የቬንዙዌላ ጊዜያዊ መሪ የማዱሮ ጥበቃ ቡድን ኃላፊ የነበሩትን ጄነራል አባረሩ

ጄኔራል ሀቪዬር ማርካኖ

የፎቶው ባለመብት, REDI

የምስሉ መግለጫ, ጄነራሉ የፕሬዝደንቱ ጥበቃ ቡድንን ከመምራታቸው በተጨማሪ የወታደሩ የስለላ ክፍል ኃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል

የቬንዙዌላ ጊዜያዊ መሪ የፕሬዝደንት ኒኮላስ ማዱሮ ጥበቃ ቡድን አዛዥ የነበሩት ጄነራል ሃቪዬር ማርካኖን ከሥልጣን አባረሩ።

ጄነራሉ ከሥልጣን የተባረሩት ኒኮላስ ማዱሮ በአሜሪካ ኃይሎች ከካራካስ ተወስደው ኒው ዮርክ በሚገኝ ፍርድ ቤት ከቀረቡ ከቀናት በኋላ ነው።

የፕሬዝደንቱ የጥበቃ ቡድን የወታደሩ ክንፍ ሲሆን የሀገሪቱን መሪ የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት።

የቬንዙዌላ መንግሥት በአሜሪካ ጥቃት ምክንያት የደረሰውን አደጋ እስካሁን ይፋ ባያደርግም ዩናይትድ ስቴትስ ማዱሮን ለመያዝ ባደረገችው ዘመቻ ምክንያት ከተገደሉ በጅምላ የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል የጥበቃ ቡድኑ አባላት እንደሚገኙበት ይታመናል።

ጄነራል ማርካኖ ታባታ ተነስተው በሌላ ግለሰብ እንዲተኩ ትዕዛዝ ያስተላለፉት የቬንዙዌላ ጊዜያዊ ፕሬዝደንት ዴልሲ ሮድሪጌዝ ናቸው።

ሮድሪጌዝ ባለፈው ሰኞ ለመንግሥት ታማኝ የሆኑ ሰዎች በሞሉት ብሔራዊ ጉባዔ ፊት ቀርበው ቃለ-መሐላ ፈፅመው ጊዜያዊ ፕሬዝደንት ተደርገው ተመርጠዋል።

የማዱሮ ምክትል ሆነው ያገለግሉ የነበሩት ሮድሪጌዝ አሁን በእስር ላይ የሚገኙት ፕሬዝደንት የቅርብ ወዳጅ እንደሆኑ ይነገራል።

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የማዱሮን መያዝ አስከትሎ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሀገራቸው ቬንዙዌላን እንደምታስዳድር ገልፀው ከሮድሪጌዝ ጋር ግንኙነት እያደረጉ እንደሆነ አስታውቀዋል።

አክለው ሮድሪጌዝ የአሜሪካን ፍላጎት የማታሟላ ከሆነ "ከማዱሮ የባሰ ዕጣ ይገጥማታል" ሲሉ መዛታቸው ይታወሳል።

ትራምፕ ማክሰኞ ቬንዙዌላ "50 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ለአሜሪካ ታስረክባለች" ቢሉም የቬንዙዌላ መንግሥት እስካሁን ያለው ነገር የለም።

በዓለማችን ግዙፉ የነዳጅ ክምችት ያላት ሀገር ጊዜያዊ ፕሬዝደንት ሆነው የተመረጡት ዴልሲ ሮድሪጌዝ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ አንድ ጊዜ የትራምፕን መንግሥት ሲያጣጥሉ ሌላ ጊዜ ደግሞ እንደሚተባበሩ ሲገልፁ ተሰምተዋል።

የማዱሮን መያዝ "ሕጋዊ ያልሆነ አፈና" ሲሉ የገለፁት ፕሬዝደንቷ "መንግሥታችን ከአሜሪካ መንግሥት ጋር ተባብሮ እንዲሠራ ጥሪ እናቀርባለን" ብለዋል።

ጄነራል ማርካኖ ከማዱሮ አገዛዝ የቅርብ ሰዎች ከሥልጣን የተባረሩ የመጀመሪያው ሰው ሆነዋል።

ጄነራሉ የፕሬዝደንቱ ጥበቃ ቡድንን ከመምራታቸው በተጨማሪ የማዱሮ ተቃዋሚ የሆኑ ድምፆችን ያፍናል ተብሎ የሚወቀሰው የወታደሩ የስለላ ክፍል ኃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው ይህ የወታደሩ የስለላ ክፍል "በማሰቃየት፣ በወሲባዊ ጥቃት እና በሌሎች ክብር በሚነሱ ኢ-ሰብዓዊና ጭካኔ የተሞላባቸው ድርጊቶች" ይወቀሳል።

የቬንዙዌላ የስለላ ድርጅት ኃላፊ ጉስታቮ ጎንዛሌዝ ሲሆኑ ካራካስ የሚገኘው እና እጅግ አደገኛ ከሚባሉ እስር ቤቶች አንዱ የሆነውን ሄሊኮይድ የሚያስተዳድር ነው።