ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ኔታንያሁ ላይ የእስር ትዕዛዝ እንዲያወጣ ደቡብ አፍሪካ ጠየቀች

ደቡብ አፍሪካ ለረዥም ዓመታት ከፍልስጤም ጎን መሆኗን አሳይታለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ላይ የእስር ትዕዛዝ እንዲያወጣ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ጠየቀ።

እስራኤልን የጦር ወንጀል ፈጽሟል በማለት እየከሰሰች ያለችው ደቡብ አፍሪካ እስከ ታህሳስ አጋማሽ ድረስም ትዕዛዙ መውጣት አለበት ብላለች።

የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ሚንስትር ኩምቡድዞ ሳቬኒ እንዳሉት ፍርድ ቤቱ ይህንን ማድረግ ካልቻለ የዓለምአቀፉ አስተዳደር "ጠቅላላ ውድቀት" ምልክት ይሆናል ብለዋል።

“ዓለም ዳር ቆሞ ዝም ብሎ አይመለከትም” ሲሉ አክለዋል።

ሐማስ መሰከረም 26 በፈጸመው ጥቃት 1 ሺህ 200 ሰዎች ሲገደሉ፣ 200 ሰዎች ታግተዋል።

እስራኤል ራሷን የመከላከል ምላሽ ነው ባለችው የማያባራ የአየር ጥቃት ከ13 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ሲገደሉ ከነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ ህጻናት እና ሴቶች መሆናቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በግዳጅ እንደተፈናቀሉ የተገለጸባት ጋዛ እስራኤል በከበባ ውስጥ አስገብታ መብራት፣ ውሃ እና ነዳጅ እንዲቋረጥባት አድርጋባታለች።

እስራኤል የሲቪሎችን ሞት ለመቀነስ እንደምትጥር አስታውቃለች። ሳቬኒ ግን የእስራኤል መንግሥት “በጋዛ ያሉ ፍልስጤማዊያን በማጽዳት አካባቢውን ሊቆጣጠር” እየሞከረ ነው ብለዋል።

ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ ባንግላዴሽ፣ ቦሊቪያ፣ ኮሞሮስ እና ጅቡቲ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በጋዛ የጦር ወንጀል እና በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ስለመፈጸሙ እንዲመረምር ጥያቄ አቀርበዋል።

ደቡብ አፍሪካ ለረዥም ዓመታት ከፍልስጤም ጎን በመቆም እንዲሁም ድምጽ በመሆን ቀጥላለች።

አገሪቱ በእስራኤል ያላትን ዲፕሎማቶች ያስወጣች ሲሆን ፕሪቶሪያ የሚገኘው የእስራኤል አምባሳደር ኃላፊነት “መቀጠል የማይቻል” እየሆነ መምጣቱንም ጠቁማለች።