ዝውውራቸው አይቀሬ የሚመስለው ራይስ፣ ቤሊንግሃም፣ ኬን፣ ኦሲምሄን እና ሜሲ ወዴት ያቀኑ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በመጪው የክረምት የዝውውር መስኮት ክለባቸውን ለቀው ወደ ሌላ ቡድን ሊቀላቀሉ ከሚችሉ ኮከቦች መካከል ጁድ ቤሊንግሃም፣ ደክላን ራይስ፣ ሊዮኔል ሜሲ፣ ቪክተር ኦሲምሄን እና ሃሪ ኬን ተጠቃሽ ናቸው።
ሜሲ ወደ ባርሳ ይመለስ ይሆን? አርሰናልስ የደክላን ራይስ ዝውውርን ማሳካት ይቻለዋል?
ለፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች የክረምት የዝውውር መስኮት ሰኔ 8/2015 ዓ.ም. ተከፍቶ ነሐሴ 26/2015 ዓ.ም. ላይ ይዘጋል።
በዚህ የውውር መስኮት ከሌሎች ክለቦች ጋር ስማቸው በስፋት እየተነሱ የሚገኙ ኮከቦችን የዝውውር ጭምጭምታ እንመልከት።
ጁድ ቤሊንግሃም
ገና በ19 ዓመቱ የቦሪሺያ ዶርተመንድ አምበል መሆን የቻለው፤ በክሎፕ “እጅግ ልዩ ተጫዋች” ተብሎ የተሞካሸው ቤሊንግሃም፣ በአሁኑ ወቅት በእግር ኳስ ተጫዋቾች ገበያ እጅግ ውድ ከሚባሉ ኮከቦች መካከል አንዱ ነው።
የስፔኑ ኃያል ቡድን ሪያል ማድሪድ አማካዩን ተጫዋች ለማስፈረም ንግግር እያደረገ ይገኛል። ማድሪድ ለእንግሊዛዊው አማካይ 89 ሚሊዮን ፓወንድ ለመክፈል ዝግጁ ቢሆንም፣ ዶርተመንድ ግን ለቤሊንግሃም 130 ሚሊዮን ፓወንድ ይፈልጋል እየተባለ ነው።
ከማድሪድ በተጨማሪ ማንችስተር ሲቲም የእንግሊዛዊው አማካይ ፈላጊ ነው። ሊቨርፑልም እንዲሁ ፍላጎቱን አሳይቶ የነበረ ቢሆንም፣ ዋጋው ለቀያዩቹ የሚቀመስ አልሆነም።
የሊቨርፑል አሠልጣኝ ክሎፕ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ሊቨርፑል ቤሊንግሃምን መፈለግ “አንድ ሕጻን ለገና በዓል ስጦታ ቅንጡ የሆነውን ፌራሪ መኪና እንደመፈለግ ነው” ብለው ነበር።
ሃሪ ኬን
“ሃሪ ኬን፤ ሰኔ ላይ እንገናኝ።”
ይህን ያሉት የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች ቡድናቸው ከቶተነሃም ጋር በተጫወተበት ወቅት ነበር።
ከዩናይትድ በተጨማሪ ቼልሲ፣ ፒኤስጂ እና ባየር ሙኒክ በተደጋጋሚ ስማቸው ከ29 ዓመቱ ኬን ጋር ተያይዞ እየተነሳ ነው።
ኬን እና ቶተነሃም ከውሳኔ መድረስ ያለባቸው ሰዓት ላይ ደርሰዋል። ኬን ከስፐርስ ጋር የአንድ ዓመት ውል ነው የቀረው። ውሉን ካላራዘመ በቀር በቀጣይ ዓመት በነጻ ሊዘዋወር ይችላል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ደክለን ራይስ
የዌስት ሃም አሠልጣኝ ዴቪድ ሞዬስ እንግሊዛዊው አማካይ በክረምት የዝውውር መስኮት ክለቡን ሊለቅ እንደሚችል ተናግረዋል።
ራይስ ከሰሜን ለንደኑ አርሰናል ጋር ስሙ በስፋት ተያይዞ ይነሳል። ይሁን እንጂ የራይስ ዋጋ ለአርሰናል የሚቀመስ ላይሆን ይችላል።
መድፈኞቹ ራይስን ለመወሰድ ለክለባቸው ክብረ ወሰን የሆነውን ለኒኮላስ ፔፔ የከፈሉትን ክፍያ በእጥፍ ማሳደግ ግድ ሊሆንባቸው ይችላል።
