ጀርመን የቻድ አምባሳደር በ48 ሰዓት ከአገር እንዲወጡ አዘዘች

መሪያም አሊ ሙሳ

የፎቶው ባለመብት, Embassy of Chad in Berlin

የምስሉ መግለጫ, መሪያም አሊ ሙሳ ከእአአ 2018 ጀምሮ በጀርመን የቻርድ አምባሳደር ሆነው ቆይተዋል።

አፍሪካዊቷ አገር ቻድ ባለፈው ሳምንት የጀርመን አምባሳደርን ማባረሯን ተከትሎ ጀርመንም በአጸፋው የቻድ አምባሳደር በ48 ሰዓታት ከአገር እንዲወጡ አዘዘች።

የጀርመን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ትላንት ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ የቻድ አምባሳደር ማሪየም አሊ ሙሳ በ48 ሰዓት ውስጥ ከጀርመን ለቀው መውጣት አለባቸው ብሏል።

“ጉዳዩ እዚህ ደረጃ በመድረሱ አሳዝኖናል” ሲል የጀርመን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በትዊተር ገጹ አስፍሯል።

በቻድ የጀርመን አምባሳደር ጃን ክርስቲያን ጎርደን ወታደራዊው መንግሥት ከቻድ ካባረራቸው በኋላ ባለፈው ዕሁድ አገሪቱን ለቀው ወጥተዋል።

ቻድ አምባሳደሩ “ቀናነት የጎደለው አመለካከት አላቸው" እንዲሁም “ለዲፕሎማሲያዊ ልምድ ክብር የላቸውም” በሚል ከአገር መባረራቸውን አስታውቃ ነበር።

አጠር ያለው የቻድ መንግሥት መግለጫ ይህንን ከማለት በስተቀር አምባሳደሩ የተባረሩበትን ምክንያት በዝርዝር አላስቀመጠም።

የጀርመን ባለስልጣናትም ቻድ አምባሳደሩን ያባረረችበትን ምክንያት እንዳልገለጸች አስታውቃለች።

“አምባሳደሩ በንጃሚና [የቻድ ዋና ከተማ] አርአያ በሚሆን መንገድ ስራቸው እየሰሩ ነበር። በቻድ ለሰብዓዊ መብት መከበርና ለፈጣን የሲቪል መንግሥት ሽግግር ሰርተዋል” ሲል የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2021 በቻድ ስልጣን ላይ የነበሩት ኢዲሪስ ዴቢይ ኢንቶ መገደላቸውን ተከትሎ ልጃቸው ጀነራል ማሃማት ኢዲሪስ ዴቢይ ስልጣን ላይ ወጥተዋል።

በአባታቸው የተተኩት ጀነራል በአገሪቱ ምርጫ እስኪካሄድ ጊዜያዊ መሪ ሆነው ለ18 ወራት አገር ያስተዳድራሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም ቻድ አሁንም በወታደራዊ አስተዳደር ስር ትገኛለች።

በአገሪቱ ሊካሄድ የነበረው ምርጫ እንዲዘገይ መደረጉ ሕዝባዊ ተቃውሞን አስከትሏል። የቻድ ወታደራዊ መንግሥት በሚቀጥለው ዓመት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የማድረግ ዕቅድ አለኝ ብሏል።