በቱርክ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሸናፊውን ለመለየት ሁለተኛ ዙር ድምጽ ሊሰጥ ይችላል

የፎቶው ባለመብት, YAVUZ OZDEN VIA GETTY IMAGES
በተጠባቂው የቱርክ ምርጫ ሁለቱም ዕጩዎች አሸናፊ የሚያደርጋቸውን የመራጮች ድምጽ እንዳገኙ እየገለጹ ቢሆንም፣ አሸናፊውን ለመለየት ወደ ሁለተኛ ዙር ድምጽ መስጠት ሊያመሩ ይችላሉ።
ለ20 ዓመታት በሥልጣን የቆዩት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን በፓርቲያቸው ዋና ጽሕፈት ቤት ተገኝተው ተጨማሪ አምስት ዓመት ለመምራት የሚያስችላቸው ድምጽ እንዳገኙ እርግጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ተቀናቃኛቸው ከማል ኪሊዳሮግሉ ምርጫውን ሊያሸንፉ እንደሚችሉ የሚጠቁሙ ምልክቶችም ታይተው ነበር።
ሆኖም ግን የመጀመሪያው ዙር ሲጠናቀቅ ያልተቆጠሩ ድምጾች በመገኘታቸው ከኤርዶዋን በታች ሆነዋል።
የኤርዶዋን ጥምረት በምክር ቤት ከፍተኛውን መቀመጫ ሊያገኝም ይችላል።
የቱርክ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለወራት ያህል ባደረጉት ንቅናቄ የኤርዶዋን የሥልጣን ዘመን እንዲያከትም ሲጥሩ ቆይተዋል።
እአአ በ2016 የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ከተካሄደ በኋላ ኤርዶዋን ሥልጣናቸውን እያራዘሙ እዚህ ደርሰዋል።
ምርጫውን የምዕራቡ ዓለምም በቅርበት እየተከታተለው ነው።
የኤርዶዋን ተቀናቃኝ ከማል ኪሊዳሮግሉ የቱርክን ዴሞክራሲ ለማደስ ቃል ገብተዋል። ቱርክ ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት እንደሚያስተካክሉም ገልጸዋል።
እስልምናን መሠረት አድርጎ የተቋቋመው የኤርዶዋን አስተዳደር ምዕራባውያን ኤርዶዋንን ከሥልጣን ለማንሳት እንዳሴሩ ይከሳል።
ተቀናቃኙ ዛሬ ሰኞ ንጋት ላይ በፓርቲያቸው ዋና ጽሕፈት ቤት ተገኝተዋል። ደጋፊዎቻቸው በቦታው ቢገኙም ተቀናቃኙ ግን ከዚህ ቀደም የታየባቸው በራስ መተማመን ዛሬ አልተስተዋለም።
“ሕዝባችን ሁለተኛ ዙር ድምጽ ይሰጥ ካለን ሁለተኛውንም ዙር በእርግጠኛነት እናሸንፋለን” ብለዋል።
ደጋፊዎቻቸው “ሁሉም ጥሩ ይሆናል” ሲሉ ከመፈክሮቻቸው አንዱን ሲያሰሙ ነበር።
የቱርክ አስተዳደር “የሕቡን ፈቃድ ለመጣስ” እየሞከረ ነው ሲሉ ከዚህ ቀደም ከሰዋል።
በፓርቲው አዲስ ድምጽ እየሆኑ የመጡት የኢስታንቡል እና አንካራ ከንቲባዎች እንዳሉት፣ የኤርዶዋን አስተዳደር ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ መንገድ ይጠቀም ነበር።
ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ድምጽ መስጫ ኮሮጆዎችን ሲጠብቁ በመቆያተቸው ከንቲባዎቹ አመስግነዋል።

የፎቶው ባለመብት, ANADOLU AGENCY
