ሮናልዶ፡ “የሳዑዲ ሊግ ከዓለማችን 5 ታላልቅ ሊጎች አንዱ ሊሆን ይችላል”

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፖርቹጋላዊው የእግር ኳስ ኮከብ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ የሳዑዲ ሊግ ከዓለማችን “አምስት ታላልቅ ሊጎች አንዱ” መሆን ይችላል አለ።
ሮናልዶ እንደሚለው ሊጉ ትልት ስም ያላቸውን ተጫዋቾች ማምጣት ከቻለ ከመመንደግ የሚያግደው የለም።
ሊዮኔል ሜሲ፣ ካሪም ቤንዜማ እና ሉካ ሞድሪች ስማቸው ከሳዑዲ ሊግ ጋር እየተያያዘ ነው።
የ38 ዓመቱ ሮናልዶ ሁሉም ቢመጡ ደስተኛ እንደሆነ ገልጧል።
አምስት ጊዜ የዓለም ኮከብ ተብሎ ባለን ደኦር የተሸለመው ሮናልዶ፤ የውድድር ዘመኑን ከሳዑዲው አል ናስር ጋር ጨርሷል።
የሮናልዶ ፊርማ እንደሚያሳየው ተጫዋቹ እስከ 2025 ድረስ በሳዑዲ የሚቆይ ይሆናል።
አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ የፈረንሳዩን ፓሪስ ሴይንት ጀርሜይን ቡድኑን እንደለቀቀ ይፋ አድርጓል።
የ35 ዓመቱ የፊት መስመር ተጫዋች ለሳዑዲ አራቢያ የቱሪዝም አምባሳደር ሆኖ ያገለግላል።
የሮናልዶ የቀድሞ የቡድን አጋሮች ካሪም ቤንዜማና ሉካ ሞድሪች ጫማ ከመስቀላቸው በፊት ወደ ሳዑዲ ሊግ ማቅናት እንደሚፈልጉ እየተሰማ ነው።
“ትልቅ ስም ያላቸው ትልቅ ተጫዋቾች ከመጡ፤ ወጣቶችም ከመጡ በደስታ ነው የምንቀበላቸው። ምክንያቱም እነሱ መጡ ማለት ሊጉ ያድጋል ማለት ነው” ብሏል ሮናልዶ ለፒኤስኤል በሰጠው ቃል።
“ሊጉ በጣም አሪፍ ነው ነገር ግን ለማደግ ብዙ ዕድሎች አሉን ብዬ አስባለሁ። ፉክክሩ ከፍ ያለው። በጣም አሪፍ ተጫዎቾች አሉን። በጣም አሪፍ አረብ ተጫዋቾች።”
ነገር ግን ይላል ሮናልዶ “ነገር ግን መሠረተ ልማቱ ትንሽ መሻሻል አለበት። ዳኛዎችም ቢሆን። ቪኤአር ትንሽ ፈጠን ማለት አለበት።”
ሮናልዶ፤ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ለሁለተኛው ጊዜ የገባው ውል በሁለቱ ስምምነት መሠረት ባለፈው ኅዳር መፍረሱ አይዘነጋም።
ፖርቹጋላዊው አጥቂ በአምስት የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ጎል ያስቆጠረ ብቸኛው ተጫዋች ነው።
ሮናልዶ ከዓለም ዋንጫው በኋላ ወደ ሳዑዲ ሊግ በማቅናት በ16 ጨዋታዎች 14 ጎሎች ማስቆጠር ችሏል።
መቀመጫውን ሪያድ ያደረገው አል ናስር ከቻምፒዮኖቹ አል ሂላል ቀጥሎ ሁለተኛ ሆነው ጨርሰዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በጎል ቁጥርና ለብሔራዊ ቡድን በመሰለፍ ክብረ-ወሰን የጨበጠው ሮናልዶ፤ የሳዑዲ ሊግ “ትንሽ መሻሻል” ያሻዋል ይላል።
“ነገር ግን እኔ እዚህ ደስተኛ ነኝ። መቀጠል እፈልጋለሁ። እቀጥላለሁም። በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት መሥራት የሚፈልጉትን ነገር ከሠሩ የሳዑዲ ሊግ ከዓለማችን አምስት ቀንደኛ ሊጎች አንዱ ይሆናል።”












