የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግን ሰርቀው ያስተላለፉ 5 ግለሰቦች በድምሩ 30 ዓመት እሥር ተላለፈባቸው

የፎቶው ባለመብት, REUTERS - CARL RECINE
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ አስተላልፈዋል የተባሉ አምስት ግለሰቦች በእሥር ተቀጡ።
አምስቱ ሰዎች ከ50 ሺህ ደንበኞች ቢያንስ 7 ሚሊዮን ፓውንድ ማትረፋቸው ተሰምቷል።
ይህ ፍርድ በፕሪሚዬር ሊጉ ታሪክ ብዙም ተሰምቶ የማያውቅ ነው።
ሃመርስሚዝና ፉልሃም ካውንስል የተባለ ድርጅት ረጅም ጊዜ ካደረገው ምርመራ በኋላ ነው ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር የዋሉት።
ለሕገ-ወጥ የእግር ኳስ ቀጥታ ሥርጭት የከፈሉ ሰዎች ስም ዝርዝር አሁን በመርማሪዎች እጅ ሥር ይገኛል። እኚህ ሰዎች ምን ዓይነት ቅጣት ይጣልባቸዋል የሚለው ግልፅ አይደለም።
የቡድኑ መሪ የሆነው የ36 ዓመቱ ማርክ ጎልድ 11 ዓመት ተፈርዶበታል።
የተቀሩት አራት ግለቦች ደግሞ ከሶስት እስከ አምስት ዓመት በሚዘልቅ እሥራት ተቀጥተዋል።
ከወንጀለኞቹ መካከል አንደኛው ክሪስቶፈር ፌልቨስ የተባለ ግለሰብ በድብቅ የተቀረፁ የአዋቂዎችና የሕፃናት ምስሎች ኮምፒውተሩ ውስጥ ተገኝተውበታል።
ጎልድ የተባለው የቡድኑ መሪ ደቡብ ለንደን፤ ግሪንዊች የተባለ ከተማ ነዋሪ ሲሆን የሕግ ሰዎች በሩን ሰብረው ገብተው በቁጥጥር ሥር አውለውታል።
ፍሎውለስ የተሰኘው ቡድን፤ ከዩኬ፣ ካታር፣ አሜሪካ፣ አውስትራሊያና ካናዳ የቀጥታ ሥርጭቶችን በመውሰድ በሕገ-ወጥ መንገድ ለተመልካቶች ያደርሳል።
ግለሰቦቹ፤ የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታና ሌሎችን ፕሮግራሞች የሚያሳይ በተንቀሳቃሽ ስልክና ስማርት ቴሌቪኖች ላይ የሚጫን መተግበሪያ ሠርተዋል።
ተመልካቾች ከመተግበሪያው ላይ የፈለጉትን ሥርጭት መርጠው መመልከት ይችላሉ።
ፕሪሚዬር ሊጉ እንዳለው በፈረንጆቹ ከ2016 እስከ 2021 ባለው ጊዜ ቡድኑ ቢያንስ 7.2 ሚሊዮን ፓውንድ አትርፏል።
ጎልድ የተባለው ግሰለብ ደግሞ በግሉ 1.7 ሚሊዮን አጋብሷል።
ሕገ-ወጡን ሥርጭት ገዝተው የሚመለከቱ ግለሰቦች በወር 10 ፓውንድ ከፍለው እያንዳንዱን የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታ መኮምኮም ይችላሉ።
ነገር ግን ስካይ፣ ቢቲ ስፖርትና አማዞን ፕራይም የተሰኙት ሕጋዊ አሰራጮች 80 ፓውንድ ግድም ነው የሚያስከፍሉት።
በርካታ ጨዋታዎች በቴሌቪዥን ባለመሰራጨታቸው ነው ሕገ-ወጥነት የበረከተው የሚሉ አስተያየቶች እየተሰሙ ነው።
የአውሮፓ እግር ኳስ ማሕበር፤ ፕሪሚዬር ሊጉ ቅዳሜ ቅዳሜ ከቀኑ 8፡45 እስካ 11፡15 የዩኬ አሰራጮች ጨዋታ ማሳየት እንዳይችሉ ማገድ ይችላል የሚል መብት ሰጥቶታል።
ይህ ለዓመታት የቆየው ሕግ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ መጥተው ጨዋታውን በአካል እንዲከታተሉ በሚል የወጣ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, PREMIER LEAGUE
ነገር ግን ሕገ-ወጥ አሰራጮቹ ተመልካቾች በለተይ በዩኬ ሰዓት አቆጣጠር ቅዳሜ 9 ሰዓት የሚጀምሩ ጨዋታዎችን ያስተላልፋሉ።
80 በመቶ የሚሆኑ ለሕገ-ወጥ አሰራጮች ገንዘብ የከፈሉ ሰዎች ዓላማቸው ቅዳሜ 9፡00 ጨዋታዎችን ለመመልከት ነው።
ኢንቴሌክችዋል ፕሮፐርቲ ኦፊስ ከተሰኘው ቢሮ የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው ባለፈው ዓመት ዩኬ ውስጥ 4 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች በሕገ-ወጥ መንገድ ስፖርት ተመልክተዋል።
አንዳንድ የሰፈር ውስጥ መጠጥ ቤቶችና ከፍ ያሉ መዝናኛ ሥፍራዎችም የማይተላለፉ ጨዋታዎችን ለማሳየት አሊያም ክፍያ ላለመክፈል ሕገ-ወጥ ማሰራጫዎችን ይጠቀማሉ።
ሕገ-ወጥ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን ከፍለው የተመለከቱ ሰዎች ቅጣት ይደርስባቸዋል ተብሎ አይታመንም።
ነገር ግን ፕሪሚዬር ሊጉ ሌሎች በሕገ-ወጥ መንገድ ጨዋታ የሚያስተላልፉ ሰዎችን አሳዶ ለመያዝ ቃል ገብቷል።












