የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ተወካዮች ጋር ሊወያዩ ነው

የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር

የፎቶው ባለመብት, Event Brite

የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር በሎስ አንጀለስ፣ ካሊፎርኒያ ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ተወካዮች ጋር ሊወያዩ መሆኑን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታወቀ።

አምባሳደር ማይክ ሐመር ለዘጠኝ ቀናት ያህል በሎስ አንጀለስ በሚያደርጉት ቆይታም ከአማራ፣ ከኦሮሞ፣ ከትግራይ፣ ሶማሊ ማኅበረሰብ የተውጣጡ ተወካዮችን አግኝተው እንደሚወያዩ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ረቡዕ ግንቦት 02/ 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ልዩ መልዕክተኛው በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተዛመተውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላም ለመቋጨት ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ በፕሪቶሪያ የተደረሰውን ዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነትን ጨምሮ በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ።

በተጨማሪም አምባሳደሩ ከቀጠናው የተውጣጡ የሴቶች መሪዎች ጥምረት ‘ዩናይትድ ዊሜን ኦፍ ዘ ሆርን’ በተባለው የሲቪክ ድርጅት አዘጋጅነት በአሜሪካ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት ጋርም ውይይት ያደርጋሉ።

ቦብ ሆፕ ፓትሪዮቲክ አዳራሽ ላይ በሚካሄደው ውይይትም “ሰላምን በማስፈን እና የሴቶችን አቅም በማጎልበት” ላይ እንደሚያተኩር ከአሜሪካ ከውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የወጣም መረጃ ያሳያል።

የአፍሪካ ቀንድ የሴቶች ጥምረት (ዩናይትድ ዊሜን ኦፍ ዘ ሆርን) የአፍሪካ ቀንድ ሰላም፣ ፍትህ እና አንድነት የሰፈነበት እንዲሆን የሚሰራ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ዝግጅቶችን አድርጓል።

ተቋሙ ሴቶች በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ ላይ በሰላም ግንባታ ላይ ስለሚኖራቸው ሚና አምባሳደር ማይክ ሐመርና ዶክተር አኔት ዌበር የተሳተፉበት ውይይት መስከረም ማገባደጃ ላይ አካሂዶ ነበር።

በዚህም ውይይት ላይ ከኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ የተውጣጡ ጋዜጠኞችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በዋነኝነት የተሳተፉበት ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ መንግሥት ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ማይክ ሐመር በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ የነበረው ጦርነት እንዲያበቃ ጉልህ ሚና ከተጫወቱ ግለሰቦች መካከል እንደሆኑ ይታወቃል።

በትግራይ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ አሜሪካ ከመደበቻቸው ልዩ መልዕክተኞች መካከል ሦስተኛው የሆኑት አምባሳደር ሐመር በጦርነት ውስጥ የነበሩትን ተፋላሚ ወገኖች በማቀራረብ እና በአፍሪካ ኅብረት መሪነት በተካሄደው ድርድር ውስጥ አገራቸውን በመወከል ዋነኛ ተሳታፊ ነበሩ።

አምባሳደር ማይክ ሐመር ጦርነቱ በሰላም እንዲቋጭ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት በተዘጋጀው የሽልማት እና የእውቅና ዝግጅትም ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ሽልማት እንደተበረከተላቸው ይታወሳል።

ልዩ መልዕክተኛው ማይክ ሐመር ከሰላም ድርድሩ በፊት ከኢትዮጵያና ከህወሃት ባለስልጣናት ጋር በተደጋጋሚ ውይይቶችን ያደረጉ ሲሆን ሸልማት ከተበረከተላቸውም በኋላም ወደ መቀለ አቅንተው ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።

ግጭት የማቆም ስምምነቱ ከተፈረመ ስድስት ወራት በኋላ ልዩ መልዕክተኛው በአገራቸው ካሉ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላት ጋር በይፋ ሲነጋገሩ ይህ የመጀመሪያው ነው።

የሰሜን ኢትዮጵያን የርስ በርስ ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እንዲቋጭ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የምሥጋና እና የዕውቅና ሥነ ሥርዓት የተካሄደው ሚያዝያ 15/2015 መሆኑ ይታወሳል።

በአዲስ አበባ የወዳጅነት አደባባይ በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሐማት፣ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ፣ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር፣ የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶች እና የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮች ተገኝተዋል።

“ጦርነት ይብቃ፤ ሰላም እናጽና” በሚል መሪ ሐሳብ በተዘጋጀው ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ በመሆን የፌደራል መንግሥቱን እና ህወሓትን በዋናነት ያደራደሩት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ለተፈጠረው ሰላም በተለይ የሁለቱን ወገኖች አመራሮችን አመስግነዋል።