በጦርነቱ ሳቢያ አገር ቤት መመለስ የማይችሉ ኢትዮጵያውያን አሜሪካ እንዲቆዩ ተፈቀደ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት እአአ ከጥቅምት 20/2022 በፊት አሜሪካ እየኖሩ ያሉ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ በጊዜያዊነት እንዲቆዩ ፈቀደ።
ይህም ኢትዮጵያ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ኢትዮጵያውያኑ ወደ አገራቸው መመለስ እንደማይችሉ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለ18 ወራት በአሜሪካ እንዲቆዩ የሚፈቅድ አሠራር ነው።
'ቴምፖራሪ ፕሮቴክትድ ስታተስ' ወይም TPS በአሜሪካ ላሉና ወደ አገራቸው መመለስ አደጋ ሊያጋልጣቸው ይችላል ለሚባሉ ሰዎች ይሰጣል።
የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት ጸሐፊ አሌሀንድሮ ማዮርካስ “ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ግጭት አሜሪካ ትገነዘባለች። አሁናዊና አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያለች አገር ስለሆነች ጊዜያዊ ከለላ ለሚያስፈልጋቸው ጥበቃ እናደርጋለን” ብለዋል።
“አሁን አሜሪካ ያሉና በግጭት፣ በጎርፍ፣ በድርቅ፣ በመፈናቀል ወይም በምግብ እጥረት ሳቢያ በተነሳ ሰብአዊ ቀውስ ምክንያት ወደ አገራቸው መመለስ የማይችሉ ኢትዮጵያውያን፤ አገራቸው ያለው ሁኔታ እስከሚሻሻል ድረስ አሜሪካ ቆይተው መሥራት ይችላሉ” ሲሉም አክለዋል።
አሜሪካ በጊዜያዊነት ቆይታ የምትሰጠው በአንድ አገር ወታደራዊ ግጭት፣ ተፈጥሯዊ ቀውስ ወይም ሌላ ጊዜያዊ አስጊ ሁኔታ ሲገጥም ነው።
በአሜሪካ ያሉ ኢትዮጵያውያን እንዲቆዩ የተፈቀደው በጦርነቱ እንዲሁም ባለው ጊዜያዊ አስጊ ሁኔታ ምክንያት እንደሆነ የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት ያወጣው መግለጫ ይጠቁማል።
“ያለው ሁኔታ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ከኢትዮጵያ የመጡ ነገር ግን አሁን ላይ ዜግነት የሌላቸው ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመለሱ ያስገድዳል” ይላል መግለጫው።
መግለጫው አክሎም፤ በወታደራዊ ግጭቱ ንጹኃን ዜጎች ግድያ እና መደፈርን ጨምሮ ለጾታዊ ጥቃቶች፣ ለብሔር ተኮር አፈና፣ ለእንግልት እንዲሁም ለሌሎችም የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንደሚጋለጡ አብራርቷል።
“ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው መመለስ ከማይችሉበት ምክንያት መካከል ከፍተኛ የምግብ እጥረት፣ ድርቅ፣ መጠነ ሰፊ መፈናቀል እና የተለያዩ ሕመሞች ይጠቀሳሉ” ሲል የደኅንነት ቢሮው ችግሩን ገልጾታል።
ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ በጊዜያዊነት እንዲቆዩ አሜሪካ ስትፈቅድ ይህ የመጀመሪያው ነው።
ፍቃዱ የተሰጣቸው እአአ ከጥቅምት 20/2022 በፊት አሜሪካ የገቡና እዛው እየኖሩ ያሉ ሰዎች ሲሆኑ፤ ከዚህ ቀን በኋላ ወደ አሜሪካ የሚጓዙ ሰዎች ግን በፈቃዱ እንደማይካተቱ ቢሮው አመልክቷል።
ኢትዮጵያውያን ለዚህ ፈቃድ ብቁ ሆነው ከተገኙ ከደኅንነትና ከጀርባ ታሪክ ጋር የተያያዘ ፍተሻን አልፈው ለ18 ወራት የሚቆየው ፍቃድ ውስጥ እንደሚካተቱ ተገልጿል።
የፊታችን ሰኞ በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል በደቡብ አፍሪካ ውይይት እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
ሁለቱም ወገኖች በሰላም ውይይቱ ለመሳተፍ ፈቃደኛነታቸውን ገልጸዋል።
በሁለቱ ወገኖች መካከል ሊደረግ የታቀደው የሰላም ንግግር ጦርነቱ በተለያዩ ግንባሮች ተባብሶ ቀጥሏል በተባለበትና የሰላማዊ ሰዎች መገደልና መፈናቀል ሪፖርት እየተደረገ ባለበት ወቅት ነው።
ለሁለት ዓመት በዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላማዊ ዜጎች ላይ መደፈር፣ ወሲባዊ ጥቃቶች፣ የዘፈቀደ ግድያ እና ረሃብ እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋላቸውን የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ሪፖርት ያሳያል፥።
ጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን ህይወት በመቅጠፍ፣ ሚሊዮኖችን በማፈናቀልና ለረሃብ በመዳረግ መጠነ ሰፊ ቀውስ አድርሷል።