ሞዬስ ሚያዝያ ወር ላይ ደክላን ራይስ ከ150 ሚሊዮን ፓወንድ ባነሰ ዋጋ አይሸጥም ብለው ነበር።
ሊዮኔል ሜሲ
የዓለም ዋንጫ አሸናፊው ሊዮኔል ሜሲ ከፒኤስጂ ጋር ያለው ውል በክረምቱ ወራት ሲጠናቀቅ ክለቡን ይለቃል።
ሜሲ ከክለቡ ጋር ያለው ግንኙነት ሻክሯል። ከሦስት ሳምንታት ገደማ በፊት አርጀንቲናዊው ተጫዋች ከክለቡ ፍቃድ ሳያገኝ ወደ ሳዑዲ አረቢያ በማቅናቱ ለሁለት ሳምንታት በክለቡ ታግዶ ነበር።
ከእገዳው በኋላ ወደ ሜዳ ተመልሶ ሲገባም ከደጋፊዎች ተቃውሞ ገጥሞታል።
ሜሲ እአአ 2021 ላይ በባርሳ በነበረው የፋይናንስ ችግር ወደ ፓሪሱ ክለብ መዘዋወሩ ይታወሳል። ሜሲን ወደ ካምፕ ኑ የመመለስ ፍላጎት ቢኖርም ባርሳ ባለበት የገንዘብ እጥረት ይህን ማሳካት የሚችል አይመስልም።
ሜሲ በቀጣይ ወደ አሜሪካ ተጉዞ በሜጀር ሊግ ሶከር ለኢንተር ማያሚ ሊጫወት ይችላል። ከዚያ ወጪ በዓመት 350 ሚሊዮን ፓወንድ ተከፍሎት የሳዑዲውን አል-ሂላልን ይቀላቀል ይሆናል የሚል ግምት አለ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቪክተር ኦሲምሄን
ኦሲምሄን በናፖሊ ባሳየው ድንቅ ብቃት የብዙ ክለቦችን ቀልብ መሳብ ችሏል።
ናይጄሪያዊውን የፊት መስመር ተጫዋች የራሳቸው ለማድረግ ፍላጎት ካላቸው ክለቦች መካከል ቼልሲ፣ አርሰናል፣ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ሊቨርፑል፣ ፒኤስጂ እና ሪያል ማድሪድን ማንሳት ይቻላል።
ናይጄሪያዊው በ30 ጨዋታዎች 23 ጎሎችን በማስቆጠር ክለቡ ከ33 ዓመታት በኋላ የሊጉን ዋንጫ እንዲያነሳ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ኦሲምሄን ኅዳር ወር ላይ፤ “ጠንክሬ የምሰራው በፕሪሚየር ሊግ የመጫወቴን ሕልም ለማሳካት ነው” ካለ በኋላ ብዙ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
የ22 ዓመቱ ተጫዋች የቀድሞ የቼልሲውን አጥቂ ዲዲዬር ድሮግባን አርአያው አድጓል። እአአ 2016 ላይ ደግሞ አርሰናልን አልፈልግም ብሎ ለጀርመኑ ዎልፍስበርግ ፈርሞ ነበር።
የዚህ ተጫዋች ዋጋ ከ90 አስከ 130 ሚሊዮን ፓወንድ እንደሆነ ይገመታል።
ማውንት፣ ምባፔ፣ ማዲሰንም ይጠበቃሉ
ሜሰን ማውንትን ለማስፈረም ፍላጎት ካላቸው ክለቦች መካከል ዩናይትድ፣ ሊቨርፑል እና አርሰናል ይጠቀሳሉ። ቼልሲ ለ24 ዓመቱ እንግሊዛዊ አማካይ 70 ሚሊዮን ፓወንድ ዋጋ ቆርጦለታል።
ሌስተር ከፕሪሚዬር ሊጉ መውረዱን ተከትሎ የጀምስ ማዲስን ዝውውር አይቀሬ ይመስላል። ኒውካስል እና ቶተንሃም ደግሞ ማዲሰንን ለመውስድ አሰፍስፈው እየጠበቁ ያሉ ክለቦች ናቸው።
የ24 ዓመቱ ኪሊያን ምባፔ በቀጣይ ዓመት ከክለቡ ጋር ያለው ውል ስለሚያበቃ ወደ ሌላ ክለብ ሊዘዋወር ይችላል በሚል በርካታ ክለቦች የራሳቸው ለማድረግ ፍላጎት እያሳዩ ነው።
የብራይተኖቹ ሞሰስ ካይሴዶ እና አሌክሲስ ማክ አሊስተርም ወደ ሌላ ክለብ መዘዋወራቸው የሚቀር አይመስልም።












