የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና አጋር ኃይሎች የሽረ ከተማን መያዛቸውን የትግራይ ኃይሎች ገለጹ

የሽረ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና አጋር ኃይሎች የሽረ ከተማን መያዛቸውን የትግራይ ኃይሎች ገለጹ።

የትግራይ ማዕከላዊ ኮማንድ በትናንትናው ዕለት ባወጣውና በክልሉ መገናኛ ብዙኃን በተላለፈው መግለጫ የኢትዮጵያና የኤርትራ ኃይሎች የሽረ ከተማን ጥቅምት 7፣ 2015 ዓ.ም መያዛቸውን አስታውቀዋል።

መግለጫው ጥምር ኃይሎቹ በተለያዩ ግንባሮች መጠነ ሰፊ ጥቃት እንደከፈቱ ገልጾ በበርካታ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች እንደተገደሉና ነዋሪዎች ለተደጋጋሚ መፈናቀል ተዳርገዋል ብሏል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል በበኩሉ ሁለት የዲፕሎማቲክ እና የሰብአዊ እርዳታ ተቋም ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው የኢትዮጵያ መንግሥትና አጋሮቹ በትናንትናው ዕለት ሽረ ከተማን ይዘዋል።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች መጠለያ የሆነችው ሽረ መያዝን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ከኤርትራ ኃይሎች በኩል በይፋ የተባለ ነገር የለም።

ነገር ግን የፌደራሉ መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ የመከላከል እርምጃ እርምጃ እየወሰድኩ ያለሁት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማረጋገጥ በማስፈለጉ ነው በማለት በትናንትናው ዕለት መግለጫ ሰጥቷል።

የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ትናንት ጥቅምት 7/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ “የህወሓት መጠነ ሰፊ ጥቃት ቡድኑን በሚደግፉ የውጪ አገር ጠላት ኃይሎች የአየር ክልል ጥሰት ጭምር የታገዘ ነበር” ብሏል።

ለዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ያሉ አየር ማረፊያዎችን እና የፌደራል ተቋማትን በአሰቸኳይ መቆጣጠር ቁልፍ ጉዳይ ነው ሲል አክሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የትግራይ ማዕከላዊ ኮማንድ መግለጫ አክሎም የትግራይ ሰራዊት የሞት እና የህይወት ትግል ይቀላል ብሏል።

“በጦርነት ወቅት ከአካካቢዎች መገፋፋት ተፈጥሯዊ ነው” ያለው መግለጫው “ኃይሎቹ ሽረ ከተማን ጨምሮ አንዳንድ አካባቢዎችን ለጊዜው ቢቆጣጠሩም አቅሙ የፈቀደ ሁሉ እንዲታገል ጥሪ” ቀርቧል።

ከዚህም በተጨማሪ መግለጫው ለአለም አቀፉ ማህበረቡም ጥሪ ያቀረበ ሲሆን በትግራይ እየተፈጸሙ ያሉ የአለም አቀፍ ህግ ጥሰቶችን ተረድቶ አፋጣኝ መፍትሄዎችን መስጠት አለበት ብሏል።

ጦርነቱን በማስቆም እና ወደ ትግራይ የሚደርሰው ሰብዓዊ እርዳታ በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማረጋገጥ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቋል።

የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ወታደሮች የትግራይ ኃይሎችን ከነዚህ ከተሞች ከተገፉ የደም መፋሰስ እንደሚከሰት ዲፕሎማቶች ከሰሞኑ እያስጠነቀቁ ነው።

በክልሉ እየተካሄደ ያለው መጠነ ሰፊ ጥቃት ተጠናክሮ በመቀጠሉም የምግብ እና የህክምና ግብዓት እያለቀ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ከሰሞኑ በሽረ ከተማ ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት የነፍስ አድን ቡድን የረድዔት ሰራተኛ ለሴቶች እና ህጻናት እርዳታ እያቀረቡ ባለበት ወቅት መገደላቸው ተገልጿል።

በዚህ ጥቃት ሌሎች ሰላማዊ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን በሽረ ከተማ እየተፈጸሙ ያሉትን የአየር ጥቃቶች በተመለከተ የአሜሪካ መንግሥት ተራድኦ ድርጅት ኃላፊ ሳማንታ ፓዎር “ጥቃቶቹ አሳሳቢ ናቸው” ብለዋል።

በተለይም በርካታ ስደተኞችን የያዙ ማዕከላት በኢትዮጵያና በኤርትራ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋል ስጋት እንዳጫረባቸው ሳማንታ ፓወር ገልጸዋል።

 "በነዚህ ጥቃቶች የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይልና የኤርትራ መከላከያ ኃይል የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፖችን ከተቆጣጠሩ በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ ተጨማሪ ጥቃት እና ግድያ የመፈጸም እድሉ ከፍተኛ ነው" ብለዋል።

የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ እና የደህንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፍ ቦረል በበኩላቸው “በሽረ የቀጠለው ጦርነት እንዲሁም ሰላማዊ ነዋሪዎች ኢላማ የመደረጋቸው ሪፖርት አስደንጋጭ ነው” ብለዋል ። 

የኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራ ኃይሎች ጋር በመሆን ከትግራይ ኃይሎች ጋር እየተዋጋ ባለበት ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹኃን ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከቤት ንብረታቸው ከመፈናቀላቸው ባሻገር የረሃብ አደጋ ተጋርጦባቸዋል።

ለአምስት ወራት የቆየው የሰብአዊ ተኩስ አቁም ስምምነት ፈርሶ ነሐሴ ላይ ጦርነቱ ካገረሸበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ ግንባሮች ውጊያዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ።

ባሳለፍነው ሳምንት ማገባደጃ ላይ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ መሐመት፤ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በአስቸኳይ ቆሞ ሰብአዊ እርዳታ እንዲቀርብ ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ኅብረቱ ቅዳሜ ጥቅምት 4/2015 ዓ. ም. የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መቀጠል እንዳሳሰበው መግለጫ ማውጣቱን ተከትሎ፤ የትግራይ አስተዳደር ጥቅምት 5/2015 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ያወጣውን መግለጫ በበጎ ጎኑ እንደሚቀበለው አስታውቋል።

የፌደራል መንግሥቱ በትግራይ የሚያደርገውን የፌደራል ማዕከላት የመቆጣጠር ወታደራዊ ዘመቻውን እንደሚቀጥል በገለጸበት መግለጫው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በውይት ለመፍታት አሁንም ቁርጠኛ ነኝ ብሏል።

ከሁለት ሳምንታት በፊት የአፍሪካ ኅብረት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሊያካሂደው አስቦት በነበረው የሰላም ንግግር ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቦ፣ ሁለቱም ወገኖች ተሳታፊ ለመሆን ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።

ነገር ግን “በሎጂስቲክስ አለመመቻቸት ምክንያት” ተብሎ ግልፅ ባልሆነ ምክንያት ለሌላ ጊዜ መተላለፉ ይታወሳል።

የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ የአውሮፓ ህብረትና አሜሪካ ተፋላሚ ወገኖች ተኩስ አቁመው ወደ ውይይቱ እንዲመለሱ ጥሪ እያቀረቡ ነው።