የጃፓን ዕቃ ጫኝ መርከብ ቀይ ባሕር ላይ በየመን ሁቲ አማጺያን ታገተ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በኢራን በሚደገፉት የየመን ሁቲ አማጺያን የእስራኤል ነው ያሉትን የጃፓን ግዙፍ የዕቃ ጫኝ መርከብ ቀይ ባሕር ላይ አገቱ።
በጃፓን የሚተዳደረው ጋላክሲ ሊደር የተባለው የተሽከርካሪዎች መጫኛ መርከብ በታጣቂዎቹ መታገቱን ተከትሎ ጃፓን ድርጊቱን በጥብቅ አውግዛለች።
የየመን ታጣቂዎች መርከቡ የእስራኤል እንደሆነ ቢገልጹም፣ የጃፓን መንግሥት ቃል አቀባይ ግን መኪና ጫኙ መርከብ የሚተዳደረው በጃፓኑ የመርከብ ድርጅት ኒፖን ዩስን ነው ብለዋል።
የጃፓን ካቢኔ ዋና ፀሐፊ መርከቡን ለማስለቀቅ እየሠሩ እንደሆነ ተናግረዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው ለዚህ ጠለፋ የሁቲን ታጣቂዎች የምትደግፈውን ኢራንን ተጠያቂ አድርገዋል።
ኔታንያሁ፣ መርከቡም ሆነ የመርከቡ ሠራተኞች እስራኤላውያን አይደሉም በማለት ድርጊቱን ኢራን “በዓለም አቀፍ መርከብ” ላይ የፈፀመችው ጥቃት ነው ብለውታል።
የእንግሊዝ ንብረት ናት ተብሎ በሚታሰበው በዚች መርከብ ላይ 22 ሰዎች ተሳፍረው እንደነበር ይታመናል።
የጃፓን የትራንስፖርት ድርጅት ኒፖን ዩስን እንዳለው ጋላክሲ ሊደር የተባለው ተሽከርካሪ ጫኝ መርከብ በጠላፊዎች የታገተው ወደ ሕንድ እያመራ ባለበት ወቅት በየመን ባሕር ዳርቻ ላይ ነው።
የጃፓን ካቢኔ ዋና ፀሐፊ ሒሮካዙ ማሱኖ መርከቡን እና ሠራተኞቹን ለማስለቀቅ የትራንስፖርት ሚኒስቴርን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች ሚኒስቴሮች እና ተቋማት መረጃዎችን እያሰባሰቡ እንደሆኑ እና ከሚመለከታቸው አገራት ጋር እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመርከቡ ላይ ተሳፍረው ከነበሩት ሰዎች መካከል የቡልጋሪያ እና የፊሊፒን ዜጎች እንደሚገኙበት ይታመናል።
የየመን ሁቲ አማጺያን ጦር ቃል አቀባይ ያህያ አል ሳሬ፣ መርከቡ የእስራኤል እንደሆነና ወደ የመን ወደብ መወሰዱን ገልጸዋል።
ሁቲ ቀደም ብሎ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ እየወሰደች ላለችው እርምጃ የአጸፋ ምላሽ ለመውሰድ የእስራኤል መርከቦችን ኢላማ እንደሚያደርግ ዝቶ ነበር።
እስራኤል የሐማስ ታጣቂዎች ከሁለት ወር ገደማ በፊት በፈፀሙባት ድንገተኛ ጥቃት 1200 ያህል ሰዎች መገደላቸውን እና ከ240 በላይ የሚሆኑት መታገታቸውን ገልጻለች።
ይህንን ተከትሎ እስራኤል ሐማስን ለማጥፋት በጋዛ ላይ በአየር እና በምድር መጠነ ሰፊ ወታደራዊ እርምጃ እያካሄደች ትገኛለች።
በሐማስ የሚተዳደረው ጤና ሚኒስቴር እስራኤል እርምጃውን መውሰድ ከጀመረች አንስቶ በጋዛ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 12 ሺህ 300 ደርሷል። ከ2 ሺህ በላይ ሰዎችም በፍርስራሽ ሥር ሳይቀበሩ እንዳልቀረ ስጋት አለ።
ሁቲዎችም በርካታ ሚሳይሎችንና ድሮኖችን ወደ እስራኤል ተኩሰዋል።
በወቅቱ አሜሪካ ሁሉም ሚሳይሎች እና ድሮኖች በጦር መርከቧ ቀይ ባሕር ላይ ከሽፈዋል ብላ ነበር።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል በመርከቡ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት “በጣም አሳዛኝ ክስተት” ብሎታል።
መከላከያ ኃይሉ እንዳለው መርከቡ የመን አቅራቢያ በቀይ ባሕር ላይ ሲታገት ከቱርክ ወደ ሕንድ እያቀና ነበር።
በቅርቡ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሁሴን አሚር አብዶላሂን፣ ከቴህራን ጋር ግንኙነት ያለው አማጺ ቡድን፣ በእስራኤል እና በደጋፊዎቿ ላይ በጥበብ ጫና ለመፍጠር እየሞከሩ ነው ብለው ነበር።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይም ሁቲዎች በየመን የባሕር ዳርቻ የአሜሪካን ወታደራዊ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) መትተው መጣላቸውን የአሜሪካ ባለሥልጣናት መናገራቸው ይታወሳል።
ሁቲዎች በሳዑዲ አረቢያ ከሚደገፈው ከየመን ይፋዊ መንግሥት ጋር ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ቆይተዋል።












