የሰላም ንግግሩ ከአራት ቀናት በኋላ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ መንግሥት ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, MINISTRY OF FOREIGN AFFAIRS
በፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል እንደሚካሄድ የሚጠበቀው የሰላም ውይይት የፊታችን ጥቅምት 14/2015 ዓ. ም. በደቡብ አፍሪካ እንደሚደረግ ከአፍሪካ ኅብረት እንደተነገራቸው የጠቅላይ ሚንስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የሆኑት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።
አምባሳደር ሬድዋን በትዊተር ገጻቸው ዛሬ ጥቅምት 10/2015 ዓ. ም. እንደጻፉት፣ ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የደረሳቸው መረጃ፣ የሚጠበቀው የሰላም ውይይት ከአራት ቀናት በኋላ በደቡብ አፍሪካ ይከናወናል።
“በንግግሩ ለመሳተፍ ቁርጠኛ መሆናችንን በድጋሚ አረጋግጠናል” ብለዋል አምባሳደር ሬድዋን።
አክለውም “ሆኖም ግን ጥቂቶች የሰላም ንግግሩን ቀድመው ዋጋ በማሳጣታቸው እና ስለ መከላከል እርምጃቸው የተሳሳተ ክስ በማሰማታቸው አዝነናል” ብለዋል።
እስካሁን ድረስ ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የሰላም ንግግርን በተመለከተ የተባለ ነገር ስለመኖሩ የትግራይ ኃይሎች ያሉት ነገር የለም።
ከሁለት ሳምንታት በፊት የአፍሪካ ኅብረት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሊያካሂደው አስቦት በነበረው የሰላም ንግግር ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቦ፣ ሁለቱም ወገኖች ተሳታፊ ለመሆን ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸው እንደነበር ይታወሳል። ነገር ግን በሎጅስቲክስ አለመሟላት የንግግሩ ቀን እንዲሸጋገር ተወስኗል።
በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ይካሄዳል ተብሎ የነበረው የሰላም ንግግር መሸጋገሩን ተከትሎ በነበሩት ቀናት ውጊያው ቀጥሎ የነበረ ሲሆን፤ የፌደራሉ መንግሥት ሽረ እና አላማጣን መያዙ አይዘነጋም።
መንግሥት የኮረም ከተማንም እንደያዘ ቢናገርም፤ የትግራይ አመራሮች ግን ከተማዋ አሁንም በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ናት ብለዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ጥቅምት 4/2015 ዓ. ም. የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በአስቸኳይ ቆሞ ሰብአዊ እርዳታ እንዲቀርብ በድጋሚ መጠየቁ ይታወሳል። ይህ ጥሪ ተፈጻሚ እንዲሆንም የትግራይ ኃይሎች ጠየቀዋል።
በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በሰጡት መግለጫ "በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጭ እየወጣ ነው" ያሉ ሲሆን ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ዳግም ጠይቀዋል።
ከዚህ በተጨማሪም "የኤርትራ ሠራዊት ከኢትዮጵያ በአስቸኳይ እንዲወጣ” ጥሪ አቅርበዋል።
የአውሮፓ ኅብረትም የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጦር በትግራይ እያካሄዱት ያሉትን ወታደራዊ ዘመቻ እንዲያቆሙ እና ኤርትራ ጦሯን ከኢትዮጵያ እንድታስወጣ ጠይቋል። ኅብረቱ ህወሓትም ከወታደራዊ እንቅስቃሴዎች እና ከጠብ ጫሪ ድርጊቶቹ እንዲቆጠብ አሳስቧል።
በመጪው ጥቅምት 24/2015 ዓ. ም. ሁለት ዓመት የሚሞላው ጦርነት በአሥር ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት፣ ለመቶ ሺዎች መፈናቀል፣ ሚሊዮኖችን ደግሞ ሰብአዊ እርዳታ ጠባቂ ከማድረግ ባሻገር ከባድ ቁሳዊ ውድመትን አስከትሏል።












