የትግራይ ኃይሎች በመጪው ሰኞ በሚደረገው የሰላም ንግግር እንደሚሳተፉ ተነገረ

የትግራይ ጦርነት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የትግራይ ኃይሎች በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር የፊታችን ሰኞ ጥቅምት 14፣ 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ሊደረግ በታቀደው የሰላም ንግግር መድረክ ላይ እንደሚገኙ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገበ።

በፌደራሉ መንግሥትና በትግራይ ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ያለውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላም ለመቋጨት በሚደረገው በዚህ ንግግር ላይ የትግራይ ልዑካን ተሳታፊ እንደሚሆኑ ኤኤፍፒ የትግራይ አመራርን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

“የኛ ልዑካን ይሳተፋሉ” ሲሉ የትግራይ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በዛሬው ዕለት ጥቅምት 11፣ 2015 ዓ.ም በላኩት የጽሁፍ መልዕክት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቀጣዩ ሰኞ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በሚደረገው ንግግር ላይ መንግሥት እንደሚሳተፍ በዛሬው ዕለት ገልጿል።

በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር የሚካሄደው የሰላም ንግግር በመጪው ሰኞ እንደሚደረግ ከህብረቱ መስማታቸውን የጠቅላይ ሚንስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የሆኑት አምባሳደር ሬድዋን በትናንትናው ዕለት አስታውቀዋል።

አምባሳደሩ በትዊተር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት “በንግግሩ ለመሳተፍ ቁርጠኛ መሆናችንን በድጋሚ አረጋግጠናል” ብለዋል።

አክለውም “ሆኖም ግን ጥቂቶች የሰላም ንግግሩን ቀድመው ዋጋ በማሳጣታቸው እና ስለ መከላከል እርምጃቸው የተሳሳተ ክስ በማሰማታቸው አዝነናል” ብለዋል።

በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚደረገው የሰላም ንግግር ጦርነቱ በተለያዩ ግንባሮች ተባብሶ ቀጥሏል በተባለበትና የሰላማዊ ሰዎች መገደልና መፈናቀል ሪፖርት እየተደረገ ባለበት ወቅት ነው።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤትም በዛሬው ዕለት ተባብሶ በቀጠለው ጦርነትና በሰላማዊ ዜጎች ላይ በደረሰው ጥቃት ላይ በዝግ እንደሚወያይ ምክር ቤቱ አስታውቋል።

የአፍሪካ ህብረት የሰላምና የጸጥታ ምክር ቤትም በዛሬው ዕለት ተሰብስቦ የነበረ ሲሆን ውይይቱን ያሸማግላሉ ተብለው የሚጠበቁት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ገለጻ አድርገዋል።

15 አባላት የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና የጸጥታ ምክር ቤት በዛሬው ዕለት በዝግ ስብሰባ ሲያደርግ ጦርነቱ ካገረሸ በኋላ የመጀመሪያው ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአፍሪካ ኅብረት ከሰሞኑ በተለያዩ ግንባሮች ተባብሶ የቀጠለው ጦርነት እንዳሳሰበው መግለጫ ማውጣቱን ተከትሎ፤ የትግራይ አስተዳደር ጥቅምት 5/2015 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ያወጣውን መግለጫ በበጎ ጎኑ እንደሚቀበለው አስታውቋል።

የፌደራል መንግሥቱ በትግራይ የሚያደርገውን የአየር ማረፊያዎችንና የፌደራል ማዕከላት የመቆጣጠር ወታደራዊ ዘመቻውን እንደሚቀጥል በገለጸበት መግለጫው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በውይት ለመፍታት አሁንም ቁርጠኛ ነኝ ብሏል።

ከሁለት ሳምንታት በፊት የአፍሪካ ኅብረት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሊያካሂደው አስቦት በነበረው የሰላም ንግግር ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቦ፣ ሁለቱም ወገኖች ተሳታፊ ለመሆን ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።

ነገር ግን “በሎጂስቲክስ አለመመቻቸት ምክንያት” ተብሎ ግልፅ ባልሆነ ምክንያት ለሌላ ጊዜ መተላለፉ ይታወሳል።

በተጨማሪም ከአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ፣ ከደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፉምዚሌ ምላምቦ-ናግኩካ ጋር በአሸማጋይነት በንግግሩ ይሳተፋሉ ተብለው የነበሩት ኬንያታ በመጨረሻው ሰዓት በሰላም ውይይቱ እንደማይገኙ መግለጻቸው ይታወሳል።

ኡሁሩ ለውይይት የተቆረጠው ቀን እሳቸው ከያዙት ሌላ መረሃ ግብር ጋር በተመሳሳይ ጊዜ በመሆኑ መገኘት እንደማይችሉ ገልጸው ለወደፊቱ ግን “ንግግሩ ስለሚካሄድበት ሂደት አወቃቀር እና አፈጻጸም፣ የተጋበዙ አሸማጋዮች መመሪያ ላይ ማብራሪያ” መጠየቃቸው የሚታወስ ነው።

በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ይካሄዳል ተብሎ የነበረው የሰላም ንግግር መሸጋገሩን ተከትሎ በነበሩት ቀናት ውጊያው የቀጠለ ሲሆን፤ የፌደራሉ መንግሥት ሽረ እና አላማጣን መያዙ አይዘነጋም።

መንግሥት የኮረም ከተማንም እንደያዘ ቢናገርም፤ የትግራይ አመራሮች ግን ከተማዋ አሁንም በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ናት ብለዋል። በቀጠለው ጦርነትም በርካታ ንጹሃን ሰዎች እንደተገደሉና እንደተፈናቀሉም ሪፖርቶች እየወጡ ይገኛሉ።

የአውሮፓ ህብረት ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከኤርትራ ሰራዊት ጋር በመተባበር በትግራይ እያካሄዱት ያለውን የጋራ ጥቃት እንዲያቆሙ ከሰሞኑ ጠይቋል።

ህብረቱ የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት ሙሉ በሙሉ እንዲወጡም ጠይቋል።

ከህብረቱ በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በተመሳሳይ መልኩ የኤርትራ ወታደሮች በአስቸኳይ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ለሁለት ዓመት የዘለቀውና በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን የቀጠፈው ደም አፋሳሽ ጦርነት አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት አንቶኒዮ ጉቴሬዝ “በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጭ እንደወጣ ገልጸው የሰላም ውይይቱ በአስቸኳይ እንዲጀመር ጠይቀዋል።

የአውሮፓ ህብረት በሰሞኑ መግለጫ የትግራይ ኃይሎች በአማራ እና አፋር አጎራባች ክልሎች ያለውን ጦርነት እንዲያቆሙና ከወታደራዊ ዘመቻ እንዲቆጠቡም አሳስቧል።

የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ የአውሮፓ ህብረትና አሜሪካ ተፋላሚ ወገኖች ተኩስ አቁመው ወደ ውይይቱ እንዲመለሱ ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ።