እስራኤል በደቡብ አፍሪካ ያሉትን አምባሳደሯን ‘ለምክክር’ ጠራች

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ከተካሄዱ ፍልስጤማውያንን ከሚደግፉ ሰልፎች በአንዱ ላይ የተሳተፉ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ደቡብ አፍሪካ እስራኤል በጋዛ ላይ የምታካሂደውን ወታደራዊ ዘመቻ አጥብቃ ከመቃወሟ በተጨማሪ በአገሪቱ ፍልስጤማውያንን የሚደግፉ በርካታ ሰልፎች ተካሂደዋል

እስራኤል በጋዛ ላይ እያካሄድ ባለው ወታደራዊ ዘመቻ ላይ ጠንካራ ተቃውሞዋን እያሰማች ባለችው ደቡብ አፍሪካ የሚገኙ አምባሳደሯን መጥራቷን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

እስራኤል የየውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ አምባሳደሩ የተጠሩት “ለምክክር ነው” ብሏል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ሊዮር ሃይታ በኤክስ ገጻቸው ላይ አምባሳደሩ ወደ ቴል አቪቭ የሚመለሱት “የደቡብ አፍሪካን የቅርብ ጊዜ መግለጫ ተከትሎ ነው” በማለት ዝርዝር ሳይሰጡ አስተያየታቸውን አስፍረዋል።

ደቡብ አፍሪካ እስራኤል በጋዛ እያከናወነች ያለውን ወታደራዊ ዘመቻ አጥበቀው ከሚተቹ ቀዳሚ አገራት መካከል አንዷ ነች።

ደቡብ አፍሪካ ትናንት ሰኞ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ላይ የእስር ትዕዛዝ እንዲያወጣ መጠየቋ ይታወቃል።

ከሁምቡዝዶ ናትሻቨሄኒ የተባሉ የደቡብ አፍሪካ ሚኒስትር ፍርድ ቤቱ በተቀመጠው ቀነ ገደብ ውስጥ ኔታኒያሁ ላይ የእስር ትዕዛዝ የማይቆረጥ ከሆነ “ዓለም አቀፋዊ የአስተዳደር ውድቀት መኖሩን ያመላክታል” ብለዋል።

የእስራኤል አምባሳደር ኤሊአቭ ቤሎትሴርኮቫስኪ ወደ ቴል አቪቭ የመጠራቻቸው ዜና የተሰማው ደቡብ አፍሪካ ቻይና፣ ሩሲያ እና ኢትዮጵያን ጨምር በአባልነት የያዘው የብሪክስ አገራት በእስራኤል-ሐማስ ጦርነት ዙሪያ ስብሰባ ለማስናዳት በዝግጅት ላይ እያለች ነው።

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ የሚመሩት ስብሰባ ውጤት አባል አገራት በእስራኤል-ሐማስ ጦርነት ላይ ተመሳሳይ አቋም እንዲይዙ ለማድረግ ያለመ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከዚህ በተጨማሪም የደቡብ አፍሪካ ፓርላማ ዛሬ ማክሰኞ በሚኖረው ስብሰባ እስራኤል የተኩስ አቁም ለማድረግ እስክትስማማ ድረስ የእስራኤል ኤምባሲን ስለመዝጋት እና ሁሉንም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን በማቋረጥ ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።

እስራኤል መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በሐማስ የተፈጸመባትን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ በጋዛ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሯ ይታወሳል።

በዚህ ሁለት ወር ሊደፍነው እየተቃረበው ጦርነት በእስራኤል በኩል 1200 ሰዎች ተገድለው 240 ሰዎች የታገቱ ሲሆን፣ በጋዛ ደግሞ በሐማስ የሚተዳደረው ጤና ሚንስቴር በእስራኤል ጥቃት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከ13ሺህ በላይ መሆኑን አስታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት እና ተቋማቱ ጋዛ ውስጥ የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ እንዲቻላቸው ለሰብዓዊነት ሲባል የተኩስ ፋታ እንዲደረግ ሲወተውቱ ቆይተዋል።

ለፍልስጤማውያን ያላትን ድጋፍ ጠንከር ባሉ አቋማ ስታንጸባርቅ የቆየችው ደቡብ አፍሪካ የእስራኤልን የጋዛ ዘመቻ “የጅምላ ቅጣት” ስትል ትተቻለች።

እስራኤል በበኩሏ ይህን ወታደራዊ እርምጃ እየወሰደች ያለችው እራሷን የመከላከል መብቷን በመጠቀም መሆኑን እና የዘመቻው ዓላማም ሐማስን በመደምሰስ ተመሳሳይ ጥቃት በእስራኤል ምድር ዳግም እንዳይፈጸም ነው ትላለች።

ከጥቂት ቀናት በፊት ደቡብ አፍሪካ፣ ባንግላዴሽ፣ ቦሊቪያ፣ ኮሞሮስ እና ጂቡቲ እስራኤል ጋዛ ውስጥ የምትፈጽመውን እርምጃ የጦር ወንጀለ እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ስለመሆኑ ምርመራ እንዲደረግበት ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ወስደውታል።

በተጨማሪም ደቡብ አፍሪካ ዲፕሎማቶቿን ከእስራኤል የጠራች ሲሆን፣ ደቡብ አፍሪካዊቷ አገር በእስራኤል ለአምስት ዓመታት ያክል አምባሳደር ኖሯት አያውቅም።