የዩናይትድ ኪንግደም የ70 ዓመታት ንግሥት ዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤጥ በ96 ዓመታቸው አረፉ

ንግሥት ኤልዛቤት ዳግማዊት 

የ96 ዓመቷ የዩናይትድ ኪንግደም እና የኮመን ዌልዝ አገራት ንግሥት ኤልዛቤት ዳግማዊት አረፉ።

ንግሥቲቱ ማረፋቸውን የባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት ይፋ አድርጓል።

ቀደም ሲል ሐኪሞች የንግሥቲቱ ጤና በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ ነው ብለው ነበር።

የንግሥቲቱ የጤና ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ተከትሎ በርካርታ የንጉሣውያን ቤተሰብ አባላት ንግሥቲቱ ወደሚገኙበት ስኮትላንድ ባልሞር ቤተ-መንግሥት አቅንተው ነበር።

ንግሥት ኤልዛቤት ዳግማዊት በ70 ዓመት የንግሥና ዘመናቸው በርካታ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ለውጦችን ተመልክተዋል።

የንግሥቲቱን የጤና አሳሳቢ መሆን ዜና ከተሰማ በኋላ በርካታ ፖለቲከኞች እና ተዋቂ ግለሰቦች በዜናው መረበሻቸውን ሲገልጹ ነበር።

ንግስት ኤልዛቤጥ ወደ ንግስናው የመጡት እአአ 1952 ነበር። ንግሥቷ በ70 ዓመታት የንግስና ዘመናቸው በዩኬ እና በመላው ዓለም ብዙ ማሕበራዊ ለውጦች ተከናውነዋል።

አዲስ ንጉስ

የንግሥት ኤልዛቤጥ ሞትን ተከትሎ የመጀመሪያ ልጃቸው ቻርልስ የዩናይትድ ኪንግደም እና የኮመንዌልዝ አገራት ንጉሥ ሆነዋል።

የቀድሞው የዌልስ ልዑል የአሁኑ የዩናይትድ ኪንግደም እና የ14 ኮመንዌልዝ መንግሥታት ንጉሥ የእናታቸው ሞት “ለእኔ እና ለመላው ቤተሰቤ ከፍተኛ ሐዘን ነው” ብለዋል።

“. . . የተወዳጇ እናቴ ሞት በመላው አገሪቱ ሐዘን እንደሚፈጥር እርግጠኛ ነኝ”ብለዋል።

የንግሥቲቱን ሞት ይፋ ያደረገው ባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት፤ “ንግሥቲቱ ዛሬ ከሰዓት በባልሞራል በሰላም አርፈዋል” ብሏል።

ንጉሥ ቻርልስን ጨምሮ የንጉሥውያን ቤተሰብ አባላት ዛሬ በባልሞራል ቆይተው ነገ ወደ መዲናዋ ለንደን እንደሚመለሱ ተገልጿል።

ሐኪሞች የንግሥቲቱ ጤና አሳሳቢ ሁኔታ ላይ መሆኑን ማስታወቃቸውን ተከትሎ የንግሥት ኤልዛቤጥ ልጆች በሙሉ ወደ ባለሞራል ተጉዘው ነበር።

ንግሥት ኤልዛቤጥ በንግሥና ሕይወታቸው ከዊንሰተን ቸርችል እስከ ሊዝ ትረስ ድረስ የ15 ጠቅላይ ሚንስትሮችን አስተዳደር አይተዋል።

የኤደንብራው መስፍን ባለቤታቸው ፊሊፕ ከ60 ዓመታት በላይ ከንግሥቲቱ ጎን ነበሩ

የፎቶው ባለመብት, TIM GRAHAM/PA

የምስሉ መግለጫ, ባለቤታቸው የኤደንብራው መስፍን ፊሊፕ ከ60 ዓመታት በላይ ከንግሥቲቱ ጎን ነበሩ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ንግሥቲቱ የመጀመሪያ ልጃቸውን ከልዑል ቻርለስ በ1948 (እአአ) ሲወልዱ፣ ከዚያም ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ልዕልት አንን ወልደዋል።

በ1960 ልዑል አንድሩን በ1964 ደግሞ ኤድዋርድን ወልደዋል። ከዚያም በኋላ ስምንት የልጅ ልጆችን እንደሁም 12 የልጅ ልጅ ልጆችን አይተዋል።

ልዕልት ኤልዛቤጥ በ1952 አባታቸው ሲያርፉ እሳቸው የታመሙትን ንጉሥ ፊሊፕን ወክለው ኬንያ ውስጥ የነበሩ ሲሆን፣ የአባታቸው ሞት እንደተሰማ ወዲያው ወደ ለንደን ተመልሰው ንግሥት በመሆን ዘውድ ደፉ።

ኤልዛቤጥ እንደ አውሮፓውያኑ ሰኔ 02/1953 በዌስት ሚኒስቴር አቤይ ንግሥናውን ሲቀበሉ 27 ዓመታቸው የነበረ ሲሆን፣ 20 ሚሊዮን ሕዝብ ሥነ ሥርዓቱን በቴሌቪዥን ተከታትሎታል።

ንግሥቲቱ ወደ ዙፋን ከወጡ በኋላ በነበሩት አስርት ዓመታት በባሕር ማዶ ያለው የብሪታኒያ ዘውዳዊ ግዛት ማብቃትና በአገር ውስጥም ከፍተኛ ለውጦች ተከስተዋል።

ንግሥቲቱ ዘውዳዊው ሥርዓት ላይ ለውጦችን ያመጡ ሲሆን፣ ሕዝባዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ በመታደም እና በተለያዩ ተግባራት ላይ በመሳተፍ ከሕዝብ ጋር የቀረበ ግንኙነትን ፈጥረዋል።

ከኮመንዌልዝ አገራት ጋር ጠንካራና መደበኛ ትስስር ለመፍጠር የተጉት ንግሥቲቱ፣ አባል አገራቱን ቢያንስ አንድ ጊዜ ጎብኝተዋል።

በንግሥና ዘመናቸው ንግሥቲቱ የግልና አገራዊ ችግሮችንም ተጋፍጠዋል። በአውሮፓውያኑ በ1992 የደረሰ የእሳት አደጋ የግል መኖሪያቸው እና ቤተመንግሥታቸው የሆነውን የዊንድሶርን ሲያወድም፣ የሦስት ልጆቻቸው ትዳርም ፈርሷል።

የዌልሷ ልዕልት ዲያና ፓሪስ ውስጥ ባጋጠማት የመኪና አደጋ ሕይወቷ ሲያልፍ፣ በይፋ ስለተከሰተው ነገር በሕዝብ ፊት ምላሽ ለመስጠት ቸልተኛ ሆነዋል በሚል ሕዝባዊ ትችትም ገጥሟቸው ነበር።

በዚህ ዘመናዊ ማኅበረሰብ ውስጥ ንግሥቲቷ የሚመሩት ዘውዳዊ ሥርዓት አስፈላጊነትንም በተመለከተ ጥያቄዎች ይነሳሉ።

“የትኛውም ተቋም ታማኝነታቸውን እና ድጋፋቸውን ከሰጡት ብቻ ሳይሆን ከሚቃወሙትም ጭምር ከሚሰጥ ትችትና ቁጥጥር ነጻ ሆኖ ሊቆይ ይችላል ተብሎ አይጠበቅም” ሲሉ ለቀረቡ ትችቶች እውቅና ሰጥተዋል።