በዚህ የሞባይል ዘመን ለልጆቻችን ስልክ መስጠት ያለብን መቼ ነው?

ሞባይል የያዘች ሕጻን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሕይወት ስንክሳር ስልክ ውስጥ ገባ፤ ቡራኬዋም እንዲሁ።

በዚህ ዘመን ያለ ስልክ እስትንፋስ የለም።

የወላጅ አንዱ ጭንቅ ከዚህ ይመነጫል።

መቼና በየትኛው ዕድሜ ለልጆች ስልክ ይሰጥ የሚለው ‘የሚሊዮን ዶላር’ ጥያቄ ነው።

በሁለቱም ወገን ሙግቶቹ ቀጥለዋል።

አንዱ ወገን ልጆች ዘመናቸውን መምሰል ነው ያለባቸው። መረጃ የሚቃርሙት በስልክ ነው። ስለዚህ መነካካት እስከቻሉ ድረስ ይጠቀሙ፤ ይበርብሩ ይላል።

ሌላኛው ‘የለም፤ የለም፤ አደጋው ይከፋል፣ መርገምቱ ይሰፋል’ ይላል።

ስልክና ልጆች ሲገናኙ ፈረንጆቹ ‘ፓንዶራ ቦክስ’ ተከፈተ የሚሉት ዓይነት ሁኔታ ይፈጠራል።

ስልክ ውስጥ ሴጣንም መልአክም አለ።

ብዙ ምርምሮች ልጆች ከስልክ ጋር መጣበቃቸው ከሰውነት አውጥቶ ማሽን አምላኪ ያደረጋቸዋል ይላሉ።

ሌሎች ምርምሮች ደግሞ አእምሯቸው ስል ይሆናል ይላሉ። ታዲያ እኛ የቱን እንቀበል?

ይህ ነገር ድሃና ሃብታም አይልም። የልጅ ነገር የሁሉም ጭንቅ ነው።

የሆሊውድ ዝነኞች ሳይቀሩ ነገሩ ግራ ሆኖባቸዋል። ማዶና በቅርቡ እንዳመነችው ከሚጸጽቷት ነገሮች አንዱ ለልጆቿ በ13 ዓመታቸው ስልክ መስጠቷ ነበር።

ሌላው ፈተና ደግሞ ወዲህ ነው።

ለምሳሌ እርስዎ እንደ ወላጅ በስልክ ይገበያያሉ፣ የቤተሰብ አልበምዎ በስልክዎ ይሰንዳሉ፣ ሥራ ይሠራሉ፣ ከጓደኞችዎ ጋር ያወራሉ፣ ትውስታን ይጋራሉ. . . ወዘተ።

ይህንን ልጆች ያስተውላሉ።

ስለሚያስተውሉም ማድረግን ይሻሉ? ሲከለከሉ ግን ግራ ይገባቸዋል።

ትምህርት ቤት ሲሄዱ ምናልባት አብዛኛዎቹ ጓደኞቻቸው ስልክ ይዘው ይመለከታሉ።

የእርስዎ ልጆች ብቻ ስልክ የላቸውም። ይህ አእምሯቸው ላይ ምን ሊፈጥር እንደሚችል ማሰብ ነው እንግዲህ።

እስኪ ጥቂቶቹን በዚህ ረገድ የተደረጉ ጥናቶችን እንመልከት።

ልጆች ስልክ በመያዛቸው ብቻ ጉዳት ይደርስባቸዋል የሚል ጥናት የለም።

ይህ ግን የነገሩን ሙሉ ገጽታ አይወክልም።

አንዳንድ ጥናቶች ልጆች አእምሯቸው ሳይጠና ስልክ ባይጎረጉሩ ይመክራሉ።

ይህ ዕድሜ ግን ከልጅ ልጅ ይለያያል፤ ከአካባቢ አካባቢ፤ ከማኅበረሰብ ማኅበረሰብ ይለያያል።

ሞባይል ይዞ መጽሐፍ የሚያነብ ታዳጊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጥናቶች ምን ያሳያሉ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ለምሳሌ 91 ከመቶ የሚሆኑት ልጆች በ9 ዓመታቸው ስልክ ይይዛሉ።

በአውሮፓ አገራት በተደረገ ጥናት 80 ከመቶ የሚሆኑ ልጆች ከ9 እስከ 16 ዕድሜ ድረስ የግል ስልክ ባለቤት ይሆናሉ። ይህ በ19 አውሮፓ አገራት የተደረገ ጥናት ነው።

በአሜሪካ ደግሞ 37 ከመቶ የሚሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው 9 ዓመት ሲሞላቸው ስልክ ገዝተው ይሰጧቸዋል።

በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ የተደረጉ ብዙ ጥናቶች ባይኖሩም ያሉት ጥናቶች ግን በልጆች የአእምሮ ጤናና ስልክ በመያዛቸው መካከል አደጋ እንዳለ አላሳየም።

ይሁንና ጥናቶች ጥቅል ሁኔታን ብቻ ነው ማስረዳት የሚችሉት። የነገሩ ጣጣ ከልጅ ልጅ ይለያያል።

አሚ ኦርበን የተባሉ የካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ የልጆች ሥነ አእምሮ ተመራማሪ እንደሚሉት ልጆች በትክክል ስልክና ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀማቸው ጉዳት እንዳመጣባቸው ማስተዋል የሚችለው ውሎና አዳራቸውን የሚያውቅ ወላጅ ብቻ ነው ይላሉ።

ለአንዳንድ ልጆች ስልክ የዕውቀት በር ሆኖ ያገለግላቸዋል።

ዓለምን ያስቃኛቸዋል።

ከወላጅና ከመምህራን ያላገኙትን መረጃ ያጋራቸዋል። አእምሯቸው ብዙ እንዲገረም ብዙ እንዲያስስ ያደርጋቸዋል።

ይህ የስልክ በረከት ሆኖ የሚታይ ነው።

አሁንም ግን ነገሩ በረከት ብቻ ሆኖ እንዲቀጥል የወላጅ የቅርብ ክትትል ከምንም በላይ ወሳኝ ነው።

የስልክ መርገምት ተብሎ የሚነሳው አንዱ ነጥብ ደግሞ፣ ከሰው ጋር ያለንን ግንኙነት ገድቦታል የሚል ነው።

ይህ ግን ጥናቶች እንዳስረዱት ከልጆች ይልቅ በአዋቂዎች ላይ የሚስተዋል ነው።

በዴንማርክ የተደረገ አንድ ጥናት ዕድሜያቸው ከ11 እስከ 15 የሆኑ ልጆች ስልክ በመያዛቸው ለወላጆቻቸው መረጋጋትን ሰጥቶ፣ ልጆችም ሄደውባቸው የማያውቁባቸውን ቦታዎች ደፍረው እንዲሁ እንዳበረታታቸው አሳይቷል።

ይህም የሆነው እነዚህ ልጆች ስልክ በመያዛቸውና አንዳች ነገር ቢከሰት ከወላጆቻቸው ጋር በቀላሉ መገናኘት በመቻላቸው የመጣ ትሩፋት ነው።

ይሁንና ይህ የታሪክ ሽራፊ ገጽታ ነው።

ፕሮፌሰር ኦርበን እንደሚሉት ስልክ የሚይዙ ልጆችና ማኅበራዊ ሚዲያውን ዘወትር ስለሚያስሱ ሁልጊዜም አንድ የጎደላቸው ነገር እንዳለ ይሰማቸዋል።

“ሁሉም እኩዮቻቸው መሆን የሚፈልጉት፣ መገኘት የሚፈልጉበት፣ መምሰል ያለባቸው የሚመስላቸው፣ መልበስ የሚገባቸው ሆኖ የሚሰማቸው አንዳች ነገር አለ፤ ያ ነገር የትኛውም ነገር ሊሆን ይችላል፤ ስልክ ያን እንዲሆኑ ይገፋቸዋል።”

የዚህ ችግር ደግሞ ልጆች ሁልጊዜም ጎዶሎነት እንዲሰማቸው ማድረጉ ነው።

ይህ ልጆች ላይ የሚስተዋል ስሜት በጥናት የተደገፈ ነው።

በሞባይል ፎቶ የሚነሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ማኅበራዊ ሚዲያ እና ልጆች

ልጆች በየትኛው ዕድሜ ላይ ምን ይሰማቸዋል በሚል በተደረገ አንድ ሰፊ ጥናት 17ሺህ የሚሆኑ አዳጊዎች እና ወጣቶች (ዕድሜያቸው ከ10 - 21 የሆኑ) ተካተዋል።

በውጤቱም ሴቶች ከ11 - 13 ወንዶች ደግሞ ከ14 - 15 ዓመት ያሉት በተለይ ማኅበራዊ ሚዲያን መጠቀም በጀመሩ በዓመቱ ከፍተኛ እርካታ የማጣት ስሜት ተስተውሎባቸዋል።

