ሆስፒታል ከገባ 10 ቀናት የተቆጠሩት አሊ ቢራ ሕክምና እየተከታተለ መሆኑን ቤተሰቦቹ ገለፁ

ድምጻዊ አሊ ቢራ

ድምጻዊ አሊ ቢራ ባጋጠመው የጤና እክል የተነሳ አዳማ ጄነራል ሆስፒታል ከገባ 10 ቀናት የሞሉት ሲሆን ተገቢው ሕክምና ክትትል እየተደረገለት መሆኑን ቤተሰቦቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የ75 ዓመቱ አርቲስት አሊ ቢራ ከዚህ ቀደምም የጤና እክል አጋጥሞት በአዲስ አበባ እና አዳማ ከተሞች በሚገኙ ሆስፒታሎች የውስጥ ደዌ ህክምና ተደርጎለት ነበር።

አሊ ቢራ ባለፉት 60 ዓመታት በኦሮሞ የሙዚቃ ስራዎች ውስጥ ከፍተኛ ስም እና ዝና አግኝቶ ቆይቷል።

በርካቶች ለኦሮምኛ ቋንቋ የሙዚቃ እድገትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ይናገራሉ።

አሊ ቢራ ከዚህ ቀደም የልብ እና የስኳር በሽታዎች ታማሚ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሮ ነበር።

ከድሬዳዋ እና ከጅማ ዩኒቨርስቲዎች የክብር ዶክትሬት የተቀበለው አሊ ቢራ፤ ለዓመታት ባስደመጣቸው ነጻነትና ፍቅርን በሚሰብኩ ሙዚቃዎቹ ይታወቃል።

በ50 ዓመት የሙዚቃ ሕይወቱ ከ260 በላይ ሙዚቃዎችን የተጫወተው አሊ ቢራ፣ ከ30 በላይ ሽልማቶችን ተቀብሏል።

በቅርቡም በተወለደበት ከተማ በስሙ ፓርክ ተሰይሞለታል።

አሊ ቢራ በግንቦት ወርበ1940 ዓ.ም በድሬዳዋ ተወለደ።

አርቲስት አሊ ቢራ በ1954 ዓ.ም የተመሰረተውን የመጀመሪያው የኦሮምኛ ቋንቋ የኪነት-ቡድን “አፍረን ቀሎ”ን በመቀላቀል ነበር የሙዚቃ ስራውን የጀመረው።

ድምጻዊ አሊ ከኦሮምኛ በተጨማሪ፣ በሱማሊኛ፣ በአፋርኛ፡ በሐረሪ፣ በአማርኛና በሱዳን ቋንቋዎች በርካታ ዘፈኖችን መጫወት ችሏል።