ፕሪጎዢን፣ ፑቲን እና ሾይጉ፡ ተቀናቃኝነት የወለደው ወታደራዊ አመፅ በሩሲያ

የቅጥረኛው ቡድን ቫግነር አድራጊ ፈጣሪ የቭገኒ ፕሪጎዢን

የፎቶው ባለመብት, PRESS SERVICE OF "CONCORD"

የቫግነር ቅጥረኛ ቡድን ወታደራዊ አመፅ 24 ሰዓት እንኳ ሳይሞላው ተቀጭቷል። ነገር ግን ይህ አመፅ ለዓመታት በቅናት፣ በተቀናቃኝነት እና በዓላማ ሲብላላ የቆየ ነው።

የዚህ ድራማ መሪ ተዋንያን አንዱ የቅጥረኛው ቡድን ቫግነር አድራጊ ፈጣሪ የቭገኒ ፕሪጎዢን ነው።

የተቀሩት ደግሞ የግዙፉ የሩሲያ ጦር መሪ የሆኑት ሰርጌ ሾይጉ እና ቫለሪ ጌራሲሞቭ ናቸው።

ፕሪጎዢን በ1980ዎቹ በተደራጀ የወንጀል ድርጊት ተከሶ ዓመታትን ዘብጥያ አሳልፏል። ላካበተው መጠን የለሽ ሃብትም የፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን እጅ አለበት።

ቅጥረኛው የቫግነር ቡድን በ2014 ከተመሠረተ በኋላ ፕሬዝደንት ፑቲን ሩሲያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተፅዕኖ ማሳያ ሆኖ አገልግሏል።

ቫግነር የተሰኘው ቅጥረኛ ወታደራዊ ኃይል ከቀድሞ የሩሲያ ልዩ ኃይል አባላት የተውጣጣ ነው። ይህ ቡድን በሶሪያ የፑቲን አጋር የሆኑትን ባሽር አል-አሳድን አግዟል። ማሊ ውስጥ ደግሞ የፈረንሳይ ተፅዕኖ እንዳይስፋፋ የበኩሉን ሚና ተጫውቷል።

ፕሪጎዢን፤ እስካለፈው ዓመት ድረስ ምንም ያክል ማስረጃ ቢኖርም የቅጥረኛው ቡድን ኃላፊ መሆኑን አያምንም ነበር።

እንዲያውም ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ አንድ ጋዜጠኛ የሚሊሻው ቡድን አለቃ ነህ ሲል ስሜን አጥፍቷል ሲል ክስ አቅርቦም እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቡድኑ ‘አፕሬሽን’ ፈፅሞ ሽምጥጥ አድርጎ መካድ መቻሉ በፑቲን ዘንድ ተወዳጅነት ከማትረፍ አልፎ የሩሲያን ወታደራዊ እና የደኅንነት ክንፍ እስከመገዳደር አድርሶታል።

በአመፅ፣ በሙስና እና በዓላማ የተቃኘ ሕይወት የመራው ግለሰቡ፣ ባለፉት 24 ዓመታት ፑቲን ለገነቧት ሩሲያ ትክክለኛ መገለጫ ባሕሪ ያለው ነው።

ምንም እንኳ ፕሪጎዢን ጉልበቱ ፈርጣማ ቢሆንም ፑቲን ካሏቸው ጥቂት የቅርብ አማካሪዎች መካከል አይደለም።

ግለሰቡ ሞስኮው የሚገኙ ሙሰኛ እና ሰነፍ ያላቸውን ባለሥልጣናት ከመዝለፍ ወደኋላ ብሎ አያውቅም።

በተለይ ደግሞ ለጦር ኃይሉ መሪ ቫለሪ ጌራሲሞቭ እና ለመከላከያ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ሾይጉ ያለውን ጥላቻ ደብቆ አያውቅም።

የመከላከያ ሚኒስትሩ እንደሌሎች የፑቲን የቅርብ ሰዎች አይደሉም። አብዛኞቹ የፑቲን አማካሪዎች የሰፈራቸው የሴንት ፒተርስበርግ ሰዎች ናቸው። ሾይጉ ግን ተወልው ያደጉት በሩሲያ እና ሞንጎሎያ ጠረፍ አካባቢ ካለ ሥፍራ ነው።

