ኔቬስ፣ ቤንዜማ፣ ሜንዲ. . . የሳዑዲ ፕሮ ሊግ የአውሮፓ ከዋክብትን የሚያስፈርመው ለምንድነው?

የፎቶው ባለመብት, AL-ITTIHAD
ጋሪ ኔቪል ፕሪሚዬር ሊጉ ተጫዋቾች ወደ ሳዑዲ እንዳይሄዱ ሊያግድ ይገባል ቢልም ይህ የሚሆን አይመስልም።
ባፈለው አርብ የ26 ዓመቱ የዎልቭስ አምበል ሩበን ኔቬስ በ47 ሚሊዮን ፓውንድ አል-ሂላል ገብቷል።
የቼልሲው ግብ ጠባቂ ኤድዋርዶ ሜንዲ ደግሞ ሌላኛው ትልቅ ስም ያለው ከአውሮፓ ወደ ሳዑዲ ሊያቀና እንደሆነ የታማ ተጫዋች ነው።
ጫማ መስቀያቸው ሩቅ ያልሆነው ክሪስቲያኖ ሮናልዶ፣ ካሪም ቤንዜማ እና ንጎሎ ካንቴ ፈርመዋል። ሊዮኔል ሜሲም ወደ ሳዑዲ ያቀናል ሲባል ነው ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ያመራው።
የቼልሲዎቹ ካሊዱ ኩሊባሊ፣ ሐኪም ዚዬሽ እና የአርሰናሉ ቶማስ ፓርቴም ሳዑዲ ይገባሉ ተብለው ይታማሉ።
የሳዑዲ ሊግ ከዓለም አምስት ትላልቅ ሊጎች አንዱ ለመሆን አቅዷል።
የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድና የእንግሊዝ ተከላካይ ጋሪ ኔቪል ይህ ነገር ካሳሰባቸው መካከል አንዱ ነው።
ኒውካስልን የገዛው የሳዑዲ አራቢያ ፐብሊክ ኢንቨስትመንት ፈንድ በወርሃ ሰኔ የክሪስቲያኖ ሮናልዶን አል-ናሲር ጨምሮ ሌሎች አራት ክለቦችን እንደሚያስተዳድር ይፋ አድርጓል።
ይህ ፈንድ የቼልሲ አክሲዮን ማሕበር አባል ነው የሚባል ሐሜት ቢኖርም የክለቡ ባለቤቶች ግን ይህን ያስተባብላሉ።
“ፕሪሚዬር ሊጉ ለጨዋታው ክብር ሲል ተጫዋቾች ወደ ሳዑዲ እንዳይጓዙ ለጊዜው እግድ መጣል አለበት” ሲል ኔቪል ለቢቢሲ ስፖርት ሐሳቡን ሰጥቷል።
“ዝውውር ሐቀኛ ነው ወይ የሚለው መጣራት አለበት። ተጣርቶ ንፁህ ከሆነ ይቀጥል። የቼልሲ ባለቤት ማን እንደሆነ በደንብ ሳይጣራ የሚካሄድ ዝውውር ትክክል አይደለም።”
የገንዘብ ጉዳይ
ቼልሲና ዎልቭስ በያዝነው የክረምት የዝውውር መስኮት ፈተና ይገጥማቸዋል ተብሎ ተጠብቆ የነበረው በፕሪሚዬር ሊጉ የገንዘብ ፍትሐዊ አጠቃቀም [ፋይናንሻል ፌር ፕለይ] ምክንያት ነው።
ቼልሲ ባለፈው የውድድር ዘመን ለዝውውር 400 ሚሊዮን ፓውንድ አውጥቷል። ዎልቭስ ደግሞ ባለፈው ዓመት 46.1 ሚሊዮን ፓውንድ ኪሳራ ገጥሞኛል ብሏል።
ዎልቭስ ፖርቹጋላዊውን አማካይ ለባርሴሎና ሊሸጥ ነው የሚል ዜና እየተነዛ ነው ተጫዋቹ በ47 ሚሊዮን ፓውንድ ወደ አል-ሂላል ያቀናው።
የቼልሲ ሰዎች እንደሚሉት የሳዑዲ አራቢያው ፐብሊክ ፈንድ ከክለቡ ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ የለውም።
የቼልሲ ባለቤት የሆነው የአሜሪካው ክሊርሌክ ድርጅት ከስድስት ሃገራት የተውጣጡ 400 ኢንቨስተሮች እንዳሉት ይነገራል።
ድርጅቱ እንደሚለው የትኛውም ኢንቨስተር ከ5 በመቶ በላይ አክሲዮን መግዛት አይችልም።
እርግጥ ነው የአውሮፓ እግር ኳስ ማሕበር አንድ ክለብ በለተያዩ ባለቤቶችን መያዙን አያወግዝም። ዋናው ጉዳይ የክለብ ባለቤቶች ሕጉን ተከትለው ሁሉን ነገር ማስኬድ አለባቸው የሚለው ነው።
