በእስራኤል ጦር የተከበበው ሆስፒታል ነዳጅ ጨርሶ ሥራ አቆመ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በእስራኤል ጦር ከበባ ስር የገባው አል-ሺፋ ሆስፒታል ነዳጅ በመጨረሱ ስራ ማቆሙን በሐማስ የሚተዳደረው ጤና ሚንስቴር አስታወቀ።
ከትናንት አርብ ምሽት ጀምሮ የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ ከተማ የሚገኘውን ሆስፒታል ከበው መያዛቸው ተዘግቧል።
የጤና ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሆስፒታሉ ነዳጅ በመጨረሱ ስራ አቁሟል ብለዋል። “በማሞቂያ ክፍል ውስጥ የነበረ ጨቅላ ሕይወቱ አልፏል። ሌሎች 45 ጨቅላዎች በሆስፒታሉ አሉ” ሲሌ አሽራፍ አል-ቂድራ ተናግረዋል።
የድምበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን አባል የሆኑት ሐኪም የተኩስ አቁም ካልተደረገ ወይም የሕክምና እርዳታ እንዲገባ ካልተደረገ “በሆስፒታሉ ያሉ ታካሚዎች በሙሉ አልቀው ሆስፒታሉ ወደ መቃብር ስፍራነት ይቀየራል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ዶ/ር መሐመድ አቡ የተባሉት ሐኪም ለቢቢሲ ሲናገሩ በሆስፒታሉ የሕጻናት ክፍል ውስጥ ይሰሩ የነበሩ የድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን ባለሙያዎች በሽተኞችን ጥለው ለመሸሽ ተገደዋል።
ሐኪሙ ጨምረው እንደተናገሩት የሕክምና ግብዓቶች ከፍተኛ እጥረት ስላለ ቀዶ ሕክምናዎች ያለ ማደንዘዣ እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

















