ትኩረት የተነፈገው እና በተደጋጋሚ የሚያገረሸው የጋምቤላ ግጭት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጋምቤላ ክልል ጎሳን ወይም ብሔርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች በተደጋጋሚ ሲከሰቱ ተስተውለዋል። ታጣቂ ኃይሎች በሚፈፅሟቸው ጥቃቶችም በርካቶች ለሞት፣ ለመቁሰል እና ለመፈናቀል ተዳርገዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጋምቤላ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በትጥቅ የታገዙ ግጭቶች ሲከሰቱ መቆየታቸውን እና በዚህ ሳቢያ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየደረሱ መሆናቸውን በቅርቡ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።
ከግንቦት 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ኢታንግ ተብሎ በሚጠራው ልዩ ወረዳ በተወሰኑ ነዋሪዎች መካከል የተነሳ አለመግባባት በፍጥነት ብሔርን መሠረት ወዳደረገ ውጥረት መሸጋገሩን ኮሚሸኑ ከነዋሪዎች መስማቱን ገልጿል።
ከቀናት በፊት በክልሉ በአዲስ መልክ ግጭት ተቀስቅሶ የሰዎች ሕይወት መጥፋቱን ተከትሎ በአጠቃላይ በክልሉ የሚቆይ እና ከሐምሌ 13/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እየሆነ ያለ የሰዓት እላፊ ታውጇል።
በክልሉ ዋና ከተማ የንፁሃን ሰዎች ግድያ እየጨመረ መምጣቱን የሚናገሩት ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ ነዋሪ በተለይም “ኑዌር እና አኙዋክ በሚባሉ ብሔረሰቦች መካከል የተፈጠረው ግጭት ከሁለቱም ወገን ለበርካቶች ሞት” ምክንያት እንደሆነ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
በክልሉ በተፈጠረ ግጭት የሞቱ እና የቆሰሉ እንዲሁም ቤት ንብረታቸውን ጥለው ለመሸሽ የተገደዱ ነዋሪዎች እንዳሉ ተገልፆ ነበር።
የጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋህዴን) ሊቀመንበር አቶ ሳይመን ቱት እንደሚሉት ከመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በተከታታይ በተፈጠሩ ግጭቶች እና በተፈፀሙ ጥቃቶች ምክንያት ከ200 በላይ ሰዎች ሞተዋል።
ባለፈው ዓመት የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ግንባር (ጋሕነግ) እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ሕብረት በመፍጠር ጥቃት ፈፅመው እንደነበረ የሚያስታወሱት አቶ ሳይመን፣ ታጣቂዎቹ የፈፀሙትን ጥቃት ተከትሎም የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል ሲሉ ይከስሳሉ።።
በዚህ ሳቢያ በሕዝቡ ዘንድ ቅሬታዎች በመፈጠራቸው መካረሮች እና ግጭቶች እየተስፋፉ መሄዳቸውን በመግለፅ በንፁሃን ላይ ግድያ እንዲፈፀም ትዕዛዝ የሰጡት “የአኝዋክ ተወላጅ አመራሮች ናቸው”፤ “አይደለም የኑዌር ተወላጆች ናቸው” የሚለው ንትርክም በአመራሮች መካከል ሳይቀር መለያየት ማስከተሉን ይናገራሉ።
በተለይም በአኝዋክ እና ኑዌር ብሔረሰብ ተወላጆች መካከል ከፍተኛ መፋጠጥ እንዳለና፣ አንዱ በሌላኛው ላይ የበቀል እርምጃ እንደሚወስዱ የሚገልፁት አቶ ሳይመን “ከመጋቢት ወር ጀምሮ ለወራት ግጭት ነው። ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ ከሁለት መቶ በላይ ሰዎች ሞተዋል የሚል ግምት አለን” ይላሉ።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጋምቤላ ክልል ያለው የፀጥታ ችግር የመንግሥትን ተጨማሪ ትኩረት የሚሻ መሆኑን ሐምሌ 16/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ማሳሰቡ ይታወሳል።