የሳዑዲ ሊግ ደረጃ
ሳዑዲ አራቢያ ሁሌም ለእግር ኳስ መልካም ሥፍራ ናት። ያላት ሊግም ተፎካካሪ የሚባል ነው።
ብሔራዊ ቡድኑ ካለፉት ስምንት የዓለም ዋንጫ ውድድሮች በስድስቱ ተካፋይ ነበር። ከጃፓን ቀጥሎ ሶስት ጊዜ የእስያ ዋንጫን በማንሳት ሁለተኛው ቡድን ነው።
ካታር በነበረው የዓለም ዋንጫ የተሳተፈው ብሔራዊ ቡድን 26ቱም ተጫዋቾች ሃገር ቤት ላሉ ክለቦች የሚጫወቱ ናቸው።
የሳዑዲው አል-ሂላል አራት ጊዜ የእስያ ቻምፒዮንስ ሊግን በማሸነፍ ክብረ-ወሰን ጨብጧል።
ሳዑዲ ከእግር ኳስ ባለፈ እንደ ፎርሙላ 1 እና የጎልፍ ውድድር በማዘጋጀት ለስፖርት አመቺ ቦታ መሆኗን እያስመሰከረች ትገኛለች።
የሳዑዲው ፈንድ ውዝግብ ሳይለየው ኒውካስልን ንብረቱ ማድረጉ ሳዑዲን ለማስተዋወቅ ትልቅ ጥቅም አለው።
ከዚህ ባለፈ ሳዑዲ፣ ግብፅና ግሪክ በ2030 የዓለም ዋንጫ ለማሳናዳት እንዳሰቡ ገልጠዋል።
ትላልቅ ስም ያላቸውን ተጫዋቾች ወደ ሳዑዲ ሊግ ማምጣት የዚህ ሕልም አንዱ አካል ይመስላል።
ሄልደር ኮስታ፣ ኤቨር ባኔጋ እና ኦዲዮን ኢጋሎ ከክሪስቲያኖ ሮናልዶ በፊት በሳዑዲው ሊግ መጫወት የጀመሩ የቀድሞ የአውሮፓ ከዋክብት ናቸው።
የዎልቭስና የቶተንሃም አሠልጣኝ የነበሩት ኑኖ ኤስፒሪቶ ሳንቶ አል-ኢቲሃድን ይዘው የሊጉን ዋንጫ አንስተዋል።
እርግጥ በአንድ ሰሞን የቻይናው ሱፐር ሊግ በተመሳሳይ ከፍተኛ ደመወዝ በመክፈል እነ ቴቬዝን ወስዶ ነበር፤ ግን ብዙም አልዘለቀም።
የሳዑዲ ሊግ መሠረቱ ጠንካራ እንደሆነ ያምናል።
አውሮፓ ተጨንቃ ይሆን?
ከዋክብት ወደ ሳዑዲ ማቅናታቸው ለአውሮፓ እግር ኳስ የራስ ምታት መሆኑ እሙን ነው።
እርግጥ ነው ተጫዋቾች ወደ ቻይና ሊግና ወደ አሜሪካው ሜጀር ሊግ ሶከር አምርተው ያውቃሉ።
ነገር ግን እንደ ኔቬስ ያሉ ገና በቁንጮ የመጫወቻ ዕድሜያቸው የሚገኙ ተጫዋች ወደ ሳዑዲ ማምራት ለአውሮፓ እግር ኳስ አሳሳቢ ነው።
አንደሚታማው ተጫዋቾች ለረብጣ ዶላር ከሆነ ወደ ሳዑዲ የሚያመሩት የአውሮፓ ክለቦች ይህን እንዴት ይቋቋማሉ?
በአውሮፓ እግር ኳስ የትኛውም ክለብ ምን ያህል ቱጃር ቢሆን እንደፈቀደ ደመወዝ አይከፍልም።
የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ጉዳይስ? ተወዳጁ ውድድር ከዋክብቱን ማጣት ከጀመረ ከአውሮፓ ውጭ ያሉ ክለቦችን ያሳትፍ ይሆን?
የዩኤፋ ፕሬዝደንት አሌክሳንደር ሴፌሪን በዚህ አይስማሙም።
“የሳዑዲ አራቢያ እግር ኳስ ስህተት እየሠራ ነው። መዋዕለ ነዋይ ማፈሰስ ያለባቸው አካደሚዎች እንጂ ጫማ ሊሰቅሉ የተቃረቡ ተጫዋቾችን ማጋዝ ለእግር ኳስ ዕድገት ጠር ነው። ቻይና የሠራችው ተመሳሳይ ስህተት እየተደገመ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
“ጉዳዩ የገንዘብ ብቻ አይደለም። ተጫዋቾች ውድድሮችን ማሸነፍ ይሻሉ። ትልቁ ውድድር ያለው ደግሞ አውሮፓ ነው።”












