ኤርትራ በዳህላክ የእስራኤል ወታደራዊ ጣቢያ ላይ ጥቃት ተፈጸመ መባሉን ሐሰት ነው አለች

ዳህላክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዳህላክ ደሴቶች አንድ አካል

በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ መገናኛ ብዙኃን በዳህላክ በሚገኝ የእስራኤል ወታደራዊ የቅኝት ጣቢያ ላይ ጥቃት ተፈጸመበት ሲሉ ያወጡት ዘገባ ሐሰት ነው ስትል ኤርትራ አስተባበለች።

የሊባኖስ ቴሌቪዥን ጣቢያ የሆነው አል ማያዲን፤ ዳህላክ ደሴት ላይ የሚገኝ ነው ያለው የእስራኤል ወታደራዊ የቅኝት ጣቢያ ላይ ጥቃት ተፈጽሟል ሲል የኤርትራ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።

ይሁን እንጂ የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል ዘገበው ፍጹም ሐሰት ነው ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ አስተባብለዋል።

ሚኒስትሩ ዘገባው የሚያትተው በኤርትራ ውስጥ በሌለ የእስራኤል ጦር ሰፈር ላይ ስለተፈጸም ጥቃት ነው በማለት፣ የተፈጸመ ጥቃት ካለመኖሩ በተጨማሪ እስራኤል በምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ውስጥ የጦር ሰፈር እንደሌላት አመልክተዋል።

አል ማያዲን ግን የኤርትራ ሠራዊት ውስጥ የሚገኙ ምንጮቼ ነግረውኛል ብሎ ባወጣው ዘገባ ትናንት ሐሙስ ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም. ተፈጽሟል ባለው ጥቃት አንድ ከፍተኛ የእስራኤል ሠራዊት የጦር መኮንን መገደሉን ጨምሮ አስነብቧል።

አል ማያዲን ጥቃቱ ዒላማ ያደረገው በቀይ ባሕር ላይ ትኩረቱን በየመን ላይ ያደረገ የእስራኤል ቅኝት ማድረጊያ የሚገኝበት ማዕከል ላይ ነው ብሏል።

ይህ መገናኛ ብዙኃን ጥቃቱን ማን እንደፈጸመ ያለው ነገር ባይኖርም በየመን የሚንቀሳቀሰው አንሳር አላህ የተባለው እስላማዊ ቡድን ሊሆን እንደሚችል ግን ጠቁሟል።

የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር ግን ዘገባው “ነጭ ውሸት ነው” ያሉ ሲሆን፣ በተደጋጋሚ እስራኤል፣ ኢራን እንዲሁም የሁቲ አማጺያን በኤርትራ የጦር ሰፈር አላቸው የሚሉ ሐሰተኛ መረጃዎች ሲወጡ ቆይተዋል ብለዋል።

እስራኤል በኤርትራ የጦር ሰፈርም ይሁን የቅኝት ጣቢያ ስለማቋቋሟ በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም።

የእስራኤሉ ሃሬትዝ ጋዜጣ ከ10 ዓመታት በፊት ስትራትፎር ግሎባል ኢንተለጀንስ የተባለን የደኅንነት ጉዳዮች ተንታኝ ተቋምን ጠቀሶ በሰራው ዘገባ እስራኤል እና ኢራን በምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር የጦር ሰፈር አቋቁመዋል ብሎ ነበር።

አሥመራ ግን የእስራኤልም ሆነ የኢራን ወታደራዊ ጣቢያዎች በግዛቷ እንደሌሉ ትገልጻለች።

ከሁለቱ አገራት በተጨማሪ ግብፅ በኤርትራ የጦር ሰፈር ለመገንባት ዕቅድ አላት የሚል ዘገባ ወጥቶ ነበር።

ይሁን እንጂ የቱርክ መንግሥት የዜና ወኪል የሆነው አናዱሉ ከዓመታት በፊት የግብፅ ወታደራዊ ምንጮችን ጠቅሶ ግብፅ በውጭ አገራት የጦር ሰፍር የመገንባት ዕቅድ እንደሌላት አስነብቦ ነበር።

አሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) በበኩሉ የሳተላይት ምስሎችን ዋቢ አድርጎ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች አሰብ ላይ ገንብታው የነበረውን ጦር ሰፈር እያፈረስች እንደሆነ ዘግቦ ነበር።

አቡ ዳቢ ይህን ወታደራዊ ጣቢያ ከሳዑዲ መራሹ ኃይል ጎን በመሰለፍ በየመን የሁቲ አማጺያንን ስትወጋ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን እና በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ ወታደሮችን ለማጓጓዝ ስትጠቀምበት ነበር።