ባለፉት ወራት በእግር ኳሱ ዓለም ከታዩ አነጋጋሪ ክስተቶች መካከል ጥቂቶቹ

ራያን ሬይኖልድስ፣ ሻኪራ፣ ማርቲኔዝ

ክሪስቲያኖ ሮናልዶ፤ ፒርስ ሞርጋን ከተሰኘው ጋዜጠኛ ጋር ካደረገው አነጋጋሪ ቃለ ምልልስ ጀምሮ እስከ አርጀንቲው ግብ ጠባቂ የዶሃ ድርጊትን ጨምሮ ባለንበት የአውሮፓውያኑ 2023 በስፖርቱ ዙሪያ ብዙ ክስተቶች ተመዝግበዋል።

የሆሊውድ ተዋንያን የሆኑት ራያን ሬይኖልድስ እና ሮብ ማኬልኒ የገዙት ክለብ ስኬታማነት ብዙዎችን አጀብ አሰኝቷል።

እነሆ በ2023 በእግር ኳሱ ዓለም አነጋገሪ የተባሉ ክስተቶችን በቅንጭቡ መልሰን እንቃኛለን።

የአሠልጣኞች አምባ ጓሮ

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ 15 አሠልጣኞችን አባሯል፤ በርካቶችን ቀጥሯል።

ቼልሲ በቶማስ ቱኽል፤ ቶተንሃም ደግሞ አንቶኒዮ ኮንቴ እየተመሩ ነው ሊጉን የጀመሩት። ነገር ግን ሁለቱም ከክለባቸው ጋር አልዘለቁም።

ባለፈው ነሐሴ ሁለቱ ክለቦች ሲገናኙ ከተጫዋቾቹ ይልቅ ደማቸው ፈልቶ የታየው ሁለቱ አሠልጣኖች ነበሩ።

ውዝግብ የበዛበት ፍልሚያ ሲጠናቀቅ ሁለቱ አሠልጣኞች ሊጨባበጡ ተቀራረቡ። ጀመርናዊው ቱኽል፤ ጣልያናዊው አቻቸው በተገቢውን መንገድ ሰላም አላሉኝም ሲሉ አኮረፉ።

በዚህ መሃል ሁለቱ አሠልጣኞች ዱላ ቀረሽ ፍጥጫ እና ግልምጫ ተለዋውጠው በሕዝብ ገላጋይነት ተለያዩ።

አንቶኒዮ ኮንቴና ቱኽል ሲጣሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአንቶኒዮ ኮንቴ እና የቱኽል ፍጥጫ

የሮናልዶ ቃለ-መጠይቅ

ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ባለፈው ኅዳር ከፒርስ ሞርጋን ጋር ያደረገው ቃለ መጠይቅ የእግር ኳሱ ዓለምን ያናጋ ነበር።

አምስት ጊዜ የዓለም ምርጥ ተብሎ ባሎን ደኦር ያነሳው የእግር ኳስ ኮከብ፣ በወቅቱ አሠልጣኙ የነበሩት ኤሪክ ቴን ሃግን ዘለፋቸው። ለአሠልጣኙ “ክብር የለኝም” ሲል ጉዱን አፈረጠው።

ሮናልዶ፤ አሠልጣኙ ከማንቸስተር ዩናይትድ እንዲወጣ ፍላጎት እንዳላቸው ተናገረ።

ተጫዋቹ፤ ዩናይትድ ከስፐርስ ሲፋለም ባለቀ ሰዓት ተቀይረህ ግባ ሲባል አሻፈረኝ ማለቱን ተከትሎ ከቴን ሃግ ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብቶ ነበር።

ከዚህ ቃለ መጠይቅ በኋላ ነው ሮናልዶ ከዩናትድ ወጥቶ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ያቀናው።

ኦባሜያንግ
የምስሉ መግለጫ, ኦባሜያንግ

ኦባሜያንግ እና አርሰናል

ፒዬር ኤሜሪክ-ኦባሜያንግ በቅራኔ ታጅቦ አርሰናልን ለቆ የወጣው ጥር 2022 ነበር።

ባለፈው ኅዳር ቼልሲ አርሰናልን ሲያስተናግድ የ33 ዓመቱ ጋቦናዊ የፊት መስመር ተጫዋች “ተመልሻለሁ፤ አሁን ሰማያዊ ነኝ። አርሰናሎች ጉዳዩን የግል ቅያሜ አታድርጉብኝ” ሲል ተደመጠ።

አርሰናል ጨዋታውን 1 ለ 0 ረታ። ኦባሜያንግ በጨዋታው ስምንት ጊዜ ብቻ ነው ኳስ የነካው። በ63ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ወጣ።

ከጨዋታው በኋላ ጎል አስቆጣሪው ጋብርኤል “ጉዳዩን የግል ቅያሜ አታድርጉብኝ” ሲል ትዊተር ገፁ ላይ ለጠፈ።

የማርቲኔዝ አወዛጋቢ ተግባር

ባለፈው ታኅሣሥ ኳታር ባስተናገደችው የዓለም ዋንጫ ብዙ አነጋጋሪ ክስተቶች ታይተዋል።

ከሁሉም ልቆ የወጣው ግን የአርጀንቲናው ግብ ጠባቂ ኤሚሊያኖ ማርቲኔዝ በኳታር ከፍተኛ ባለሥልጣናት ፊት ዋንጫዋን የያዘበት መንገድ ነው።

