ሩሲያ ከአፍሪካ ጋር በሚኖራት ግንኙነት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ምን ሊጠቀሙ ይችላሉ?

የመጀመሪያው የሩሲያ-አፍሪካ ስብሰባ ሩሲያ ሶቺ ውስጥ በተካሄደበት ጊዜ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የመጀመሪያው የሩሲያ-አፍሪካ ስብሰባ ሩሲያ ሶቺ ውስጥ በተካሄደበት ጊዜ

የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የአፍሪካን ተፈላጊነት ይበልጥ ጨምሮታል።

አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና እና ቱርክ ባለፈው ጥር ብቻ ስመ-ጥር ዲፕሎማቶቻቸውን ወደ 14 የአፍሪካ አገራት ልከዋል።

በጦርነቱ ዙሪያ ድጋፍ ማሰባሰብ አንደኛው አጀንዳ ነው። ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ማሳደግ ሌላኛው የጉብኝቱ አካል ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሩሲያን በተመለከተ ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ 17 አገራት በድምጸ ተዓቅቦ አልፈዋል።

ኤርትራ ከተቃወሙት ጎራ ተሰልፋለች። ኢትዮጵያ ደግሞ በድምጸ ተዓቅቦ አልፋዋለች።

ከሰሞኑ ደግሞ የትኩረት አቅጣጫው ከአፍሪካ ወደ ሴንት ፒተርስበርግ ዞሮ ነበር። አሁንም ግን አፍሪካ የዐይን ማረፊያ ሆናለች።

ፓሪስ፣ ዋሽንግተን እና ለንደንን ጨምሮ ብዙ አገራት በንቃት የተከታተሉት ሁለተኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ለሁለት ቀናት ተካሂዷል።

ከመጀመሪያው ጉባኤ አንጻር የተሳታፊ መሪዎች ቁጥር ቀንሷል።

አፍሪካ መሪዎች በዘንድሮው ጉባኤው ላይ እንዳይገኙ ጫና ተደርጎባቸዋል ስትል ሞስኮ ክስ አሰምታለች።

ኢሳያስ አፈወርቂ (ኤርትራ)፣ ሲርል ራማፖሳ (ደቡብ አፍሪካ)፣ አብዱል ፋታህ አልሲሲ (ግብፅ)፣ ዐቢይ አሕመድ (ኢትዮጵያ)፣ ዩዌሪ ሙሴቬኒ (ኡጋንዳ) እና ኤመርሰን ምናንጋግዋ (ዚምባብዌ) ከተሳታፊዎቹ መካከል ነበሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ፕሬዝዳንት ፑቲን በመጀመሪያው የአፍሪካ ሩሲያ ስብሰባ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ፕሬዝዳንት ፑቲን በመጀመሪያው የአፍሪካ ሩሲያ ስብሰባ ላይ

ያልተሳካው ሩሲያን የመነጠል ሙከራ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሩሲያ እና የአፍሪካ ግንኙነት ሁለቱንም አትራፊ የሚያደርግ ነው የሚሉት መቀመጫቸውን ለንደን ያደረጉት የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኙ ዓብዱራህማን ሰይድ አቡ ሐሽም ናቸው።

ሩሲያ የምትፈልገውን የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ከአፍሪካ ታገኛለች። በቀዳሚነት የሚያነሱት ደግሞ ማዕድንን ነው።

የአፍሪካ እና ሩሲያ ግንኙነት ከ100 ዓመት በላይ መሻገሩን የሚያነሱት ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በጀርመን አገር እየተከታተሉ የሚገኙት አቶ ነገራ ጉደታ ናቸው።

ከ50 በላይ የአፍሪካ አገራት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ያላቸውን ድምጽ ትልቅ መሆኑን በማንሳት “[ሩሲያ] በዓለም አቀፍ መድረክ ማዕቀብ ተጥሎ ጫና እንዳይኖርባት እነዚህን ድምጾች ትፈልጋለች” የሚሉት አቡ ሐሽም ጉባኤው ለሩሲያ “ጥሩ የሕዝብ ግንኙነት ነው” ይላሉ።

ከዋና ዋናዎቹ የስንዴ አምራቾች መካከል ጦርነት የገጠሙት ሩሲያ እና ዩክሬን ይጠቀሳሉ። በርካታ የአፍሪካ አገራት ደግሞ ስንዴ ይፈልጋሉ። ይህን መሰሉ ግንኙነት በርካታዎቹን የአፍሪካ አገራትን የሚረዳቸው መሆኑን ይልጻሉ።

