የጋናው ብሔራዊ ባንክ በአንድ ዓመት ውስጥ 5 ቢሊዮን ዶላር እንዴት ሊያጣ ቻለ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ምዕራባዊቷ አፍሪካዊት አገር ጋና በአንድ ወቅት የአፍሪካ ምጣኔ ሃብት ስኬት ማሳያ ተብላ ትጠራ ነበር።
ሌሎች በጦርነት ሲናጡ ጋና በተረጋጋ ሁኔታ የምጣኔ ሃብቷ መመንደጉ በበርካታ ዓለም አቀፍ የምጣኔ ሃብት ጉባኤዎች ላይ ስሟ እንዲጠራ አድርጓታል።
በአሁኑ ወቅት ጋና ከዚህ ቀደም አይታው የማታውቀው የገንዘብ ቀውስ አጋጥሟታል።
ቀውሱን ዝም ብለው ያልተመለከቱት ጋናውያን ተቃውሟቸውን አደባባይ ወጥተው አሰምተዋል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች በመዲናዋ አክራ ጎዳናዎች ላይ በመውጣት የጋና ባንክ ገዢ እና ምክትሎቻቸው ሥራቸውን እንዲለቁ ጠይቀዋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዢ እና ምክትሎቻቸው ባለፈው ዓመት 60 ቢሊዮን ሲዲ [የጋና መገበያያ ገንዘብ] ወይም 5.2 ቢሊዮን ዶላር አጥፍተዋል በሚልም ነው ከኃላፊነታቸው እንዲለቁ እየተጠየቁ ያሉት።
‘የጋናን ባንክ መቆጣጠር’ (ኦኩፓይ ባንክ ኦፍ ጋና) በሚል የተጠራውን የታቃውሞ ሰልፍ የመራው የአገሪቱ ተቀናቃኝ ፓርቲ ናሺናል ዲሞክራቲክ ኮንግረስ (ኤንዲሲ) ነው።
ተቃዋሚዎቹ “ዘረፋው ይቁም እኛ እየተሰቃየን ነው” በሚልም መፈክሮችን ሲያሰሙ ተደምጠዋል።
ባንኩ ለመንግሥት ብድር ለመስጠት ሲል በሕገወጥ መንገድ ገንዘብ አሳትሟል ሲሉ ተቃዋሚዎች ይወቅሱታል።
ይህም ሁኔታ የአገሪቷ መገበያያ ገንዘብ አቅም እንዲያሽቆለቁል እና የዋጋ ግሽበት እንዲፈጠር አድርጓል ይላሉ።
ሌላኛው ባንኩ የሚተችበት ለአገር እና ለውጭ ጉዞ ከ762 ሺህ ዶላር በላይ ወጪ አድርጓል፣ እንዲሁም አዲስ ሕንጻ ለመገንባት 250 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጉን በመጥቀስ ነው።
ተቃዋሚዎች ባንኩ ያወጣቸው ወጪዎች በሙሉ በባንኩ የውስጥ ኦዲት ውስጥ ተመዝግበዋል ይላሉ።
ፓርቲው የማዕከላዊ ባንክ ገዢ የሆኑት ዶ/ር ኧርነስት አዲስ ግዴለሽነት አሳይተዋል እንዲሁም በብልሹ አስተዳደርም እየከሰሳቸው ይገኛል።
ባንኩ ከዚህ ቀደም በብልሹ አስተዳደር ቢከሰስም ይህን ያህል መጠን ያለው ገንዘብ ግን አጥቶ አያውቅም።
“ይህንን የመሰለ ነገር በታሪካችን አይተን አናውቅም። የጋና ባንክ ከዚህ ኪሳራ እንዲያገግም ከተፈለገ ከ45 ዓመታት በላይ ይፈጅባቸዋል” ሲሉ የጋና ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሃብት ፕሮፌሰር ጎድፍሬድ ቦክፒን ይናገራሉ።
ባንኩ በበኩሉ ኪሳራው የተከሰተው በብልሹ አሰራር አይደለም ይላል። እንደ ባንኩ ከሆነ ኪሳራው የተከሰተው ተለዋዋጭ በሆነ የምንዛሪ ሥርዓት እና የመንግሥት ተቋማት የማይከፈል ብድር በመውሰዳቸው ነው።
ከእነዚህ በተጨማሪም የጋና መንግሥት 700 ሚሊዮር ዶላር ተበድሮ ሙሉ በሙሉ ባለመመለሱ ለችግሩ መባባስ አስተዋጽኦ አድርጓል ይላሉ።
የባንኩ ገዢዎች በተከተሉት የገንዘብ ፖሊሲ በአገሪቱ ከፍተኛ የዋጋ ግሸበት እንዲመጣ እና የምጣኔ ሃብት ቀውሱን በማባባስ እየተወነጀሉ ይገኛሉ።
“ለመንግሥት በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ሲያሳትሙ ምን አይነት ውጤት እንደሚያስከትል አያውቁም ነበር?” ሲሉ የሕግ ባለሙያው ማርቲን ኬፕቡን ይጠይቃሉ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ይህ ለምን ተከሰተ?
