መንግሥት የከተማ ጦርነት ሳላካሂድ የሽረ፣ አላማጣ እና ኮረም ከተሞችን ያዝኩ አለ

የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት

የፌደራሉ መንግሥት የከተማ ጦርነት ሳላካሂድ የትግራይ ከተሞች የሆኑትን ሽረ፣ አላማጣ እና ኮረምን ያዝኩ አለ።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ማክሰኞ ከሰዓት ጥቅምት 8/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የአገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ የከተማ ውስጥ ውጊያ ሳያካሂድ የትግራይ ከተሞች የሆኑትን ሽረ፣ አላማጣ እና ኮረምን መያዙን አስታወቋል።

የትግራይ ኃይሎች ሽረ ከተማ በመንግሥት ጥምር ኃይል ስር መግባቱን ይግለጹ እንጂ እስካሁን ድረስ አላማጣ እና ኮረምን በተመለከተ ያሉት ነገር የለም።

ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት በቁጥጥሩ ስር በገቡ የትግራይ ከተሞች የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ስራዎች እንደሚጀመሩ በመግለጫው አስታውቋል።

የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ትናንት ጥቅምት 7/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ያሉ አየር ማረፊያዎችን እና የፌደራል ተቋማትን በአሰቸኳይ መቆጣጠር ቁልፍ ጉዳይ ነው ማለቱ ይታወሳል።

የፌደራሉ መንግሥት የትግራይ ከተሞችን መያዙን እና በከተሞቹ የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያቀርብ የገለጸው በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጪ ሆኗል ከተባለ በኋላ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ትናንት ሰኞ ጥቅምት 7/2015 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ "በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጭ እየወጣ ነው" ያሉ ሲሆን ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ዳግም ጠይቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም "የኤርትራ ሠራዊት ከኢትዮጵያ በአስቸኳይ እንዲወጣ” ጥሪ አቅርበዋል።

ጉተሬዝ ይህን ማለታቸውን ተከትሎ የጠቅላይ ሚንስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬደዋን ሁሴን በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጪ አይደለም ብለዋል።

የፌደራሉ መንግሥት የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ውይይቱ የሚካሄድበትን ቀን እስኪያሳውቅ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት አምባሳደሩ፤ ግጭቱ እየተስፋፋ የነበረው ወደሌሎች ክልሎች እየተዛመተ በነበረበት ወቅት እንጂ አሁን ላይ ግጭቱ እየተስፋፋ አይደለም ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፈረዋል።

የአውሮፓ ኅብረት በበኩሉ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጦር በትግራይ የእያካሄዱት ያሉትን ወታደራዊ ዘመቻ እንዲያቆሙ እና ኤርትራ ጦሯን ከኢትዮጵያ እንድታስወጣ ጠይቋል። ኅብረቱ ህወሓትም ከወታደራዊ እንቅስቃሴዎች እና ከጠብ ጫሪ ድርጊቶቹ እንዲቆጠብ አሳስቧል።

በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚገኙ የትግራይ አካባቢዎች

ሽረ፣ አላማጣ እና ኮረም

የፌደራሉ መንግሥት በሰሜን ምዕራብ ትግራይ የምትገኘውን ሽረ እንዳስላስ ከተማን እንዲሁም የራያ አላማጣ ወረዳ መዲና አላማጣን እና ኮረም ከተማን መያዙን ከመግለጹ ቀደም ብሎ የትግራይ ኃይሎች ሽረ ከተማ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጥምር ጦር በቁጥጥር ሥር መግባቷን አስታውቀው ነበር።

ከትግራይ ማዕከላዊ ኮማንድ ተሰጠ በተባለው እና በክልሉ መገናኛ ብዙኃን በተላለፈው መግለጫ፤ የኢትዮጵያና የኤርትራ ኃይሎች የሽረ ከተማን ጥቅምት 7፣ 2015 ዓ.ም መያዛቸውን አስታውቀዋል።

መግለጫው ጥምር ኃይሎቹ በተለያዩ ግንባሮች መጠነ ሰፊ ጥቃት እንደከፈቱ ገልጾ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች እንደተገደሉና ነዋሪዎች ለተደጋጋሚ መፈናቀል መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

የትግራይ ኃይሎች የሽረ ከተማ የተያዘችው በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጥምር ኃይሎች ነው ይበሉ እንጂ የፌደራሉ መንግሥት የኤርትራ ጦር በዚህ ጦርነት ተሳታፊ ስለመሆኑ ያለው ነገር የለም።

ሽረ ከተማ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች እና ንብረትነቱ “የጠላት አገር የሆነ አውሮፕላን ያርፍበት ነበረ” የተባለ አየር ማረፊያ መገኛ ከተማ ናት።

የትግራይ ኃይሎች የሽረን መያዝ ባስታወቁበት መግለጫቸው “በጦርነት ወቅት ከአካካቢዎች መገፋፋት ተፈጥሯዊ ነው” ካሉ በኋላ “ሽረ ከተማን ጨምሮ አንዳንድ አካባቢዎችን ለጊዜው ቢቆጣጠሩም አቅሙ የፈቀደ ሁሉ ይታገል” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የሰብዓዊ እርዳታ ጅማሮ

የመንግሥት ኩሙኒኬሽን ዛሬ ባወጣው መግለጫ የአገር መከላከያ ሠራዊት ሰላማዊ ሰዎችን ለመጠበቅ የወሰዳቸው እርምጃዎች እስካሁን ድረስ ውጤታማ ሆነዋል ብሏል።

መንግሥት ይህን ይበል እንጂ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ አየር ኃይሎች አካሂደዋቸዋል በተባሉት የአየር ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸውን እና መኖሪያ መንደሮች መውደማቸውን የትግራይ ኃይሎች እና የሰብዓዊ ድርጅት ሠራተኞች ሲናገሩ ቆይቷል።

የፌደራሉ መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች ባስለቀቃቸው ከተሞች የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ስራ እንደሚጀመር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በመግለጫው ጨምሮ ገልጿል።

በሽረ አየር ማረፊያ በኩል እንዲሁም በሌሎች በመንግሥት ቁጥጥር ሥር በገቡ አካባቢዎች የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅት መጀመሩን እና ከሚመለከታቸው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ድርጅቶች ጋር እንደሚጣመር መንግሥት አስታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት ከሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ጋር በመሆን የሰብዓዊ እርዳታ መተላለፊያ መስመሮችን ለማስፋፋት ዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጿል።

“የሰሜን ጎንደር-ሽረ እንዲሁም የኮምቦልቻ-ደሴ-ቆቦ-አላማጣ መስመሮች ለመክፈት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው” ይላል የዛሬው መግለጫ።