ኢሰመኮ በጋምቤላ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በትጥቅ የታገዙ ግጭቶች ሲከሰቱ መቆየታቸውን እና በዚህ ሳቢያ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየደረሱ መሆኑንም ገልጿል።
በተጨማሪም ከግንቦት 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ኢታንግ ተብሎ በሚጠራው ልዩ ወረዳ በተወሰኑ ነዋሪዎች መካከል የተነሳ አለመግባባት በፍጥነት ብሔርን መሠረት ወዳደረገ ውጥረት መሸጋገሩን ኮሚሽኑ ጠቅሷል።

የግጭቱ መነሻ
በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኘው የጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን፣ ከኦሮሚያ እና ከደቡብ ክልል ጋር የሚዋሰን ሲሆን፣ አኝዋክ፣ ኮሞ፣ መዠንገር፣ ኑዌር እና ኦፖ የሚባሉ አምስት ብሔረሰቦችም አሉት።
በተጨማሪም ከቀሪው የአገሪቱ ክፍል የተወጣጡ ሌሎች ብሔረሰቦችም የሚኖሩበት ሲሆን፣ በተለያዩ ጊዜያት ብሔርን መሠረት ያደረጉ ተደጋጋሚ ጥቃቶች እና ግጭቶች ታይተውበታል። በተጨማሪም ከደቡብ ሱዳን ሰርገው የሚገቡ ታጣቂዎችም ጥቃት ይፈጽሙበታል።
እንደ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት መረጃ ከሆነ ክልሉ ከ480 ሺህ በላይ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች መጠለያም ነው።
የክልሉ መንግሥት በተከሰተው ግጭት የሞቱም ሆነ የተጎዱ ሰዎችን ቁጥር ባይገልጽም “በሰላም መደፍረሱ እጃቸው ያለበት የሚባሉ አመራሮችም ሆኑ ሌላ አካላት” ተጣርቶ ተጠያቂ እንደሚደርግ ባወጣው መግለጫው ቃል ገብቷል።
ኢሰመኮ በእነዚህ ግጭቶች በሰው እና በንብረት ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ፣ በፀጥታው ችግር ምክንያት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በክልሉ ውስጥ የወደሙ መንገዶች መኖራቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል ብሏል።
ከጥቂት ቀናት በፊት ተከስቶ በነበረ ግጭት ምክንያት የሰው ሕይወት ማለፉን እና በንብረት ላይም ጉዳት መድረሱን የክልሉ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡገቱ አዲንግ በሰጡት መግለጫ ላይ አስታውቀዋል።
በእርግጥ ኃላፊው በዚህ መግለጫቸው ምን ያህል ሰው እንደሞተ እና እንደቆሰለ፣ የወደመው ንብረትም ምን ያህል እንደሚገመት ከመናገር ተቆጥበዋል።
ከዚህ ቀደም ለሁለት ሦስት ቀናት ብቻ የሚቆይ ግጭት በዘር አልያም፣ በደም መመለስ ምክንያት ያገጥም እንደነበረ የሚያስረዱት ቢቢሲ ያነጋገራቸው የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ፣ ከጥቂት ቀናት በፊት የተከሰተው ግን “የከረረ” እንደሆነ ገልፀዋል።
ሁኔታው ከብሔር ጥያቄ ባሻገር ወደ ግዛት ጉዳይ እየተሻጋገረ ያለ እንደሚመስል እና ከደቡብ ሱዳን በኩልም ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው በመግባት በኢታንግ እና ላሬ መካከል ከአኝዋክ ብሔረሰብ ጋር የተኩስ ልውውጥ እንደሚያደርጉ ጨምረው ያስረዳሉ።
እሳቸው እንደሚሉት በቅርቡ የተከፈተውን ግጭት ተከትሎ መከላከያ ሠራዊት በመሃል ገብቶ ለማረጋጋት ሞክሯል።

የፎቶው ባለመብት, GAMBELLA TOURISM
ስደተኞች እና ግጭት
በክልሉ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳለ እና ለግጭቶቹ መባባስ ምክንያት እንደሆነ ፖለቲከኛው እና የክልሉ ነዋሪ ይናገራሉ።