ጋና በአሁኑ ወቅት ትውልዱ አይቶት በማያውቅ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች።
ባለፈው ዓመት የዋጋ ግሽበቱ 54 በመቶ ሆኖም ተመዝግቧል።
ይህ በአገሪቱ ከፍተኛ አሃዝ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም ከ40 በመቶ በላይ ነው።
አገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመበደር አቅሟም እንደወረደ የብድር ተቋማት ደረጃዋን ዝቅ አድርገዋል።
ይህም ሁኔታ አገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ገንዘብ የመበደር አቅሟን አውርዶታል።
የጋና አጠቃላይ ዕዳ ሲታይ ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ላይ ወደ 55 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ማለቱ ታይቷል። ይህም ማለት መንግሥት ዕዳውን ለመክፈል ከገቢው 70 በመቶ በላይ ያስፈልገው ነበር።
ሆኖም ይህንን ማድረግም አልተቻለም። ጋና በተያዘላት ወቅትም ዕዳዋን መክፈል አልቻለችም። መንግሥት እርዳታ ለማግኘት ዓለም አቀፉን የገንዘብ ተቋም - አይኤምኤፍን መጠየቅ ነበረበት።
ጋና በዚህ የአውሮፓውያን ዓመት 3 ቢሊዮን ዶላር ብድር ለማግኘት ተቋሙ ያቀረባቸውን በርካታ መስፈርቶችን ለማሟላት መስማማትን መርጣለች።
ከእነዚህ ውስጥም አንዱ የአገሪቱ የዕዳ ወለድ ክፍያ በአውሮፓውያኑ 2028 መከፈል ወደሚችልበት ደረጃ መቀነስ ነው።
ይህም የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት በተረጋጋ ሁኔታ ለመምራት የሚያስችል በቂ ገንዘብ እንዲኖርም ያደርጋል የሚል እሳቤን ይዟል።
ይህንንም ለማሳካት የጋና መንግሥት የብድር ሸግሽግን አስመልክቶ ከአበዳሪዎች ጋር እንደገና መደራደር፣ በመንግሥት ብድር ላይ ዝቅተኛ የወለድ መጠንን የማስቀመጥ ሃሳብን አቅርቧል።
በተጨማሪም በሕዝብ ፋይናንስ ላይ ያለውን ጫና ለማቃለል ረዘም ያለ የብድር የመክፈያ ጊዜን የያዘ የድርድር ሃሳብ አቅርቧል።
ሆኖም አንዳንድ አበዳሪዎች በዚህ የመንግሥት ፕሮግራም ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ አልሆኑም።
ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ መንግሥት የአይኤምኤፍን መስፈርት ለማሟላት በቂ ገንዘብ እንደሌለው እና በዚህም ምክንያት ከባንኩ የተበደረውን 700 ሚሊዮን ዶላር ግማሹን እንደማይከፍል በመግለጽ የጋና ባንክ መግለጫ አወጣ።
መንግሥት ከባንኩ የተበደረው ገንዘብ ዕዳውን ለማሸጋሸግ እንደሚውል እና ለባንኩ ምንም አይነት ወለድም እንደማይከፍል ተናግሯል።
የአገሪቱ ባንክ በፖሊሲ ደረጃ ለመንግሥት የመጨረሻው አማራጭ አበዳሪ ቢሆንም ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ አዶ የሚመሩት መንግሥት ከዚህ ተቃርኗል ይላሉ።
መንግሥት ባንኩን እንደበዘበዘ እና የባንኩን ሕግጋት እንደጣሰ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
“የጋና ባንክ ሕግ በጣም ግልጽ ነው። ገንዘብን ማተም ወይም ለመንግሥት የገንዘብ ድጋፍ የሚደረገው ከባንኩ ገቢ በ5 በመቶ ብቻ የተገደበ ነው። ይህም ማለት በመርኅ ደረጃ መንግሥትን መደገፍ ወንጀል ባይሆንም፣ ነገር ግን ከ5 በመቶ በላይ መሄድ አይቻልም” ይላሉ ፕሮፌሰር ቦክፒን።
