የውጭ ባንኮች መግባት አገር በቀል ባንኮችን ያከስማቸዋል? ለተጠቃሚውስ ምን ይዞ ይመጣል?

የኢትዮጵያ ባንዲራ እና ሳንቲም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ለውጭ አገር ባንኮች አዲስ አይደለም። ባንኮ ዲ ሮማ እና አቢሲኒያ ባንክን መጥቀስ ይቻላል።

ቢሆንም ላለፈው ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የኢትዮጵያ ገበያ እንደ ባንክ እና ቴሌኮም ያሉ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ለውጭ አገር ኢንቨስተሮችና ለግል ባለሀብቶች ዝግ አድርጎ ቆይቷል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በፈረንጆቹ 2012 በዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ ቀርበው ኢትዮጵያ ባንክ እና ቴሌኮምን “ክፍት የምታደርግበት አቅም የላትም” ሲሉ ጠንከር ያለ ንግግድ አድርገው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ “አይደለም እኛ ልንቆጣጠራቸው፤ ልንረዳቸው የማንችላቸው መሳሪያዎች ነው የሚጠቀሙት። እንዴት ብለን ነው ታዲያ የምንቆጣጠራቸው? አይቻልም፤ አሁን አቅሙ የለንም” የሚል ንግግር አሰምተው ነበር።

ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትሩን አቋም የሚደግፉት የመኖራቸውን ያህል ከዓለም ገበያ ተነጥለን መቆየት አንችልም ብለው የሚከራከሩም አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ በመንግሥት እጅ ያሉ ተቋማት ቤቶች ለሽያጭ ሊቀርቡ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተው ነበር።

መንግሥት ይህን ለማድረግ የወሰነው ተጨማሪ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ እና በግብርና ላይ የተመሰረተው የአገሪቱ ምጣኔ ሐብትን ለማዘመን በሚል እንደሆነ ይነገራል።

በተጨማሪም ይህ እርምጃ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት በማቀላጠፍ፣ በሥራ ፈጠራ እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት በማጎልበት ለምጣኔ ሐብት ዕድገት አስፈላጊ ነው ተብሎ ታምኗል።

እነሆ የቴሌኮም ዘርፉ ለውጭ አገር ኢንቨስተሮች ክፍት መሆኑን ተከትሎ የባንኩ ኢንዱስትሪ ለውጭ አገር ባንኮች ክፍት እንዲሆን ተወስኗል።

ባለፈው የካቲት ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር “ባንኮች በዘመናዊ መንገዶችና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ከዓለም ዕድገት ጋር የሚጓዝ እንዲሁም ከሌሎች አገራት ባንኮች ጋር ለመወዳደር የሚያበቃ ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል” ብለው ነበር።

ብሔራዊ ባንክ ይህንን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ እንዲያስችለው የባንክ ፖሊሲ፣ ሕግጋት እና ደንቦችን ሲያሻሽል ቆይቷል።

ማሻሻያው የውጭ ባንኮች በቅድሚያ በሽርክና ሥራ እንዲጀምሩ የሚያስችል ዝቅተኛ ካፒታል ማዘጋጀትን ያካትታል።

ለመሆኑ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ለአገር በቀል ባንኮች ስጋት ይሆን? ለተጠቃሚውስ ምን ይዘው ይመጣሉ?

ግራፍ

ምን ይዘው ይመጣሉ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በርካታ የአፍሪካ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ለመዝለቅ ፍላጎት እያሳዩ እንደሆነ የማዕከላዊ ባንክ አስተዳዳሪ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ከወራት በፊት ተናግረው ነበር።

ባለፉት ዓመታት የተለያዩ የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ጽህፈት ቤት ከፍተው የአገሪቷን ገበያ እያጤኑ እንደሆነ የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ።

‘ፋርዘር አፍሪካ’ የተባለ ድረገጽ በ2020 ባወጣው መረጃ እ.ኤ.አ ከ2015 ጀምሮ በኢትዮጵያ ዘጠኝ የውጭ ባንኮች ወኪል ጽህፈት ቤት ከፍተዋል።

የፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ ግሎባል ሊቀመንበር ዘመዴነህ ንጋቱ “አዋጁ ትልቅ እርምጃ ነው” ይላሉ።

