የመጨረሻው የሶቭየት መሪ ሚካይል ጎርባቸቭ በ91 ዓመታቸው አረፉ

ሚካይል ጎርባቸቭ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቀዝቃዛው ጦርነት በሰላም እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ የሚነገርላቸው የቀድሞው የሶቭየት ኅብረት መሪ ሚካይል ጎርባቸቭ በ91 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

እንደ አውሮፓውያኑ 1985 ሥልጣን ላይ የወጡት ጎርባቸቭ የያኔዋን የሶቭየት ኅብረትን ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያቀራረቡ ሲሆን በአገሪቱ ውስጥም ማሻሻያዎችን አድርገዋል።

ይሁን እንጂ ጎርባቸቭ ሶቭየት ኅብረትን ከመፈራረስ መታደግ አልቻሉም ነበር።

የጎርባቸቭን ሕልፈት ተከትሎ በመላው ዓለም በርካቶች ሀዘናቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ “የታሪክን ሂደት የቀየሩ መሪ ነበሩ” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ ለእርሳቸው ያላቸውን ክብር ገልጸዋል።

“ዓለም ቁርጠኛ እና ለሰላም ደከመኝ ሰለቸኝ የማይሉ ታላቅ መሪ አጥታለች” ብለዋል የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ ጉቴሬዝ።

ጎርባቸቭ ሕይወታቸው ያለፈበት በሞስኮው የሚገኝ ሆስፒታል፣የቀድሞው የሶቭየት መሪ ለረዥም ጊዜ በከፋ ሕመም ሲሰቃዩ እንደነበር ገልጿል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የጤንነታቸው ሁኔታ በማሽቆልቆሉ ሆስፒታል ሲመላለሱ እንደነበረ ተዘግቧል።

ሰኔ ወር ላይ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በኩላሊት ሕመም ሆስፒታል ገብተው እንደነበር ዘግበዋል። ይሁን እንጂ አሁን ሕይወታቸው ያለፈበት ምክንያት ምን እንደሆነ አልተገለጸም።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በጎርባቸቭ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን መግለጻቸውን ቃል አቀባያቸው ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለሩሲያ የዜና ወኪል፣ኢንተርፋክስ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን “ብርቅዬ መሪ” ሲሉ የገለጿቸው ሲሆን፣ ጎርባቸቭ በቀዝቃዛው ጦርነት ውጥረት ውስጥ “መጪውን ዘመን አሻግረው መመልከት የቻሉ ልዩ ፖለቲከኛ ነበሩ” ሲሉ አወድሰዋቸዋል።

የአውሮፓ ኅብረት ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ላይንም “ለነጻ አውሮፓ መንገድ የከፈቱ ታማኝ እና የተከበሩ መሪ ነበሩ” ሲሉ አድንቀዋቸዋል። ፕሬዝዳንቷ አክለውም “ያሳረፉትን አሻራ አንረሳውም” ብለዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በበኩላቸው የጎርባቸቭን ጽናት እና ጥንካሬ እንደሚያደንቁ ገልጸው፤ ፑቲን በዩክሬን ላይ ወረራ ሲፈጽሙ ጎርባቸቭ የሶቭየት ኅብረት ማኅበረሰብን ክፍት ማድረጋቸው ለሁላችንም ምሳሌ ሆኖ ይቆያል ብለዋል።

ጎርባቸቭ እንደ አውሮፓውያኑ 1985 የሶቭየት የኮሚዩኒስት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ እና የአገሪቱ መሪ ነበሩ።

በዚያን ጊዜ የ54 ዓመት ጎልማሳ የነበሩ ሲሆን ፖሊት ቢሮ በመባል የሚታወቀው አገሪቷን የሚመራው ምክር ቤት ወጣት አባል ነበሩ።

በበርካታ እድሜያቸው የገፉ የምክር ቤት አባላት መካከልም እንደ ትኩስ ኃይል ይታዩ ነበር።

ጎርባቸቭ ፣ በምዕራባውያኑ ዘንድ በአሜሪካ እና በእንግሊዝ መካከል ያለውን ጨምሮ በሶቭየት ኅብረትና በምዕራባውያኑ መካከል ከፍተኛ ውጥረት በነበረበት ወቅት የቀዝቃዛው ጦርነት እንዲቆም አቅጣጫ የቀየሱ መሪ ተደርገው ይታያሉ።

በዚህም እንደ አውሮፓውያኑ 1990 በምስራቁ እና በምዕራቡ ዓለም መካከል ያለውን ግንኙነት ለመለወጥ በተጫወቱት ከፍተኛ የመሪነት ሚና የኖቤል ሰላም ተሸላሚ ሆነዋል።

ከ30 ዓመታት በፊት በሥልጣን ዘመን ማብቂያቸው ላይ፣ ታላቋ ኃያል አገር ሶቪየት ኅብረት ፈርሳ የመጨረሻው የሶሻሊስቷ አገር ፕሬዝዳንት ሆነው ወደ ጡረታ አምርተዋል።