የዩናይትድ ኪንግደም ፓውንድ የመግዛት አቅም ከዶላር አንጻር ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ዝቅ አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከአውሮፓውያኑ 1971 በኋላ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የዩናይትድ ኪንግደም ፓወንድ ከአሜሪካ ዶላር ጋር ሲነጻጸር ያለው ዋጋ ማሽቆልቆሉ ተነገረ።
ፓውንድ ስተርሊንግ በእስያ ገበያ ያለው የመግዛት አቅም በ4 በመቶ የወረደ ሲሆን አንዱ ፓውንድ ዋጋ ቀደም ሲል ከነበረው ከ1.05 ወደ 1.0327 ዶላር ዝቅ ብሏል።
ይህ የተሰማው የዩናይትድ ኪንግደም ቻንስለር ካዋሲ ከዋርቴነግ በከፍተኛ የብድር ድጋፍ የታገዘ ታሪካዊ የታክስ ቅነሳን ይፋ ካደረጉ በኋላ ነው።
በአሜሪካ ማዕከላዊ ባንክ እየተደረገ ያለው ዶላርን የማጠናከር እና የወለድ ምጣኔ ጭማሪ የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ፓወንድ ከዶላር አንጻር ያለው የመግዛት አቅም ጫና ውስጥ እንዲገባ ምክንያት ሆኗል።
በተጨማሪም ከዶላር አንጻር የዩሮ የመግዛት አቅም ከ20 ዓመት ወዲህ በእስያ ገበያ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ዝቅ ብሏል።
ይህም በዩክሬን የተቀሰቀሰው ጦርነት ያስከተለው የነዳጅ ቀውስ መቼ እንደሚፈታ ምልክት አለማሰየቱ ባለሃብቶችን አሳስቧል ተብሏል።
በአሁኑ ወቅት ሁሉም የመገበያያ ገንዘብ አይንቶች ከዶላር አንጻር ያላቸው አቅም እየተዳከመ ነው። ስለዚህ የአሜሪካ ዶላር ከፍተኛ ጥንካሬ እያሳየ ነው።
ፓውንድን በታክስ ቅነሳ ለመደፍ መታሰቡ ማሽቆልቆሉን እንዲባባስ ያደርገዋል ሲሉ የአንድ የንግድ ተቋም ተባባሪ መስራች የሆኑት ፒተር ኢስኮ ተናግረዋል።
“የኃይል አቅርቦት ላይ በቅርቡ የተደረገው ድጎማ እና የዩኬ ባንክ የአደጋ ጊዜ የዋጋ ጭማሪ ሊኖር እንደሚችል የሚጠቁመው ዜና የፍርሃት ምልክት ነው” ሲሉም አክለዋል።
ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ የፌደራል ጠባባቂያ እና የዩኬ ባንክን ጨምሮ የበርካታ አገራት ማዕከላዊ ባንኮች የዋጋ ጭማሪን ለመከላከል የወሰዱት የወለድ ምጣኔን የመጨመር እርምጃ የዓለም ገበያን እንዲቀዘቅዝ አድርጓል።
ፓውንደ ከዶላር በታች ሀኖ የሚቆይ ከሆነ ጋዝ እና ነዳጅ ዘይትን ጨምሮ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች ዋጋ አሁን ካለው በላይ ሊወደደዱ ይቸላሉ።
ከአሜሪካ ወደ ዩኬ የሚገቡ ሌሎች ምርቶችም ሊወደዱ እንደሚችሉ የሚጠበቅ ሲሆን በበአላት ወደ አሜሪካ የሚጓዙ የብርታኒያ ቱሪስቶች ቁጥር ከዚህ ቀደም ከነበረው ሊወርድ ይችላል ተብሏል።