ዘርፉን ክፍት ያደረጉ የሌሎች አገራትን ተሞክሮ ልምድ የሚወጠቅሱት የፋይናንስ ባለሙያው፤ በአጠቃላይ አገራዊ ምርት [ጂዲፒ] ከሰሃራ በታች ከናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ቀጥላ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ዘርፉ መክፈቷ “ለቢዝነስ ዝግጁ መሆኗን የሚያሳይ ነው” ይላሉ።

“የውጭ ባንኮች ሲመጡ ዓለም አቀፍ ልምዳቸውን ይዘው ነው የሚመጡት። የማኔጅመንት [አስተዳደር] ልምዳቸውን፣ ቴክኖሎጂያቸውን፣ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ይዘው ይመጣሉ። ከውጭ የሚመጣን ኢንቨስተር የማስተናገድ አቅም አላቸው።”

ዘመዴነህ ባንኮቹ ለደንበኞቻቸው የሚያቀርቡት አገልግሎትንም እንደ አንድ ጥቅም ያወሳሉ።

“ለምሳሌ በአሜሪካ ባንኮች ደንበኞቻቸውን በጣም ይንከባከባሉ። እኛ አገር ተጠቃሚው ባንኩን ለምኖ ነው የሚጠቀመው። የተገላቢጦሽ ነው። የሚያበድሩትም ለተወሰነ ሰው ነው።”

የዩናይትድ ኪንግደም የተመሰከረላቸው የሒሳብ አዋቂዎች ማኅበር አባል የሆኑት የማማከር እና ኦዲቲንግ ባለሙያው ጥላሁን ግርማ፣ በተመሳሳይ የውጭ አገር ባንኮች ወደ አገር ቤት መምጣታቸው አንደኛው ጥቅሙ የውጭ ኢንቨስተሮችን መሳባቸው ነው ይላሉ።

“በሩ ለውጭ አገር ባንኮች መከፈቱ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እንዲስፋፉ ያደርጋል፤ አዳዲስ የባንክ አገልግሎቶች ለደንበኞች እንዲዳረሱ መንገድ ይፈጥራል፤ የአገር ውስጥ ባንኮች በቂ ፋይናንስ ይሰጡኛል ብለው የማይተማመኑ የውጭ አገር ኢንቨስተሮችን ሊጋብዝ ይችላል።”

አማካሪው “ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲቲባንክ አሊያም ስታንዳርድ ቻርደተርድ ቢገባ የውጭ አገር ኢንቨስተሮች ጥናት ሲሰሩ አንደ አንድ መልካም ጎን ያዩታል” ሲሉ ያክላሉ።

ነገር ግን አቶ ጥላሁን እንደሚሉት ኢትዮጵያ የባንኩን ኢንዱስትሪ ለውጭ ባንኮች የከፈትችው ከዓለም አቀፍ ተቋማት በደረሰባት ጫና ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ።

“የዓለም ንግድ ድርጅት አንደኛው መመዘኛው አገራት የንግድና አገልግሎት መሣለጥን ማገድ የለባቸውም የሚል ነው። ስለዚህ ጫናው በዋናነትነ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትና ከዓለም ንግድ ድርጅት የመጣ ነው” ሲሉ ይከራከራሉ።

ዘመዴነህ፤ ዓለም አቀፍ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ከአገር በቀል ባንኮች ጋር የመሥራት ዕድል ስላላቸው ቴክኖሎጂው ይሸጋገራል ይላሉ።

ቢሆንም የሒሳብ አማካሪው ጥላሁን የአገር ውስጥ ባንኮች ከቀድሞው በተሻለ የካፒታልና የቴክኖሎጂ ደረጃ ላይ ቢሆኑም ገና በጣም ብዙ እንደሚቀራቸው ይናገራሉ።

ታድያ የኢትዮጵያ የግል ባንኮች ይህንን ፉክክር እንዴት መግጠም ይችላሉ?

የአገር ውስጥ ባንኮች መቀመጫ የሆነው የአዲስ አበባ አካባቢ በምሽት

የፎቶው ባለመብት, addis ababa mayor office

የምስሉ መግለጫ, የአገር ውስጥ ባንኮች መቀመጫ የሆነው የአዲስ አበባ አካባቢ በምሽት

አገር በቀል ባንኮች ምን ተስፋ አላቸው?

