀላሉ ሊጎዳ ይችላል። በፌዴራል መንግሥቱ ላይ ጫና በመፍጠር መፍትሄ የሚገኝበትን መንገድ መፈለግ ያስፈልጋል።”
ከዚህ ከኢትዮጵያ እና ከኤርትራ ግንኙነት ጋር በተያያዘ በርካታ መላ ምቶች ባለፉት ወራት ሲነገሩ የቆዩ ሲሆን፣ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሚያዚያ 23/2015 ዓ.ም. በሀላላ ኬላ መዝናኛ ማዕከል የተናገሩት ደግሞ ከዚህ ትኩረትን ስቦ መነጋጋሪያ ሆኖ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራ ክልል የተከሰተውን ውጥረት ተከትሎ “…በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ እየገቡ መፈትፈት የሚፈልጉ ኃይሎች፣ በተለይም ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ለማሳሰብ እወዳለሁ።
“…የእኛን ጉዳይ ለእኛ ትተው፣ በርከት ያለ ያልሠሩት ጉዳይ ስላላቸው፣ ሥራዎቻቸውን በምድራቸው ላይ መሥራት እንዲችሉ፣ የእኛን ጉዳይ ለእኛ እንዲተዉ ማሳሰብ እፈልጋለሁ….” ብለው ነበር።
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የተሰነዘረው ለማን እንደሆነ ግልጽ ባለመሆኑ ለቀናት የማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ዋነኛ መነጋገሪያ ሆኖ የተለያዩ ግምቶችን ሲያሰነዝር ነበር።
እንደ አቡ ሐሽም ዕይታ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር “ግብፅን መጠርጠር ቢቻልም ግን አይሆንም። ሱዳን አሁን ካለችበት ሁኔታ አንጻር የማይመስል ነገር ነው። ጉዳዩ ኤርትራ የሚመለከት ነው ሊሆን የሚችለው። ስለዚህ ከሦስቱ አገራት በተለይ ኤርትራን የሚመለከት ይመስለኛል” ይላሉ።
አምባሳደር እውነቱም ይህንን ሃሳብ ይጋሩታል፤ ኤርትራ በቀጠናው እና በተለይ በኢትዮጵያ ላይ ካላት ፍላጎት የተነሳ “ዐቢይ ይህንን ያሉት ስለኤርትራ ከሆነ የተሳሳተ ሳይሆን ትክክለኛ ነው” በማለት፣ ኢሳያስ በኢትዮጵያ ያለው ችግር “እንዲወሳሰብ አድርገዋል” ብለዋል።
ቀጣይ ግንኙነት እና ስጋቶች
ለሁለት ዓመት የተካሄደው ጦርነት በህወሓት ላይ ከባድ ጉዳትን አድርሶ ወታደራዊ አቅሙ ቢዳከምም ሙሉ ለሙሉ አልጠፋም የሚሉት አቡ ሓሽም፣ ቡድኑ አሁንም ፖለቲካዊ እና የውጭ ግንኙነት አቅሙ ጠንካራ እንደሆነ ያምናሉ።
“በዲፕሎማሲ ዐይን ከታየም ባለፉት ጊዜያት ህወሓት ከሁለቱም (ከአዲስ አበባ እና አሥመራ) የተሻለ መሥራት ችሏል። ስለዚህም በህወሓት እና በአዲስ አበባ መካከል ያለው ግንኙነት ሲጠናክር፤ በአሥመራ እና በአዲስ አበባ መካከል ያለው ግንኙነት መቀዛቀዙ ግድ ነው።”
የኢትዮጵያን መንግሥት እየገጠመው ያለው ችግር በትግራይ ብቻ ሳይወሰን በአማራ እና በኦሮሚያ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ጭምር በመሆኑ ሌላ ሥራ እንደሚጠብቀው ያመለከቱት አቡ ሓሽም፣ “ኤርትራ ይህንን የምታባብስ ከሆነ ፌደራሉን መንግሥት ሊያስደስተው አይችልም” ይላሉ።
ከዚህ አንጻር የፕሬዝዳንት ኢሳያስ እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ግንኙነት ንፋስ ከገባው እና ኤርትራ ደስተኛ ካልሆነች፣ ከህወሓት ጋር እንደነበረው “ሌላ አማራጭ የመፈለግ” አዝማሚያ ሊኖር ይችላል። ይህም ማለት “ከሌሎች አካላት ወይም ቡድኖች ጋር ግንኙነት ወደ መፍጠር ሊሄዱ ይችላሉ” ሲሉ ያክላሉ።
በእርግጥ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት በዚህ ወቅት ነፋስ ከገባው “ሁለቱ መሪዎች ለጦርነት ተደጋግፈው ለሠላም እና ለእርቅ ተለያዩ ማለት ይቻላል” የሚሉት አምባሳደር እውነቱ በግንኙነቱ ሐቀኝነት ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው በመግለጽ ሁለቱ አገራት ወደ ዳግም ጦርነት እንዳይገቡ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ወደ ሌላ የጦርነት አዙሪት እንደማይገባ ተስፋ የሚያደርጉት አቡ ሓሽም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መልዕክት ለማንም ይሁን ለማን በአሥመራ በኩል በቀናነት ሊወሰድ የሚገባው መሆኑን ያነሳሉ።












