ቻርለስ ንጉሥ ሆኑ

ንጉሥ ቻርልስ

የፎቶው ባለመብት, © NADAV KANDER

የምስሉ መግለጫ, ንጉሥ ቻርልስ

የዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤጥ ሞትን ተከትሎ ንግሥናው ወደ ዌልሱ ልዑል ቻርለስ ተላልፏል።

ቻርልስ ንጉሥ ተብለው በይፋ እንዲሰየሙ የተለያዩ ዝርዝር ሥነ ሥርዓቶችን ማለፍ ይጠበቅባቸዋል።

መጠሪያ ስማቸው ማን ይሆናል?

ንጉሥ ቻርለስ ሦስተኛ ተብለው የሚጠሩ ይሆናል።

የመጠሪያ ስም መምረጥ የመጀመሪያው የንጉሥ ወይም ንግሥት ኃላፊነት ይሆናል። ቻርለስ ከአራቱ መጠሪያ ስማቸው ማለትም፤ ቻርለስ ፊሊፕ አርተር ጆርጅ አንዱን መምረጥ ይችላሉ።

የስም ለውጥ የሚያደርጉት ቻርልስ ብቻ አይደሉም። የቻርለስ ልጅ ልዑል ዊሊያም የአባታቸውን ስም በመውረስ የኮርንዌል አልጋ ወራሽ ይባላሉ። የልዑል ዊሊያም ባለቤት ካትሪን ደግሞ የኮርዌል ሶፋኒት ተብለው የሚጠሩ ይሆናል።

የንጉሡ ባለቤት ስም ላይም ለውጥ ይኖራል። የንጉሡ ባለቤት ንግሥት ኮንሶርት ተብለው ይጠራሉ። ኮርሶርት የንጉሥ ወይም ንግሥት ባለቤት የሚጠቀሙበት መጠሪያ ነበር።

በቀጣይ የሚኖረው ሥርዓት

ቻርልስ የእናታቸውን ሞት ተከትሎ በሚኖሩት 24 ሰዓታት ውስጥ በይፋ ንጉሥ ተብለው ይሰየማሉ።

ይህ የሚሆነው ለንደን በሚገኘው ቅዱስ ጄምስ ቤተ-መንግሥት ነው።

በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ እስከ 700 ሰዎች ሊታደሙ ይችላሉ ቢባልም፣ የታዳሚዎች ቁጥር ከዚህ በእጅጉ ያነሰ ሊሆን ይችላል።

እአአ 1952 ላይ የታዳሚዎች ቁጥር 200 አካባቢ ነበር።

ንጉሥ ቻርልስ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ, ንጉሥ ቻርልስ

አዲስ ንጉሥ መሠየም

አዲስ ንጉሥ ከመጣ በአብዛኛው ከአንድ ቀን በኋላ የሚሰበሰበው የንግሥና ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ንጉሡ ከሌሎች ጋር ተሳታፊ ይሆናል።

የብሪታኒያ ንጉሥ ወደ ሥልጣን ሲመጣ የቃለ መሐላ ሥነ ሥርዓት ማድረግ አይኖርበትም።

ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በነበረ ልማድ መሠረት በአዲሱ ንጉሥ አዋጅ ይነገራል፣ በዚህም ለስኮትላንድ ቤተክርስቲያን ታማኝነቱን ያረጋግጣል።

ከዚያም የተለየ ሥን ሥርዓት ከተደረገ በኋላ ለሕዝብ ይፋ በሚደረግ አዋጅ አማካይነት ቻርለስ አዲሱ ንጉሥ መሆናቸው ይፋ ይደረጋል።

ዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤጥ ልጃቸውን ቻርለስን በ1969 (እአአ) የዌልስ ልዑል አድርገው ዘውድ ሲደፉለት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤጥ ልጃቸውን ቻርለስን በ1969 (እአአ) የዌልስ ልዑል አድርገው ዘውድ ሲደፉለት

የንግሥና ሥነ ሥርዓት

ይህንንም ተከትሎ በሚካሄድ የንግሥና ሥነ ሥርዓት አማካይነት ቻርለስ በደንቡ መሠረት ዘውድ ይደፋሉ። ነገር ግን ይህ የንግሥና ሥነ ሥርዓት በሚያስፈልገው ዝግጅት ምክንያት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚካሄድ አይሆንም።

ላለፉት 900 ዓመታት የንግሥናው ሥነ ሥርዓት በዌስት ሚኒስቴር አቤይ ካቴድራል ሲካሄድ የቆየ ሲሆን፣ ንጉሥ ቻርለስም 40ኛው ንጉሥ በመሆን ይነግሳሉ።

ንግሥቲቱን በመተካት ቻርለስ ከሚረከቡት የዩናይትድ ኪንግደም ንጉሥ በተጨማሪ፣ የ56 ነጻ አገራት እና 2.4 ቢሊዮን ሕዝብ ያላቸው የኮመንዌልዝ አገራት ማኅበር የበላይ ይሆናሉ።