ከቫግነር ጋር በዩክሬን እንዲዋጋ ከእስር የተለቀቀው ሩሲያዊ በሌሎች ወንጀሎች ተከሰሰ

 ደምያን ክቮርክያን

የፎቶው ባለመብት, JOINT PRESS SERVICE OF KRASNODAR REGIONAL COURTS

ከሩሲያ ቅጥረኛ ቡድን ቫግነር ጋር በዩክሬን እንዲዋጋ ቀደም ብሎ ከእስር እንደተለቀቀ የታመነው እስረኛ ከጦርነቱ ከተመለሰ በኋላ በሩሲያ የግድያ ወንጀሎችን በመፈፀም ተከሰሰ።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2016፣ 18 ዓመታትን በእስር እንዲያሳልፍ የተፈረደበት ደምያን ክቮርክያን፣ ከሥራ ቦታቸው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ የነበሩ አንድ ወጣት ወንድ እና ወጣት ሴት በመግደል ወንጀል ተከሶ በቁጥጥር ሥር ውሏል።

ይሁን እንጅ ግለሰቡ ድርጊቱን አልፈፀምኩም ብሏል።

ቀደም ብሎ በዩክሬን እንዲዋጋ ከእስር በነጻ የተለቀቀው እና ይቅርታ የተደረገለት፣ በኋላ ላይ ደግሞ በሌሎች ወንጀሎች የተከሰሰው እርሱ ብቻ እንዳልሆነ ቢቢሲ መረዳት ችሏል።

የቀድሞ እስረኛን ጠቅሶ አንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ እንደዘገበው ከሆነ፣ ክቮርክያን ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ የቫግነር ቅጥረኛ ቡድን መሪ ዮቭገኒ ፕሪጎዢን እርሱ የሚገኝበትን እስር ቤት በጎበኙበት ወቅት ከተመለመሉ 150 እስረኞች መካከል አንዱ ነበር።

ከዚያም በኋላ ክቮርክያን፣ በሩሲያ ደቡብ ምዕራብ፣ ካራስኖዳር ውስጥ በሚገኘው በትውልድ መንደሩ ፕሪዶሮዥናያ መታየቱንና ከዩክሬን የጦር ሜዳ መመለሱን ለሰዎች ሲናገር እንደነበር ቢቢሲ ሰምቷል።

የቀድሞ እስረኛው በግድያ ከተከሰሰባቸው ግለሰቦች መካከል የሕጻናት አዝናኝ የሆነችው የ19 ዓመቷ ታትያን ሞስትይኮ አንዷ ናት።

የሞስትይኮ እናት ናደዥዳ ልጇ ታትያና በአንድ ዝግጅት ላይ ጌሞችን ስታሰናዳ እና ስትደንስ የሚያሳይ ቪዲዮ ለቢቢሲ አሳይታለች።

“ ይህንን የልጄን ሥራ እወደዋለሁ። ከሥራ ስመለስ ሲሰሩ የነበሩትን እያየሁ እስቅ ነበር። በጣም ያስደንቁኝ ነበር ” ብላለች ናደዥዳ።

ነገር ግን ታትያን የመጨረሻ ሥራዋን የሰራችው በአውሮፓውያኑ ሚያዝያ 28 ነው።

ታትያን ሞስትይኮ

የፎቶው ባለመብት, FAMILY ARCHIVE

የምስሉ መግለጫ, የሕጻናት አዝናኝ የሆነችው ታትያን ሞስትይኮ የ19 ዓመት ወጣት ነበረች።
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ታትያን በወቅቱ የሥራ ኃላፊዋ ክሪል ቹብኮ ወደ ቤቷ እያደረሳት እያለ ደቡብ ምዕራብ ሩሲያ በምትገኘው በቤሬዛንካያ ከተማ አቅራቢያ የመኪና ጎማቸው ስለፈነዳባቸው ዳር መኪናቸውን አቆሙ።

የክሪል ባለቤት የሆነችው ዳሪያ ለአገር ውስጥ ሚዲያ እንደተናገረችው ክሪል በወቅቱ ሊዘገይ እንደሚችልና የሚረዷቸው ወጣቶች በማግኘታቸው እንዳትጨነቅ ደውሎላት ነበር።

ነገር ግን ለመጨረሻ ጊዜ የሰማችው የባለቤቷ ድምጽ ያ ነበር።

ሌሊቱን ደጅ ደጅ ስታይ ያሳለፈችው ዳሪያ ጠዋት ላይ ቤት አለመድረሳቸውንና አንዳች ነገር ተፈጥሮ ሊሆን እንደሚችል በመጠርጠር ለፖሊስ ማሳወቋን ገልጻለች።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም በተለያዩ አካባቢዎች ግለሰቦቹን ለመፈለግ ሲረዱ የነበረ ሲሆን የታትያና እናትም ልጇን ለመፈለግ በምስራቅ ሩሲያ ከሚገኘው የመኖሪያ መንደሯ በመነሳት ወደ አካባቢው ለመድረስ በባቡርና በአውሮፕላን የ6 ሰዓት ጉዞ አድርጋለች።

የልጇን የመገደል መርዶ የሰማችውም በረራ ላይ ዘግታው ቆይታ የነበረውን ስልኳን በከፈተችበት ወቅት ነበር።

የ31 ዓመቱን ክቮርክያንን ጨምሮ በግድያ ወንጀል የተጠረጠሩ 3 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን፣ አናቶሊይ ድቮይኒኮቭ እና አራም ታቶስያን የተባሉ ሌሎች ሁለት ግለሰቦችም መርማሪዎች በውድላንድ የሚገኙ ትኩስ መቃብሮችን እንዲመረምሩ መርተዋቸዋል።

ክሪል እና ታትያን በስለት የተወጉ ሲሆን ፖሊስ እንደለው ወጣቷ ሴት ጥቃት የተሞላበት ግድያ እንደተፈፀመበት ምልክት ታይቶባታል።

በግድያው ወንጀል ተሳትፈዋል በሚል የተከሰሱት ድቮይኒኮቭ እና ታቶስያን ዘረፋ እና ግድያውን እንደፈፀሙ ያመኑ ሲሆን ክቮርክያን ምንም እንኳን ከደሙ ንጹህ ነኝ ቢልም እርሱ አስተባባሪው እንደነበር ተናግረዋል።

ኬቮርክያ ከዚህ ቀደም በሰራው ወንጀል 18 ዓመት ተፈርዶበት ነበር።

ክቮርክያን፣ ታቲያ እና ኪሪል ከተገደሉበት ብዙም ሳይርቅ መኪና የዘረፈ የወንበዴ ቡድንን በመምራትም ተከሷል።ወንበዴዎቹ በመኪናው ውስጥ ያሉ ሰዎችን ከዘረፉ በኋላ አንዱን ተኩሰው ገድለዋል።

ናደዥዳ ግለሰቡ በምን ሕጋዊ መሠረት እንደተፈታ ግልጽ አልሆነላትም።

በሩሲያ ሕግ መሠረት እስረኞች ለመለቀቅ ቢያንስ ሁለት ሦስተኛውን ፍርዳቸውን መጨረስ አለባቸው። በዚህም ክቮርክያን ቢያንስ 12 ዓመታትን በእስር ማሰለፍ ይጠበቅበት ነበር።