ማርቲኔዝ በዓለም ዋንጫው የፍፃሜ ጨዋታ ፍፁም ቅጣት ምት ሲመለስ የተጠቀማቸው መላዎችም መነጋገሪያ ነበሩ።

ከሁሉ በላይ በፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ፊት ያሳየው ዳንስ ግማሹን ያዝናና የተቀረውን ያስከፋ ነበር።

የክለብ አሠልጣኙ ኡናይ ኤሜሪ ማርቲኔዝ ወደ አስተን ቪላ ሲመለስ ቁጭ ብለው እንደሚያወሩ መናገራቸው ይታወሳል።

የ30 ዓመቱ ግብ ጠባቂ አገሩ አርጀንቲና ከፓናማ ስትጫወት ተመሳሳይ ድርጊት አሳየ።

ሻኪራና ፒኬ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሻኪራና ፒኬ በፍቅራቸው ዘመን

ሻኪራ እና ፒኬ

ባለፈው ጥር ኮሎምቢያዊቷ የፖፕ ሙዚቃ ኮከብ ሻኪራ፤ የቀድሞ የፍቅር ጓደኛዋ ፒኬን የሚያጥላላ ሙዚቃ ለቀቀች።

ግጥሙ እንዲህ ይላል፡ “ፌራሪን በትዊንጎ ለውጥህ፤ ሮሌክሱን በካሲዮ ቀየርህ፣ ብርቱዋን እኔ በከንቱ ተካህ” ማለቷ ነው።

ከቀናት በኋላ በቅርቡ ጫማ የሰቀለው የ35 ዓመቱ የቀድሞው የባርሴሎና ተከላካይ ዤራርድ ፒኬ፤ ትዊንጎ የተባለውን መኪና እየነዳ፤ ካሲዮ የእጅ ሰዓት አጥልቆ መጣ።

በሾርኔ የመልስ ምት መስጠቱ ነው።

‘የአባሩኝ ተማፅኖ’

ባለፈው መጋቢት ቶተንሃም ከሳውዝአምፕተን ተገናኝቶ 3 ለ 3 ተለያየ።

ከግጥሚያው በኋላ የቶተንሃሙ አሠልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ ለጋዜጠኞች አስተያየታቸን ሰጡ። ተጫዋች አልቀራቸው፤ የክለቡ አመራሮች ሁሉንም ወረዱባቸው።

ከጥቂት ቀናት በኋላ ከሥራቸው ተባረሩ።

አንቶኒዮ ኮንቴ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አንቶኒዮ ኮንቴ

የዳኛው ክርን

ይህ የሆነው ደግሞ ወርሃ ሚያዝያ ላይ ነው። ሊቨርፑል ከአርሰናል ሲጋጠም፣ ቀልብ ገዢ የነበረው ጨዋታ የሊቨርፑልን መነቃቃት የአርሰናልን ደግሞ ድክመት ያሳየ ነበር።

አርሰናል ከዚህ ጨዋታ በኋላ ባደረጋቸው ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች አቻ ወጣ።

ነገር ግን አነጋጋሪ የነበረው ክስተት የተፈጠረው በጨዋታው አጋማሽ ነው። አንዲ ሮበርትሰን አራጋቢው ኮንስታንቲን በክርናቸው ብለውኛል ሲል አማረረ።

የዳኞች ማኅበር ምርመራ አካሂዶ ምንም ጥፋት አላየሁም አለ።

የኒውካስሉ ምክትል አሠልጣኝ ጉዳይ

ኒውካስል ዩናይትድ በሚቀጥለው ዓመት በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ይጫወታል። ይህ የሚሆነው ከ2003 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ዘንድሮ በኒውካስል ቤት አነጋጋሪ ከነበሩ ሰዎች መካከል አንዱ ምክትል አሠልጣኙ ጄሰን ቲንዳል ናቸው።

አንድ የትዊተር ተጠቃሚ “ጄሰን ቲንዳል በጣም የትኩረት ምንጭ መሆን ይወዳሉ” ብሎ ፅፎ በርካታ ሺህ ‘ላይክ’ ካፈሰ በኋላ ነው መነጋገሪያ የሆነው።

አሠልጣኝ ኤዲ ሃው “ሁለተኛንም ሁሌ ቆመን ትዕዛዝ እንሰጣለን። ቲንዳል ከእኔ እኩል ተጫዋቾችን እንዲያነቃቃ አበረታታዋለሁ” ብለዋል።

የሬክስሃም ግስጋሴ

ማጠቃለያ እንዲሆነን የሬክስሃም ዩናይትድን ጉዳይ እናንሳ።

የሆሊውድ ተዋንያኑ ራያን ሬይኖልድስ እና ሮብ ማኬልኒ የገዙት ክለብ ስኬታማነት ብዙዎችን አጀብ አሰኝቷል።

ሬክስሃም የተሰኘው ክለብ ወደ ላይኛው ሊግ ለማለፍ ያደረገው ጨዋታ በጣም ቀልብ ገዢ እና ልብ አንጠልጣይ ነበር።

ሁለቱ ባለቤቶች ለእግር ኳስ አዲስ ቢሆኑም፣ አሁን ግን ሲተኙም ሲነሱም የሚያልሙት ስለኳስ እንደሆነ ተናግረዋል።

ክለቡ በሚመጣው የክረምት የዝግጅት ወቅት ወደ አሜሪካ አቅንቶ ከእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ቡድኖች ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ዕቅድ ይዟል።

ማንቸስተር ዩናይትድ እና ቼልሲ በወዳጅነት ጨዋታ መርሃ ግብር የተካተቱ ቡድኖች ናቸው።