የውጭ ባንኮች እንዲገቡ መፈቀዱ ለአገር በቀል ባንኮች “መልካም አጋጣሚ” ነው የሚሉት ዘመዴነህ ንጋቱ፣ “የአገር ውስጥ ባንኮች አትራፊ ቢሆኑም በዓለም አቀፍ ደረጃ የመወዳደር ልምድ የላቸውም። እነዚህ የውጭ ባንኮች በሚመጡበት ጊዜ አብረው የመሥራት ዕድል ይኖራቸዋል” የሚል መከራከሪያ ያስቀምጣሉ።

መንግሥት አገር በቀል ባንኮች አዲሱን ፖሊሲ ተከትሎ ተፎካካሪ ሆነው መቀጠል የሚሹ ከሆነ መዋሃድ አለባቸው የሚል ሐሳብ ይሰጣል።

ዘመዴነህ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ።

ለበርካታ ዓመታት ኧርንስት ኤንድ ያንግ ከተሰኘው ኩባንያ ጋር የሠሩት ዘመዴነህ፤ “ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ትልቁ የግል ባንክ የሆነው አዋሽ ባንክ በአፍሪካ ደረጃ እንኳ 83ተኛ ደረጃ ላይ ነው የተቀመጠው” በማለት ባንኮች መጣመር እንዳለባቸው ያሰምራሉ።

“በዘርፉ ባንኮች የሚኖራቸው አቅም ትልቅ ዋጋ አለው። 18 ባንኮች አሉን፤ በቅርቡ ሦስት፣ አራት ሊጨመሩ ይችላሉ። 10 ገደማ ደግሞ ፈቃድ እየጠበቁ ነው። ይህ ጨርሶ አስፈላጊ አይደለም። በእኔ ግምት የዛሬ አንድ ዓመት ተኩል 5 ትላልቅ አቅም ያላቸው የግል ባንኮች ይኖራሉ።”

ባንኮች ቢዋሃዱ የማበደር አቅማቸው ከፍ ይላል፣ ቴክኖሎጂያቸው ያድጋል፣ አልፎም ውጭ ባንኮች ቢመጡም የመቋቋም አቅም ይኖራቸዋል ይላሉ።

ናይጄሪያን በምሳሌነት የሚጠቅሱት አማካሪ እና ኦዲተሩ ጥላሁን “መጀመሪያ በውዴታ እንዲዋሃዱ ሊደረግ ይችላል፤ አሊያም አቅም ያለው አቅም የሌለውን ሊጠቀልል ይችላል” የሚል ትንበያ አላቸው።

የውጭ ባንኮች ሲገቡ አገር በቀል ባንኮች ሊከስሙ ይችላሉ የሚለውን ስጋት በተመለከተም “የኢትዮጵያ ባንኮች ይጠፋሉ የሚል ግምት የለኝም። ‘ኮርፖሬት’ ደንበኞቻቸውን ይነጠቃሉ? አዎ!” ይላሉ አቶ ጥላሁን።

“መሳሳት የሌለብን እነዚህ የውጭ ባንኮች ገጠር ድረስ ዘልቀው በዝቅተኛ ደረጃ [ሪቴይል ባንኪንግ] ይሠራሉ ተብሎ አይታሰብም።”

ዘመዴነህ ከባንኮች መዋሃድ በተጨማሪ ‘ጆይንት ቬንቸር’ የተሰኘው የኢኮኖሚ ሥርዓት መተግበር ቢችል አዋጭ ነው ባይ ናቸው።

“ለምሳሌ ቻይና መጀመሪያ ባንኮች ሲገቡ ‘በጆይንት ቬንቸር’ እንዲገቡ ነው የፈቀደችው። ይህ ማለት የውጭ ባንኮች የተወሰነ ድርሻ ገዝተው እንዲገቡ ማድረግ ማለት ነው።”

ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ባንኮች ድርሻ ገዝተው አብረው መሥራት ቢችሉ የማደግ ጥሩ ዕድል ይኖራቸዋል የሚል ሐሳብ አላቸው።

አገር በቀል ባንኮች አይጠፉም ሲሉ የሚከራከሩት ጥላሁን የውጭ ባንኮች ትኩረታቸውን በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ እና ሌሎች ትላልቅ ከተሞች ላይ ስለሚያደርጉ፣ አገር በቀል ባንኮች የተቀረውን ማኅበረሰብ ማገልገል ይችላሉ ይላሉ።

“በፖሊሲ ካላስገደድናቸው በቀር ሥራቸውን የሚሠሩት በአንድ ዋና መሥሪያ ቤት፤ የተቀረውን ደግሞ በቴክኖሎጂ በማስተሳሰር እንጂ፣ እንደኛ ባንኮች በየመንደሩ ቅርንጫፍ ይከፍታሉ ተብሎ አይታሰብም።”

አማካሪው ‘ኮርፖሬት ደንበኛ’ የተሰኘውን ሐሳብ ደጋግመው ያነሳሉ። ለመሆኑ ኮርፖሬት ደንበኛ ምን ማለት ነው?