ሩሲያ ለተወሰኑ አገራት ስንዴ በነጻ ለመስጠት መወሰኗን ከዚህ የመነጨ ነው ብለው ያስባሉ። ሌሎቹ በዝቅተኛ ዋጋ የሚያገኙበት አጋጣሚ እንደሚኖርም በጥቀስ “በግብርና ዘርፍም ሊተባበሩ ይችላሉ” ይላሉ።

የሩሲያ እና የአፍሪካ ግንኙነት እንደ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ሞቅ ቀዝቀዝ እንደሚል የሚያነሱት አቶ ነገራ፤ ሩሲያ እርዳታ እና መሳሪያ ስትሰጥ ከምዕራባዊያን አንጻር ብዙ ቅድመ ሁኔታ አለማስቀመጧ ተመራጭ አድርጓታል ይላሉ።

በዚህ ሁሉ መሐል በተደረገው ጉባኤ ምዕራባዊያን ሩሲያን በተለይም ፑቲንን ለመነጠል ያደረጉት ጥረት ያልተሳካ መሆኑን ያሳየ ነው ይላሉ አቡ ሐሽም።

ከፈረንሳይ እና ከሌሎች ምዕራባዊያን ተጽዕኖ ይኖራል የሚል ስጋት በግል እንደነበራቸው አስታውቀው “እንደሚመስለኝ ግን ምንም አላስቆሟቸውም። ይህ [ለምዕራባውያን] ትንሽ ውድቀት ሲሆን ለሩሲያ ደግሞ የዲፕሎማሲ እና የሕዝብ ግንኙነት ድል ነው ማለት ይቻላል” ብለዋል።

“ከዚያ አልፎ ብዙም ለውጥ የሚያመጣ አይመስለኝም” ይላሉ።

ለዚህ ምክንያት የሚሉት የበርካታ አፍሪካ አገራት ኢኮኖሚ ከዓለም ባንክ እና ከአይኤምኤፍ ጋር የተጣበቀ መሆኑን ነው። ሁለቱ ተቋማት ደግሞ የአሜሪካ ጫና ያለባቸው መሆኑን ያነሳሉ።

ፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ አገራት ላይ ፓሪስ “ጥብቅ ቁጥጥር አላት” በማለት ለምን ግንኙነቱን ብዙም ለውጥ አያመጣም እንዳሉ ያስረዳሉ።

17 የአገር መሪዎች ብቻ መገኘታቸውን በማንሳት “ጉባኤው እንደተጠበቀው አልነበረም” ያሉት ደግሞ አቶ ነገራ፣ በ2019 በተካሄደው የመጀመሪያው ጉባኤ ከ43 በላይ መሪዎች ተሳታፊ ነበሩ።

የአፍሪካ ተጠቃሚነት

“አፍሪካ መጥፎ ዕድል ሆኖ ኃያላኖቹ የሚከፋፍሏት እና ለጥቅማቸው የሚጠቀሙባት አህጉር ናት” የሚሉት አቡ ሐሽም፤ ሩሲያ፣ ቻይና፣ አሜሪካን ጨምሮ ሌሎችም ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚረባረቡባት አህጉር መሆኗን ይጠቁማሉ።

ተጽዕኖ ለመፍጠር የማይፈንቅሉት ድንጋይ የለም። ስብብሰባ በማካሄድ፣ ድጋፍ በማድረግ፣ ብድር በመስጠት እና በሌላም በሌላም መንገድ “ብዙዎቹ ከቀኝ ወደ ግራ ሊስቧቸው ይሞክራሉ፤ ይህ ይቀጥላል” ይላሉ።

ሩሲያ ደግሞ በመደበኛው ብቻ ሳይሆን በኢ-መደበኛው መንገድ ጭምር እንደምትንቀሳቀስ ቫግነር የተባለውን የቅጥረኛ ተዋጊዎች ቡድንን በመጠቀም “አፍሪካ ውስጥ በወታደራዊ እና በማዕድን ማውጣት ይሳተፋል” ብለዋል።

ከዚህ አንጻር ከሩሲያ ጋር በሚደረገው ግንኙነት አፍሪካ ምን ያህል ትጠቀማለች የሚለው ለአፍሪካ መሪዎች እና ሕዝቦች የሚተው መሆኑን ጠቁመዋል።

ነገር ግን አሜሪካ ብቸኛዋ ኃያል አገር ሆና አፍሪካን ስትዘውር ከነበረችበት ጊዜ አንጻር አሁን አማራጭ በመፈጠሩ “በአንድ በኩል ምቹ ሊሆን ይችላል” ይላሉ።