የሚገርመው ደግሞ ስልክና ማኅበራዊ ሚዲያ ባልተጠቀሙት ላይ የእርካታና እፎይታ ስሜት መታየቱ ነው።

በአሥራዎቹ የሚገኙ አዳጊዎች ሁልጊዜም ቢሆን ሌላው ስለነርሱ ምን እንደሚያስብ ያስጨንቃቸዋል።

ማኅበራዊ ሚዲያ ደግሞ ሰዎች በግላጭ ፍቅርና ጥላቻቸውን የሚረጩበት መድረክ ነው። አዳጊዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተጽእኖ ውስጥ የሚወድቁትም ለዚሁ ነው።

እርካታ ጥሏቸው ይበናል። ለምን ቢባል ሁሌም የሆነ የሚበልጣቸው እኩያቸው በማኀበራዊ ሚዲያ አለ። ያ ደስታቸውን ይቀማቸዋል።

በአጠቃላይ በርካታ ጥናቶች በዚህ ዘርፍ ቢደረጉም አንዳቸውም የትኛው ዕድሜ ነው ለልጆች ስልክ ሊገዛላቸው የሚገባው የሚለውን በትክክል መመለስ አልቻሉም።

ፕሮፌሰር ኦርበን እንደሚሉት፣ ነገሮች በዚህ ዘመን ውስብስብ ስለሆኑ ቀላል መልስ መስጠት አይቻልም፤ እንዲያውም ይህን ቁልፍ ጥያቄ መመለስ ያለባቸው ከተመራማሪዎች ይልቅ ወላጆች ናቸው ይላሉ።

ለአንዳንድ ቤተሰብ ስልክ መስጠት ልጁን በቅርብ ለመቆጣጠር፣ ልጁም በራሱ እንዲያምን ለማበረታታት ጠቃሚ ሆኖ ይታየዋል።

ለሌሎች ደግሞ ቀደም ብለን እንዳነሳነው የልጁን ሕይወት የመቀማት ያህል ይታያል።

አንዱ ፈተና በስልክ ውስጥ ያለ ይዘት፣ ልጆች ማየት ያለባቸውንና የሌለባቸውን ነገር ለመቆጣጠር እንደሚታሰበው ቀላል አለመሆኑ ነው።

ባለሙያዎች አንዱ የሚመክሩት ወላጆች ራሳቸው በእርግጥ ልጆቻቸው ስልክ ቢይዙ ምን ያህል ምቾት ይሰማቸዋል የሚለውን እንዲመረምሩ ነው።

ምን ያህልስ በልጆቻቸው ይተማመናሉ?

ሌላው መሠረታዊ ጥያቄ ልጆች ብቻ ሳይሆን ወላጆች ራሳቸው የስልክ አጠቃቀማቸው ምን ይመስላል?

ለምሳሌ ብዙ ልጆች መመከርን ይጠላሉ። ብዙ ልጆች ግብዝነት ከምንም በላይ ያበሳጫቸዋል።

በስልክ ተደፍተው የሚውሉ ወላጆቻቸው ስልክ ሲቀሟቸው ልጆች ብስጭት ውስጥ የሚገቡትም ለዚያ ነው። “ማሚ! ራስሽ ፌስቡክ እያየሽ አይደል፤ ያላየሁሽ መሰለሽ?” ብለው ቅሬታ ውስጥ ይገባሉ።

ይህ በወላጅና በልጅ መካከል የላላ መተማመንን ይፈጥራል፤ አለመተማመኑ ደግሞ ልጆች የሚያደርጉትን ነገር መደበቅ እንዳለባቸው እንዲሰማቸው ያደርጋል።

ሌላው ባለሙያዎች የሚመክሩት ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የሚያጠፉትን ጊዜ በተቻለ አቅም እንዲጨምሩ ነው።

ለምሳሌ በስልክ አጠቃቀም ጊዜ እንኳን ከስልኩ አጠገብ አብረዋቸው እንዲጫወቱ ማድረግ ብልህነት ነው።

በስልኩ ውስጥ የሚኖር መተግበሪያና ጌም ብዛትና ዓይነትም ከልጆች ጋር በመመካከር መከታተል ይጠቅማል።

እንዲያውም የልጆች ሥነ ልቦና አዋቂዎች እንደሚሉት ወላጆች አንዳንድ ጌሞችን አብረው ከልጆቻቸው ቢጫወቱ የበለጠ የልጆችን ሥነ ልቦና በቅርብ ለመከታተል ይረዳቸዋል።

ከልጆች ጋር በቅርብ በተነጋገርን ቁጥር ልብ ለልብ እንገናኛለን። ስልክ የምንሰጣቸው ልጆቻችን እንዳይረብሹን ከሆነ ግን እኛ ወላጆች ለጊዜው ሰላም እናገኝ ይሆናል፤ ልጆቻችን ግን ሰላማቸው ጠፍቶ፣ ሥነ ልቦናቸው ተቃውሶ ይጠብቀናል።