ሾይጉ ምንም እንኳ የሩሲያን ወታደራዊ ኃይል ከአሥር ዓመት በላይ ቢያስተዳድሩም መለዮ ለብሰው አላገለገሉም።

ይልቁንስ በኮሚዩኒስት ፓርቲ የውስጥ እርከን እያደጉ መጥተው ነው ለዚህ ደረጃ የደረሱት።

ሌላኛው የጦር ኃይሉ መሪ ጌራሲሞቭ ግን በተቃራኒው ውስጥ አዋቂ ናቸው። በ90ዎቹ ቼችንያ ውስጥ በተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ የተሳተፉ ሲሆን፣ ከሶቪየት ኅብረት ውድቀት በኋላ ለረዥም ዓመታት ወታደራዊ ኃይሉን የመሩ ናቸው።

ፕሪጎዢን ለወታደሮች ማራኪ ደመወዝ እየከፈለ የሩሲያ ጦር ኃይል አባላት እንዲፈልሱ ማድረጉ በሦስቱ ግለሰቦች መካከል መሻከር እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።

ነገሮች እየተጧጧፉ የመጡት ከዩክሬን ወረራ በኋላ ነው። በለተይ ደግሞ ባኽሙት ውስጥ የተካሄደውን ከባድ ጦርነት ተከትሎ ፍጥጫቸው ግልጽ ወጥቷል።

በዚህ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ የቫግነር ወታደሮች እንደሞቱ ይታመናል። ይህ ደግሞ ፕሪጎዢን ለጦር ኃይሉ መሪዎች ያለው ጥላቻ ከፍ እንዲል አድርጓል።

ፕሪጎዢን፤ ሁለቱ የጦር መሪዎች የቫግነር ወታደሮችን ድል የራሳቸው አስመስለው ስማቸውን እያጎሉ ነው ሲል ይከሳል።

ግለሰቡ የሩሲያ ጦር ኃይል መሪዎችን በግላጭ መዝለፉ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ትኩረት ምንጭ አድርጎታል።

የሩሲያ ጦር ኃይል የሰውየውን ዘለፋ እንዴት መመከት እንዳለበት ግራ እንደገባው አንድ ሾልኮ የወጣ ማስረጃ ያሳያል።

ሾይጉንና ጌራሲሞቭን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ወደ ክሬምሊን ስንመጣ ፑቲን ወትሮውኑም ተቀናቃኞቻቸው እርስ በርስ ሲባሉ ዝም ብለው ያያሉ እንጂ ጣልቃ አቀያገቡም።

ይህን የሚያደርጉት ተቀናቃኞቻቸው እርስ በርሳቸው ተጠላልፈው መውደቅ ለእርሳቸው የተሻለ የሥልጣን ዕድሜ ነው ብለው ስለሚያስቡ እንደሆነ ይታመናል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ የሆነ ነገር ቢያደርጉ የቫግነር ሚሊሻ ይከታተላቸዋል፤ ፕሪጎዢንን ደግሞ ወታራዊው ኃይል ይቆጣጠረዋል ማለት ነው። ከላይ ፑቲን ይቀመጣሉ።

ፕሪጎዢን ምንም ቢሆን አፉን አውጥቶ የፑቲንን ስም አንስቶ ነቀፌታ አሰምቶ አያውቅም። ባይሆን ሩሲያ የዩክሬንን ጦርነት በጊዜ ያልቋጨችው ፑቲንን የከበቧቸው ሰዎች አቅመ ደካማ በመሆናቸው ነው የሚል ትችት ያሰማል።

ልክ ፕሪጎዢን እንዳለው የዩክሬን ጦርነት ከታሰበው በላይ ጊዜ ለመፍጀቱ ፑቲን፤ ጌራሲሞቭ እና ሾይጉን ተጠያቂ አድርገዋል የሚል ሐሜት አለ።

ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፑቲን ስትራቴጂ ውጤት አልባ መሆን ጀመረ።

ፕሪጎዢን፤ አንድ ቴሌግራም ላይ በተለቀቀ ተንቀሳቀሽ ምስል፣ በቫግነር ወታደሮች ሬሳ ተከቦ የሾይጉ እና ጌራሲሞቭን ስም እያነሳ “የጦር መሣሪያው የታል?” እያለ በኃይለ ቃላት የታጀበ ዘለፋ ሲያሰማ ይታያል።

ከዩናይትድ ስቴትስ ስለላ መረብ የተገኘ አንድ ድብቅ ማስረጃ በወቅቱ ፕሪጎዢን፤ ፑቲን እና ሾይጉ በተገኙበት ለስብሰባ መጠራቱን ያሳያል። ነገር ግን ስብሰባው የታሰበውን ያህል ለውጥ አላመጣም።

በፈረንጆቹ ሰኔ 10 ሾይጉ አንድ ዕቅድ አወጡ። ዕቅዱ ቅጥረኛ ወታደሮች በሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ስር እንዲሆኑ ፊርማቸውን እንዲያሳርፉ የሚያደርግ ነው።