አገራቱ “ይህን ዕድል ምን ያህል ይጠቀሙታል” የሚለውን ግን ደጋግመው ያነሱታል።

“ዩክሬን ለመስዋዕትነት ቀርባለች”

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ጋር በሚቀርብባቸው ክስ እና በተጣሉባቸው ማዕቀቦች ምክንያት ከዓለም አቀፉ መድረክ ከተነጠሉ ረጅም ዓመታት አስቆጥረዋል።

ከቅርብ ወራት ወዲህ ግን ፕሬዝዳንቱ ወደ ጎረቤት አገራት፣ ሩሲያ እና ቻይና ደጋግመው መመላለሳቸው፣ ፕሬዝዳንቱ ከሩሲያ እና ቻይና ጋር ጥሩ ግንኙነት እየፈጠሩ መሆናቸውን እያሳዩ እንደሆነ አቡ ሐሽም ይገልጻሉ።

ዓለም እየተቀየረ መሆኑን በመረዳት ከሁለቱ አገራት ጋር ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ፍላጎት ያላቸው ፕሬዝዳንቱ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፉት የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ላይ ሞስኮን አወድሰው ምዕራባውያንን አምርረው ወርፈዋል።

ኢሳያስ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ባደረጉት የተናጠል ውይይት “ለእኔ የዩክሬን-ሩሲያ የሚባል ጦርነት የለም ነው የምለው። ይህ ኔቶ በሩሲያ ላይ ያወጀው ጦርነት ነው። ዓለምን በበላይነት ለመቆጣጠር የተከፈተ ነው” ብለዋል።

ምዕራባውያኑ ለዘመናት ቢሞክሩም ሩሲያን “በፍጹም መቆጣጠር እንደማይችሉ” ገልጸው ዩክሬንን “ለመስዋዕት የቀረበች” ሲሉ ገልጸዋታል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም “...ሩሲያ በተደጋጋሚ ዒላማ በመሆኗ ይህን የመሰለ ትልቅ ዓለም አቀፍ ትብብርን የመምራት ድርሻዋን መወጣት ይኖርባታል። ሩሲያ ሁሉንም በመወከል ድርሻዋን የመወጣት ታሪካዊ ተልዕኮ አላት። ይህንን መምራት የሚችሉትም ፑቲን ናቸው” ብለዋል።

ኤርትራ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ውስጥ ከሩሲያ የስንዴ በነጻ እንደሚደርሳቸው ከተጠቀሱ ስድስት የአፍሪካ አገራት አንዷ ናት።

ኤርትራ ከምዕራባውያን ጋር ያላት ግንኙነት ማሽቆልቆሉን የሚናገሩት አቶ ነገራ፤ ይህም አሥመራ ፀረ-ምዕራብ አቋም ካላቸው አገራት ጋር ወዳጅነት እንድትመሰርት እንዳስገደዳት ይገልጻሉ።

ሁለቱ አገራት በቆዳ ስፋት፣ በኢኮኖሚ እና በሕዝብ ብዛት የተለያዩ ቢሆኑም ‘የጋራ ጠላት ስላላቸው’ ግንኙነታቸውን ስትራቴጂያዊ ሳይሆን ታክቲካል መሆኑን ጠቁመዋል።

ሩሲያ ቀይ ባሕር ላይ ለማቋቋም ለምትፈልገው የጦር ሰፈር ኤርትራ ተመራጭ መሆኗን አንስተዋል። ይህ ደግሞ ገቢ እና መሣሪያ ለማግኘት ያስችላታል ይላሉ።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ድምጽን በድምጽ የመሻር ሥልጣን ያላት ሩሲያ ደግሞ ‘ኤርትራ ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎችን ትከላከላለች።’

ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ግንኙነታቸው “የተመጣጠነ አይደለም” ይላሉ።

ማን አሸናፊ እንደሚሆን አይታወቅም

ሩሲያ ከአፍሪካ አገራት ቀድማ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት ከጀመረች 125 ዓመታትን ተቆጥረዋል።

ቭላድሚር ፑቲን በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት ለማሳደግ በቅርቡ አዲስ አበባ ላይ የንግድ ቢሮ መከፈቱን ገልጸዋል።

