ከንግሥቲቱ ሞት በኋላ በዩናይትድ ኪንግደም ምን ይከናወናል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀዳማዊት ንግሥት ኤልዛቤጥ ሞትን ተከትሎ እስከ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ድረስ የሚኖሩ ዝርዝር ሥርዓቶች ይፋ የሚደረጉ ቢሆንም፤ የንግሥቲቱ ሞት ግን በዩናይትድ ኪንግደም በቀጣይ ቀናት በሚኖሩ የሕዝቡ የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ለውጥ ያመጣል።
ንግሥት ኤልዛቤጥ ከ11 አስከ 12 ቀናት ውስጥ በዌስትሚኒስቴር አቤይ ግብዓተ መሬታቸው ይፈጸማል ተብሎ ይጠበቃል። የቀብር ሥነ-ሥርዓቱ የሚፈጸምበት ቀንን የባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት ያስታውቃል።
አሁን ላይ ያለው ግምት ግን የንግሥቲቱ የቀብር ሥነ-ሥርዓት በሚፈጸምበት ዕለት ሥራ ዝግ ይሆናል። ይህም በባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት እና በአገሪቱ መንግሥት ይፋ ይደረጋል።
መንግሥት በዕለቱ ሥራ እንደማይኖር ካስታወቀ ትምህርት ቤቶችም ዝግ ይሆናሉ።
የሚሰረዙ ኩነቶች ይኖራሉ?
ዛሬ አርብ ጳጉሜ 04/2014 ዓ.ም. ለመካሄድ ቀጠሮ ተይዞላቸው የነበሩ አብዛኞቹ የእርግ ኳስ ጨዋታዎች ተሰርዘዋል።
በእንግሊዝ የእርግ ኳስ ሊግ እና በሰሜን አየርላንድ የእግር ኳስ ሊግ ዛሬ ሊደረጉ የነበሩ የእግር ኳስ ጨዋታዎች ተሰርዘዋል።
ከእግር ኳስ በተጨማሪ ዛሬ ሊካሄዱ የነበሩ የፈረስ ግልቢያ ውድድሮች፣ የጎልፍ ጨዋታዎች እና የብስክሌት ውድድሮች ተሰርዘዋል። እንግሊዝ እና ደቡብ አፍሪካ ሊያደርጉት የነበረው የክሪኬት ግጥሚያም ተሰርዟል።
የሥራ ማቆም አድርማ ጠርቶ የነበረው የባቡር፣ የባሕር እና ትራንስፖርት ሠራተኞች ማኅበር ለንግሥቲቱ ክብር ሲባል የተጠራው የሥራ ማቆም አድማን ተሰርዟል ብሏል።
በተመሳሳይ የኮሚዩኒኬሽን ማኅበር ጠርቶት የነበረው አድማም በተመሳሳይ ተሰርዟል።
ዛሬ አርብ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት ለንግሥቲቱ በቅዱስ ጳውሎስ ካቴድራል የመታሰቢያ ሥነ-ሥርዓት ይካሄዳል።
ንግሥቲቱ ስኮትላንድ ውስጥ በማረፋቸው አስክሬናቸው ኤደንብራ በሚገኘው ቅዱስ ጋሊስ ካቴድራል ይቆያል። ከዚያም ወደ ለንደን ተወስዶ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ በዌስትሚኒስቴር አዳራሽ በአካል ተገኝቶ አስክሬናቸውን በመሰናበት ያልፋል።
ዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤት ሕይወታቸው ካለፈ ከ24 ሰዓታት በኋላ ሰንደቅ ዓላማዎች ዳግም ከፍ ብለው ይውለበለባሉ።
ለንግሥት ኤልዛቤጥ ክብር ዌስትሚኒስትር አቤይ፣ ቅዱስ ጳውሎስ ካቴድራል እና ዊንድሰር ቤተ-መንግሥት የደውል ድምጽ ያሰማሉ።
እያንዳንዱን የዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤጥ የንግሥና ዓመታትን ለማሰብ 96 ጊዜ በሃይድ ፓርክ መድፍ ይተኮሳል።