ተቀናቃኙ ፖለቲከኛ 74 ዓመታቸው ሲሆን ሪፐብሊካን ፒፕልስ ፓርቲ የተባለው ፓርቲያቸው መሪ ለመሆን በተደጋጋሚ ምርጫ ቢወዳደሩም አልተሳካላቸውም።
በዚህኛው ምርጫ ዙር ግን የኤርዶዋንን አስተዳደር ለመርታት ባቀረቡት ምክረ ሐሳብ ተቀባይነት አግኝተዋል።
ቱርካውያን 44% የደረሰውን የዋጋ ንረት ሲያማርሩ ነበር። ትችት የበዛበት የኤርዶዋን የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ ነገሩን እንዳባባሰው ይገለጻል።
ከወራት በፊት በ11 ግዛቶች በተነሳውና ከ50 ሺህ በላይ ሰዎችን በገደለው የመሬት መንቀጥቀት የኤርዶዋን መንግሥት የሰጠው ምላሽ የዘገመ ነበር ብለው የሚተቹም አልታጡም።
ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ግን የኤርዶዋን ፓርቲ አብላጫውን ድምጽ ያገኘ ይመስላል።
ኤርዶዋን “የምርጫው የመጨረሻ ውጤት ባይታወቅም መሪነቱን ይዘናል” ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል።
ምናልባት ከሁለት ሳምንት በኋላ በድጋሚ ድምጽ ሲሰጥ ምን ደረጃ እንደሚይዙ ግልጽ አይደለም።
የኤርዶዋን አካሄድ ተቀናቃኛቸው ሁለተኛ ዙር ድምጽ ሳይሰጥም ሊያሸንፉ ይችላሉ ብለው አስተያየት ከሰጡ ሰዎች በተቃራኒው ይመስላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ምክር ቤት አብላጫውን መቀመጫ ሊያገኙም እንደሚችሉም ያልተረጋገጡ የምርጫ ውጤቶችን መነሻ አድርጎ የተሠራ የአናዶሉ ትንታኔ ይጠቁማል።
የኤርዶዋን ደጋፊዎች ተቀናቃኙ ከማል ኪሊዳሮግሉ የቱርክ 13ኛው ፕሬዝዳንት ሊሆኑ ይችላሉ መባሉ አልተዋጠላቸውም።
ይህ ምርጫ የቱርክ ሕዝብ ምን ያህል በአቋም እንደተራራቀ አሳይቷል።
ዘመናዊቷ የቱርክ ሪፐብሊክ በከማል አታቱርክ ከተመሠረተች 100 ዓመታት ተቆጥረዋል።
ምርጫ ከመጀመሩ በፊት ከማል ኪሊዳሮግሉ በአንካራ የአታቱርክ መታሰቢያ ሲገኙ፣ ኤርዶዋን ደግሞ ከወግ አጥባቂና ብሔርተኛ ደጋፊዎቻቸው ጊዜውን ማሳለፍ መርጠዋል።
አቋማቸውን ለመግለጽ የመረጡት ቦታ ደግሞ ኢስታንቡል የሚገኘው ሀጊያ ሶፊያ መስጊድን ነው። ይህ ስፍራ በአታቱርክ ዘመን ከኦርቶዶክስ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያንነት ወደ ሙዝየም የተቀየረ ሲሆን በ2020 ኤርዶዋን መስጊድ አድርገውታል።
ለሁለተኛ ጊዜ ድምጽ ለመስጠት ምን ያህል ቅርብ እንደሆነ ገና ግልጽ አይደለም።
በምርጫው 5% ድምጽ የተሰጠው ለአክራሪ ብሔርተኛው ተወዳዳሪ ሲናን ኦጋን ሲሆን፣ ይህ ድምጽ ወደየት እንደሚያመራም አልታወቀም።
ሁለቱ ዋነኛ ተፎካካሪዎች ይህንን ድምጽ ለመጠቅለል እንደሚሞክሩ በመረዳት ቅርመ ሁኔታዎች አስቀምጠዋል።
ከተፎካካሪዎቹ አንዱን ለመደገፍ ቢወስኑ እንኳን በመጀመሪያ ዙር ድምጻቸውን የሰጡ ቱርካውያን ይህንን ስለማድረጋቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም።