በኢንፎርሜሽን ደኅንነት፣ የኢንፎርሜሽን እና ቴክኖሎጂ፣ በኒውክለር ኃይል እና የአየር ትራንስፖርት ዙሪያ ለመሥራት መስማማታቸውን ጠቅሰዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት 20 ሺህ ተማሪዎች በሩሲያ የመማር ዕድል ማግኘታቸውን ገለጹት ፕሬዝዳንቱ፣ ሞስኮ በየዓመቱ የምትቀበላቸውን ተማሪዎች ቁጥር ከሦስት እጥፍ በላይ እንደምታሳድግ ገልጸዋል።

ሁለቱ አገራት በዲፕሎማሲ እና በባህል ያላቸውን ቁርኝት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጉባኤው መገኘታቸው ግንኙነታቸውን እንደሚያጠናክርም ተስፋቸውን ገልጸዋል።

በቴክኖሎጂ፣ በሳይበር ደኅንነት፣ በኢኮኖሚ እና በንግድ ላይ በጋራ ለመሥራት እንዲሁም ንግድ እና ቱሪዝም ማስፋፋትን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች በጋራ ለመስራት ከስምምነት ደርሰዋል።

ከኤርትራ አንጻር የኢትዮጵያ እና የሩሲያ ግንኙነት ትልቅ መሆኑን የሚያነሱት አቶ ነገራ፣ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል መሆኗ በዲፕሎማሲ ረገድ ለሩሲያ የምትሰጠው ድጋፍ ትልቅ እንደሆነ ገልጸዋል።

አብዛኛው የአገሪቱ የጦር መሳሪያ የሩሲያ መሆኑን እና ኢትዮጵያ በማቋቋም ላይ ለምትገኘው የባሕር ኃይል ድጋፍ እያደረገች መሆኑንም ያነሳሉ።

በመጀመሪያው የአፍሪካ ሩሲያ ጉባኤ ሞስኮ ኢትዮጵያን ዕዳ ሰርዛ የነበረ ሲሆን፣ በተደጋጋሚም የኢትዮጵያን መንግሥት በመደገፍ ሩሲያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፀጥታው ምክር ቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን ተጠቅማ ከጎኗ ተሰልፋለች።

ከዚህ ባሻገር አቶ ነገራ ስጋት አላቸው፤ ምዕራባዊያን እና ሩሲያ ኢትዮጵያን መፈለጋቸውን አንስተው “በሁለቱ መካከል ስትገባ ፈተኝ ሁኔታ ውስጥ ሊከታት ይችላል” ይላሉ።

“የአሜሪካ ተጽዕኖ እየቀነሰ ነው ቢባልም እንደ ዓለም ባንክ ያሉት ተቋማት በዋሽንግተን ስለሚዘወሩ ኢትዮጵያ የመሃሉን መንገድ ብትከተል ይመረጣል” በማለት ይመክራሉ።

ደርግ ወደ ቀድሞዋ ሶቪዬት ኅብረት በማዘንበሉ ኅብረቱ ሲፈረካከስ ‘ደርግም አብሮ መውደቁን’ አንስተው “ማን አሸናፊ እንደሚሆን ስለማይታወቅ ኢትዮጵያ ወደ አንዱ ካዘነበለች የደርግ ታሪክ ራሱን ሊደግም ይችላል” ብለዋል።

የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እንዲያበቃ ይረዳሉ?

የአፍሪካ አገራት የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትን ለመቋጨት የማደራደር ሚና ወስደው በተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርጉም እስካሁን ግን አልተሳካላቸውም፤ ለአቡ ሐሽም ይህ ወደፊትም የሚሳካ አይመስላቸውም።

ለዚህ ደግሞ ለማደራደር በሁለቱም ወገን ተቀባይነትን ማግኘት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው “የአፍሪካ አገራት እንደዚያ አይደሉም” በማለት ጦርነቱ ለስሙ የዩክሬን እና የሩሲያ ይባል እንጂ የምዕራባውያን እና የሩሲያ ነው ይላሉ።

አፍሪካ አገራት ችግሩን ለመፍታት ካሰቡ ሞስኮ እና ዋሽንግተንን (ምዕራባዊያን ደጋፊዎቿንም) ያካተተ ድርድር እንደሚያስፈልግ ያነሳሉ።

ጦርነቱን በድርድር ለማብቃት አሸማጋይ ለመሆን ከአፍሪካ ይልቅ የተሻለ ዕድል ቱርክ እንዳላት በማንሳት ኢስታንቡልም ብትሆን “የተሳካላት ጦርነቱን ከማስቆም ይልቅ የስንዴ ንግድን በተመለከተ ነው” ብለዋል።