ቅጥረኛ ወታደሮች ይህን ፊርማ እስከ ሐምሌ 1 ድረስ እንዲፈርሙ አዲሱ ሕግ ያስገድዳል።

ምንም እንኳ ይህ ሕግ ይፋ ሲሆን የፕሪጎዢን ስም ባይነሳም የሰውየውን ተፅዕኖ ለመቀነስ ሆን ተብሎ እንደተደረገ ብዙዎች ያምናሉ።

ይሄኔ ፕሪጎዢን በቁጣ ተነሳ። “ቫግነር ከሾይጉ ጋር ምንም ዓይነት ስምምነት አይፈፅምም” ሲል ዛተ። ይሄኔ ነው የቀድሞ ወዳጁ ፑቲን እሱን ክደው ለሹመኛው ሾይጉ እንዳደሉ የተገለጠለት።

ከቀናት በኋላ ፑቲን ለመገናኛ ብዙኃን ስለአዲሱ ዕቅድ ሲያወሩ “በፍጥነት ሊተገበር የሚገባው ነው ሲሉ ተደመጡ።”

ብዙዎች እንደሚያምኑት ፕሪጎዢን ወታደራዊ አመፅ ለማነሳት ዕቅድ ማውጣት የጀመረው ከዚህ አስተያት በኋላ ነው።

የቫግነር ወታደሮች በሮስቶቭ

የፎቶው ባለመብት, EPA

መጀመሪያ የቫግነር ወታደሮች አንድ የሩሲያ ወታደራዊ አዛዥን በማገት አመፃቸውን አንድ ብለው ጀመሩ።

የዩናይትድ ስቴትስ መገናኛ ብዙኃን እንደሚሉት የአሜሪካ ደኅንነት ፕሪጎዢን አንድ ያቀደው ነገር እንዳለ ለፕሬዝደንት ባይደን ያሳወቁት ከአርቡ አመፅ ቀደም ብሎ ነው።

የቫግነር ወታደሮች ከዩክሬን ወደ ሩሲያ አቅንተው መጀመሪያ ሮስቶቭን ቀጥሎም ሌሎች ሁለት ከተማዎችን ከተቆጣጠሩ በኋላ ወደ ሞስኮ ማቅናት ጀምረው ነው ወደኋላ የተመለሱት።

አንዳንዶች እንደሚያምኑት ፕሪጎዢን አመፁን አቋርጦ ወደ ቤላሩስ የገባው ከፑቲን የሥልጣን ለውጥ እንደሚኖር ቃል ተገብቶለት ነው። ነገር ግን ይህን ማረጋገጥ ከባድ ነው።

ሾይጉን እና ጌራሲሞቭን ማን ይተካል የሚለው ሌላኛው ከባድ ጥያቄ ነው።

ጄኔራል አርማጌድዮን በተሰኘ ቅፅል ስማቸው የሚታወቁት በአንድ ወቅት የፕሪጎዢን ወዳጅ የነበሩት ጄኔራል ሰርጌ ሱሮቪኪን ወደላይ ይመጣሉ የሚል ግምት አለ።

ፕሪጎዢን ምን ይጠብቀዋል የሚለው ሌላኛው ምላሽ የሚሻ ጥያቄ ሆኗል።

ሴንት ፒተርስበርግ ውስጥ ካለ የቫግነር ቡድን ቢሮ ውስጥ 38 ሚሊዮን ዶላር ጥሬ ገንዘብ መገኘቱ ተሰምቷል። ፑቲን፤ ግለሰቡ ይህን ገንዘብ እንዲወስድ ይፈቅዱለት ይሆን? አልታወቀም።

ሩሲያ ውስጥ ቅጥረኛ ወታደር ያሏቸው 10 ኩባንያዎች አሉ። እኒህ ኩባንያዎች ከባለሥልጣናት እና ባለሃብቶች ጋር ግንኙነት አላቸው።

የመከላከያ ሚኒስትሩም 'ፓትሪዮት' የተባለ ቅጥረኛ ቡድን እንዳላቸው ይነገራል። ይህ ዩክሬን ውስጥ የሚንቀሳቀስ ቡድን የቫግነር ዋነኛ ተቀናቃኝ ነው ይላል የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ባለሥልጣናት።

እኒህ ቅጥረኛ ቡድኖች ለፑቲን አስተዳደር ያላቸው ታማኝነት ምን ያህል ነው የሚለው ጥያቄ ላይ ወድቋል። አሁን ባለው ሁኔታ የፑቲን መንግሥት ዩክሬን ላይ እያካሄደ ያለውን ጦርነት መቋቋም ይችላል ወይ የሚለውም ሌላው አጠያያቂ ጉዳይ ሆኗል።