መንግሥት ከ5 በመቶ ገደብ ካለፈ የባንኩ ኃላፊዎች ለፓርላማ ሪፖርት እንዲያቀርቡ ሕጉ ደንግጓል። ይህንን ሪፖርት አለማድረግ የገንዘብ መቀጮ ወይም ከሁለት ዓመት የማይበልጥ እስራት ሊያስቀጣ ይችላል።

የፎቶው ባለመብት, WPA POOL
ይህ ማለት የጋና ባንክ ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ከስሯል ማለት አይደለም።
ማዕከላዊ ባንኩ የተቋቋመው እንደ ንግድ ባንኮች ትርፍ ለማግኘት አይደለም። ስለዚህ ኪሳራው በመደበኛ ሥራው ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር አይገባም።
ባንኩ እንደ መጨረሻ አበዳሪነቱም የራሱን ገንዘብም ማምጣት ይችላል።
ነገር ግን የማዕከላዊ ባንኩ ኪሳራ በአገሪቱ ላይ ቀውሶችን እንደሚያስከትል ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ባንኩ የጋናን የንግድ ባንኮች የመቆጣጠር የሞራል ከፍታ አይኖረውም። እንዲሁም በአገሪቱ የፋይናንስ ሥርዓት ላይ ያለውን መተማመንም እጅጉኑ ይሸረሽረዋል።
ምንም እንኳን በዓለም ዙሪያ ያሉ ሌሎች ማዕከላዊ ባንኮች ተመሳሳይ ፈተናዎች ቢያጋጥማቸውም የጋናን ልዩ የሚያደርገው ግን አገሪቷ ያላት የምጣኔ ሃብት ከጠፋው ገንዘብ ጋር ሲነጻጸር ነው።
ለምሳሌ በዩናይትድ ኪንግደም የእንግሊዝ ማዕከላዊ ባንክ በሚቀጥሉት ዓመታት ውስጥ 180 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የሚያጣ ሲሆን፣ ይህም በዩናይድ ኪንግደም መንግሥት በሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ ይሸፈናል።
የዩናይትድ ኪንግደም ምጣኔ ሃብት በትሪሊዮን ዶላር የሚቆጠር ነው።
የጋና ባንክ የደረሰበትን ኪሳራ ከሌሎች አገራት ጋር ማወዳደር ተገቢ እንዳልሆነም የማኅበራዊ ፈጠራ ባለሙያ እና ደራሲው ብራይት ሲሞንስ ይናገራሉ።
“የደረሰባቸውን ኪሳራ በሌሎች ማዕከላዊ ባንኮች ላይ እጃቸውን በመቀሰር እና አቅጣጫ ለማስቀየር የሚያደርጉት ሙከራ ትርጉም የለውም። የደረሰባቸው የኪሳራ መጠን ከሌሎች አቻ ባንኮች ጋር ሲወዳደር እጅግ የላቀ ነው” ይላሉ።
“አብዛኛው ብልሽት የተፈጠረው ባንኩ የመንግሥት ልቅ የፊሲካል ፖሊሲን በመቀበሉ” እንደሆነም ያስረዳሉ።
በሌላ አነጋገር ባንኩ ገንዘብ በማተም (በማምጣት) መንግሥት ከአቅሙ በላይ እንዲሆን አድርጎታል።
በሕዝቡ ላይ የሚኖረው ተጽእኖ
የዓለም ባንክ ባለፈው ወር ባወጣው ሪፖርት 850 ሺህ የሚሆኑ ጋናውያን በከፍተኛ የዋጋ ግሸበት ምክንያት ወደ ድህነት ገብተዋል።
የጋናውያን ገቢም በመሸርሸሩ የመግዛት አቅማቸውም በከፍተኛ ሁኔታ አሽቆልቁሏል።
የምግብ፣ የነዳጅ እና ሌሎች የፍጆታ ሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ንሯል። በርካቶች የቀን ተቀን ኑሯቸውን ለማሸነፍ እና የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን እየታገሉ ይገኛሉ።
ከሁሉም በላይ የአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ በአገር ውስጥ እንዲሁም በአይኤምኤፍ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። በአይኤምኤፍ ብድር ውል መሠረት መንግሥት ተጨማሪ ገንዘብ ከጠየቀ ባንኩ ከመከልከል ውጪ ሌላ አማራጭ አይኖረውም።