ነዋሪው የፌደራል መንግሥት በክልሉ የሚፈጠሩ ግጭቶችን በጥልቀት በመመርመር በጊዜ መፍትሄ መስጠት አለመቻሉ ሲደጋገም የመጣው ችግር አሁን ካለበት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ይላሉ።
“ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ ከፍተኛ የስደተኞች ቁጥር ነው ያለው። በጋምቤላ ያለ ስደተኛ ከ480 ሺህ በላይ ይሆናል። አብዛኞቹ ስደተኞችም የኑዌር [ከደቡብ ሱዳን የመጡ] ተወላጆች ናቸው። ስለዚህ ግጭት ሲፈጠር ስደተኞቹ ወደ ከተማ በብዛት ስለሚገቡ ከነዋሪው ጋር ይቀላቀላሉ” በማለት ይህም ለችግሩ መባባስ አስተዋፅኦ እንዳለው አስረድተዋል።
የስደተኞች ቁጥር ከክልሉ አቅም በላይ መሆኑን የሚገልፁት እኝህ ነዋሪ፣ እነዚህ የኑዌር ተወላጅ የሆኑ ስደተኞችም የአኝዋክ ብሔር ተወላጆች በብዛት በሚኖሩበት አካባቢ በመጠለላቸው ለማያቋርጥ ግጭት ምክንያት እንደሚሆን ያላቸውን ግምት ያስቀምጣሉ።
ከዚህ በተጨማሪም የብሔር ልዩነቶች ለግጭት መነሻ እንደሚሆኑ የሚናገሩት አስተያየት ሰጪው “የክልሉ ፕሬዝዳንት የአኙዋክ ተወላጅ ሲሆኑ ምክትሉ ኑዌር ናቸው። በዚህም ምክንያት ኑዌሮች ፕሬዝዳንት መሆን አለብን የሚል ሽኩቻ አለ። ስለዚህ የሥልጣን እና ጥቅማ ጥቅም ጉዳይ በብሔሮቹ መካከል የተካረረ ልዩነት ፈጥሯል” ይላሉ።
በስደተኞች ምክንያት ግጭቶች ይነሳሉ እንዲሁም በግጭቶች ውስጥ ተሳትፈዋል በሚለው ላይ ተጨባጭ መረጃ እንደሌላቸው የሚናገሩት የጋህዴኑ ሊቀመንበር አቶ ሳይመን በበኩላቸው፣ ክልሉን በፕሬዝዳንትነት የመምራት ጉዳይም በሁለቱም ብሔሮች መካከል የፍጥጫ ምክንያት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ፓርቲያቸው ሐምሌ 16/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይም “በክልሉ የሚገኙ የገዢው ፓርቲ ብልፅግና ሹመኞች የብሔር ግጭት እንደ ፖለቲካ መሳርያ እየተጠቀሙ መሆናቸውን” ማስቀመጡ አስታውሰዋል።
በክልሉ ያሉ የብልፅግና ሹመኞች ከዚህ ግጭት ማትረፍ የሚፈልጉት ነገር ቢኖር “የራሳቸውን ፓርቲ ስም ማጠልሸት ነው” ይላሉ የጋህዴኑ መሪ።
የክልሉ መንግሥት ግጭቶች ማጋጠማቸውን እና ጥቃቶች መፈፀማቸውን ቢገልፅም፣ በእነዚህ ጊዜያት የተከሰቱ ችግሮች ምክንያት ግን ምን ያህል የሰው ሕይወት እንደጠፋ፣ ስንቶች እንደቆሰሉና እንደተፈናቀሉ በግልፅ የሚያስቀምጠው መረጃ የለም።
ከጥቂት ቀናት በፊት የጋምቤላ ክልላዊ ምክር ቤት ባካሄደው ስብሰባ ከሕዝብ ተወካዮች መካከል ለፕሬዝዳንቱ ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን፣ ከግጭቶች እና ጥቃቶች ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጥያቄዎችም እንደተነሱ የክልሉ ፕሬስ ሴክረታሪያት ጽህፈት ቤት በፌስቡክ ገፁ ላይ ባወጣው መረጃ ላይ ጠቁሟል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በጋምቤላ እና በሌሎችም አካባቢዎች ሰዎች መገደላቸውን ጠቅሰው “በክልሉ ሰላም እንዳይሰፍን የሚሰሩ አካላት የብሔር ዋሻ ስር በመደበቅ ሰዎችን እያጋደሉ እና ጽንፈኝነትን እየሰበኩ” መሆኑን መናገራቸው ተዘግቧል።
ችግሩን የሚያባብሱም ሆነ እጃቸው ያለበት አካላትን ተጠያቂ የማድረግ ተግባር እየተካሄደ እንደሚገኝ ርዕሰ መስተዳድሩ በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ማሳወቃቸው ተገልጿል።
በክልሉ የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል የግምገማ መድረክ በጋምቤላ ከተማ መካሄድ መጀመሩ የጋምቤላ ብልፅግና ፓርቲ በፌስቡክ ገፅ ላይ ባወጣው አጭር መረጃ አስታውቋል።
ቢቢሲ በጋምቤላ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ከክልሉ ባለሥልጣናት ተጨማሪ መረጃ እና ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።












