ደቡብ አፍሪካ ሁሉንም ዲፕሎማቶቿን ከእስራኤል ጠራች

ደቡብ አፍሪካ የፍልስጥኤም የነጻነት ትግልን ለረዥም ጊዜ ደግፋለች

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

የምስሉ መግለጫ, ደቡብ አፍሪካ የፍልስጥኤም የነጻነት ትግልን ለረዥም ጊዜ ደግፋለች

ደቡብ አፍሪካ ሁሉም ዲፕሎማቶቿ ከቴል አቪቭ እንዲወጡ አዘዘች።

ደቡብ አፍሪካ ይህን እርምጃ የወሰደችው እስራኤል በጋዛ ላይ መጠነ ሰፊ የአየር ድብደባ ማድረሷን ተከትሎ ነው።

በተለይ እስራኤል ከትናንት በስቲያ እሑድ በጋዛ ላይ ያዘነበችው ቦምብ ጦርነቱ ከተጀመረ ከአንድ ወር ወዲህ ከፍተኛው ነው ተብሏል።

የጋዛ አልሺፋ ሆስፒታል እንዳስታወቀው ወደ 200 ሰዎች በዚህ ጥቃት ተገድለዋል።

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ትናንት ሰኞ ይህን በንጹሐን ላይ የደረሰን ጥቃት በብርቱ የኮነነ ሲሆን ዲፕሎማቶቹ በሙሉ ከቴል አቪቭ ለቀው እንዲወጡ አዟል።

ደቡብ አፍሪካ የፍልስጥኤም ነጻነት ላይ የማያወላዳ አቋም ካላቸው አገራት አንዷ ናት።

የደቡብ አፍሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “አገሬ በፍልስጤም ሕጻናትና ሌሎች ንጹሐን የጅምላ ቅጣት ተረብሻለች። እስራኤል እየወሰደችው ያለው ተመጣጣኝ ያልሆነ ምላሽ በጅምላ ሕዝብን መቅጣት አድርገን ነው የምንረዳው” ብለዋል።

እስራኤል በበኩሏ የንጹሐንን ሞት ለመቀነስ እየጣረች እንደሆነና ሐማስ ግን ንጹሐንን ሰብአዊ ምሽግ አድርጎ እየተጠቀመባቸው እንደሆነ ትከራከራለች።

መስከረም 26 ሐማስ ባደረሰው መብረቃዊ ጥቃት 1ሺህ 400 ሰዎችን በእስራኤል መግደሉን ተከትሎ ነው እስራኤል የአጸፋ እርምጃ መውሰድ የጀመረችው።

ሐማስ በዩኬ፣ አሜሪካ እና ሌሎች የምዕራብ አገራት አሸባሪ ድርጅት በሚል የተፈረጀ ነው።

ሐማስ ከገደላቸው ሰዎች በተጨማሪ 230 ሰዎችን አግቶ ወስዷል።

በታጋችነት ከወሰዳቸው ሰዎች መካከል አንድ ደቡብ አፍሪካዊ ዜግነት ያለው ይገኝበታል ተብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እስራኤል ሐማስን ሙሉ በሙሉ ከምድረ ገጽ አጠፋለሁ በማለት የዛተች ሲሆን የአየር ጥቃት በጋዛ ላይ ያለማቋረጥ እየፈጸመችው ነው።

በዚህም ከ10ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ይህ አሐዝ በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር ነው።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ የሆኑት ሊዯር ሃይት በኤክስ ገጻቸው በሰጡት አስተያየት፣ “የደቡብ አፍሪካ ዲፕሎማቶቿን ከቴልአቪቭ መጥራት ለሐማስ አሸባሪዎች ትልቅ ድል ነው” ብለዋል።

ጨምረውም፣ “እስራኤል፣ ደቡብ አፍሪካ ሐማስን እንድታወግዝ ትሻለች። ሐማስ ከአይሲስ የባሰ ነው። ደቡብ አፍሪካ የእስራኤልን ራሷን የመከላከል መብት ልታከብር ይገባ ነበር። ራሷን የምትከላከለው ደግሞ አሸባሪ ከሆነው ሐማስ ነው፣ እስራኤልን ከካርታ ለማጥፋት ከሚሰራው ሐማስ” ሲሉ ተቃውሟቸውን ገልጠዋል።

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት የፍልስጥኤምን ትግል ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ይደግፋል።

በተለይም ገዢው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ANC) የፍልስጥኤማዊያንን ለነጻነት የሚያደርጉትን ትግል ድርጅቱ ከአፓርታይድ ነጻ ለመውጣት ያደረገውን ትግል መሳ አድርጎ ነው የሚረዳው።

“ዲፕሎማቶችን መጥራት በዲፕሎማሲ የተለመደ አሠራር ነው፤ ዲፕሎማቶቹ ማብራሪያ ይሰጣሉ። ከዚያ ደግሞ መንግሥት በእርግጥ ግንኙነቱ መቀጠል አለበት ወይ በሚለው ላይ ይወስናል” ብለዋል የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፓንዶር።

የደቡብ አፍሪካ ካቢኔ በበኩሉ የእስራኤል አምባሳደር የሆኑት ኤሊያቭ ቤሎሰርኮቪስኪ ደቡብ አፍሪካን በተመለከተ የሰጡት ''አጸያፊ'' አስተያየትን ያወገዘ ሲሆን አምባሳደሩ የፍልስጥኤምን ትግል የሚደግፉ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ማብጠልጠላቸውን ተችቷል።

ደቡብ አፍሪካ ዲፕሎማቶቿን ከእስራኤል ለመጥራት ብቸኛዋ አገር አይደለችም።

እስራኤል በጋዛ የምታደርሰውን መጠነ ሰፊ ጥቃት ተከትሎ ቻድ፣ ቺሌ እና ኮሎምቢያ ተመሳሳይ እርምጃ ከወሰዱ አገራት ይጠቀሳሉ።