አሜሪካ ሰኞ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀውን የሰላም ውይይት እንደምትደግፍ አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፊታችን ሰኞ በደቡብ አፍሪካ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀውን የሰላም ውይይት እንደምትደግፍ አሜሪካ አስታወቀች።
ሰኞ ጥቅምት 14/2015 ዓ. ም. በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በትግራይ አመራሮች መካከል የሰላም ውይይት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲሁም የትግራይ አመራሮችም በዚህ የሰላም ውይይት ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ትላንት ጥቅምት 11፣ 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፣ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀውን የሰላም ውይይት አሜሪካ እንደምትደግፈው አትቷል።
“ደቡብ አፍሪካ ይህንን ውይይት ለማስተናገድ በመፍቀዷ እናመሰግናለን። የአፍሪካ ኅብረት ልዩ ልዑክ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆን እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት ፓናል አባል የሆኑተን ፑምዚሌ ማልምቦ ንግቹካ እና ኡሁሩ ኬንያታ የሰላም ስምምነት ላይ እንዲደረስ የሚያደርጉትን ጥረት እንደግፋለን” ይላል መግለጫው።
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ድረ ገጽ ላይ የወጣው መግለጫ “ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን መስከረም ላይ በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንዳሉት፣ የአፍሪካ ኅብረት ፓናል አባላቱ አማካይነት የሚደረሰው የሰላም ስምምነት፣ በኢትዮጵያ ያለውን ውጊያ ይገታል። ለሁሉም ዜጎች መረጋጋትንም ይመልሳል” ሲልም አክሏል።
በተያያዥ፣ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክርቤት በኢትዮጵያን ጉዳይ ለመወያየት ያደረገውን ውይይት ተከትሎ፣ በተመድ የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ በሰጡት መግለጫ፣ “አሁንም መናገር የምንፈልገው ተተፋላሚ ወገኖች ጠመንጃቸውን አስቀምጠው ንግግር እንዲጀምሩ ነው” ብለዋል።
ጨምረውም “ሁለት ዓመት በዘለቀው ጦርነት ከግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ሞቷል። አሜሪካ በቀጣይ ሊመጣ የሚችለው ነገር ያሳስባታል። በቅርቡ በተገደለው የዓለም አቀፉ ሬስኪው ኮሚቴ ባልደረባ ሐዘን ተሰምቶናል። ዛሬ እንደተነገረን ከሆነ በድምሩ 26 ሰብአዊ ድጋፍ ሠራተኞች ተገድለዋል” ብለዋል አምባሳደር ሊንዳ።
አምባሳደር ሊንዳ በንግግራቸው “ኤርትራ በጥምር የከፈተችውን ጥቃት እንድታቆም እንጠይቃለን። ኢትዮጵያም ኤርትራን ወታደሮቿን ከትግራይ ክልል እንድታስወጣ መጠየቅ ይኖርባታል” ብለዋል።
አፍሪካ ኅብረት ሰኞ በደቡብ አፍሪካ ንግግር እንደሚጀመር ማሳወቁ እንዳስደሰታቸው እና የኢትዮጵያ መንግሥትና የትግራይ ኃይሎች በዚህ ንግግር ለመገኘት መፍቀዳቸውም በደስታ እንደሚቀበሉት ተናግረዋል።
አምባሳደር ሊንዳ “አሜሪካ የአፍሪካ ኅብረትን በማገዝ ረገድ በሙሉ አቅምና በቀጥተኛ ሁኔታ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረቶችን እያደረገች” እንደሆነ ተናግረዋል።
አይይዘውም “ለዚህ እንቅፋት በሚሆኑት እና ሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በሚፈጽሙ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኛና ዝግጁ ነን” ብለዋል።
“ለዚህ ግጭት ወታደራዊ መፍትሄ የለውም። መቋጨት ያለበትም በድርድር ነው። ይህ ግጭት ከቁጥጥር ውጭ ወጥቶ አካባቢውን እንዳያምስ እንሰጋለን። የምናባክናት ደቂቃ መኖር የለባትም” ሲሉም ተደምጠዋል።
የትግራይ ኃይሎች በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር የፊታችን ሰኞ በደቡብ አፍሪካ ሊደረግ በታቀደው የሰላም ንግግር መድረክ ላይ እንደሚገኙ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ መዘገቡ ይታወሳል።
የትግራይ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት ናቸው “የኛ ልዑካን ይሳተፋሉ” ሲሉ በጽሑፍ መልዕክት ያስታወቁት።
የሰላም ንግግሩ በመጪው ሰኞ እንደሚደረግ ከአፍሪካ ኅብረት መስማታቸውን የጠቅላይ ሚንስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን በትዊተር ገጻቸው ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
አምባሳደሩ በትዊተር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት “በንግግሩ ለመሳተፍ ቁርጠኛ መሆናችንን በድጋሚ አረጋግጠናል” ብለዋል።
ሁለቱም ወገኖች በደቡብ አፍሪካው የሰላም ውይይት ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆናቸውን ከገለጹ በኋላ፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ባወጣው መግለጫ “የአፍሪካ ኅብረት አጋር እንደመሆናችን በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ እንቀጥላለን” ብሏል።
በተያያዥም “ለአምስት ወራት የዘለቀው ሰብአዊ ተኩስ አቁም ነሐሴ ላይ መሰበሩን ተከትሎ፣ በርካታ ሕይወት መጥፋቱ፣ ውድመት መከሰቱ፣ የዘፈቀደ ድብደባ መፈጸሙ እና የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸሙ ያሳስበናል። መጠነ ሰፊው ቀውስም ያሰጋናል” ሲል የአሜሪካ መንግሥት አቋሙን ገልጿል።
ከሳምንታት በፊት በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ይካሄዳል ተብሎ የነበረው የሰላም ንግግር መሸጋገሩን ተከትሎ በነበሩት ቀናት ውጊያው የቀጠለ ሲሆን፤ የፌደራሉ መንግሥት ሽረ እና አላማጣን መያዙ አይዘነጋም።
መንግሥት የኮረም ከተማንም እንደያዘ ቢናገርም፤ የትግራይ አመራሮች ግን ከተማዋ አሁንም በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ናት ብለዋል።
በቀጠለው ጦርነትም በርካታ ንጹኃን ሰዎች እንደተገደሉና እንደተፈናቀሉም ሪፖርቶች እየወጡ ይገኛሉ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በቀጣዩ ሳምንት የሚጠበቀውን የሰላም ውይይት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ “ከሰላም ውይይቱ ቀድሞ ሁሉም ወገኖች በአፋጣኝ ግጭት እንዲያቆሙ እንጠይቃለን። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንዲሁም የኤርትራ መከላከያ ጥምር ወታደራዊ እርምጃቸውን ገትተው የንጹኃንን ደኅንነት እንዲጠበቅ እናሳስባለን” ብሏል።
በተጨማሪም “ኤርትራ ወታደራዊ ኃይሏን ከሰሜን ኢትዮጵያ እንድታስወጣ እና ሰብአዊ እርዳታ ለሚያሻቸው ሁሉ ያልተገደበ ድጋፍ በአፋጣኝ እንዲቀጥል ጥሪ እናቀርባለን” ሲል አክሏል።
በመጪው ጥቅምት 24/2015 ዓ. ም. ሁለት ዓመት የሚሞላው ጦርነት በአሥር ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት፣ ለመቶ ሺዎች መፈናቀል፣ ሚሊዮኖችን ደግሞ ሰብአዊ እርዳታ ጠባቂ ከማድረግ ባሻገር ከባድ ቁሳዊ ውድመትን አስከትሏል።