“በባንክ ኢንዱስትሪ 20/80 የሚባል ነገር አለ። 20 በመቶው ለባንኮች ትልቅ የውጭ ምንዛሬ የሚያመጡ ናቸው። የውጭ ባንኮች እነዚህን ደንበኞች ለመንጠቅ አሰፍስፈው እንደሚመጡ ምንም ጥርጥር የለኝም። ዒላማቸው ‘ኮርፖሬት’ ደንበኛ ናቸው እንጂ ታች ወርደው ብድር ይሰጣሉ ብሎ ማሰብ ስህተት ነው።”

ጥላሁን፤ “ለዚህ ነው ለውድድር እንዲመቻቸው መዋሃድ ይኖርባቸዋል የምለው፤ ብሔራዊ ባንኩም ሰላሳ አርባ ባንክ መቆጣጠር አይጠበቅበትም” ይላሉ።

ባለሙያው፤ የብሔራዊ ባንክ የባንኮችን ‘ካፒታል’ አሁን ካለበት በቅርቡ ከፍ ሊያደርገው የሚችል ሲሆን፣ “ይህንን ለማሟላት ደግሞ አገር በቀል ባንኮች ያላቸው አማራጭ መዋሃድ ብቻ ነው።”

ግራፍ

“የውጭ ባንኮችን ለማስገባት ጊዜው አይደለም”

በምጣኔ ሃብት ጉዳዮች የተለያዩ ጽሑፎችን በማቅረብ የሚታወቁት የኩዌት ኢንስቲትዩት ፎር ሳይንቲፊክ ሪሰርች ተመራማሪው አየለ ገላን (ዶ/ር) የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ መፈቀዱን አጥብቀው ከሚቃወሙ መካከል ናቸው።

“ይህ ውሳኔ የራስ ምታት ላለበት ሰው የሆድ ቁርጠት መድኃኒት እንደመስጠት ነው” የሚሉት የምጣኔ ሃብት ምሁሩ፣ የባንክ ኢንዱስትሪውን ለውጭ ባንኮች ክፍት ማድረግ “አገር ውስጥ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘብ አይደለም” ይላሉ።

እንደ አየለ ገለፃ የኢትዮጵያ የባንክ እና የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ሁለት ቀንደኛ ችግሮች አሉበት።

አንደኛው ‘ስትራክቸራል ኢንባላንስ’ ማለትም ትላልቅ የመንግሥት ባንኮች የሚወዳደሩት ‘ትናንሽ’ ከሚባሉት ጋር መሆኑ ነው ሲሉ ይተነትናሉ።

ይህንን ለመፍታት እኒህ ትላልቅ ባንኮች ተከፋፍለው አነስተኛ ባንኮች እንዲሆኑ አሊያም የግል እንዲሆኑ ማድረግ [ፕራይቬታይዝ] ነው እንጂ የውጭ ባንኮችን ማምጣት መፍትሔ አይሆንም ይላሉ።

እንደምጣኔ ሃብት ባለሙያው ገለፃ ሁለተኛው የፋይናንስ ዘርፍ ችግር ቁጥጥር (ሬጉሌሽን) ነው። የባንኮችን የብድር የወለድ መጠንን እንደምሳሌ ይጠቅሳሉ።

“ከዓለም አገራት በ15 አሊያም በ18 በመቶ የወለድ መጠን ተበድሮ፣ ነግዶ፣ አትርፎ ብድሩን በመመለስ አገር ይለውጣል ማለት ዘበት ነው።»

ይህ ችግር የመነጨው የመንግሥት አስተዳደር ውስጥ ያሉ አካላትና የባንክ ባለቤቶች በመስማማት በመወሰናቸው ነው ይላሉ።

ነገር ግን ዘመዴነህም ሆኑ ጥላሁን የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው የወለድ መጠኑ እንዲቀንስ ያስችላል ሲሉ ይከራከራሉ።

“የእነዚህ የውጭ ባንኮች መግባት ሌሎቹን የግል ባንኮች ያነቃል። ለምሳሌ የወለድ ቅናሽ ሊኖር ይችላል” ይላሉ ጥላሁን።

እንደ ሌሎች አገራት የብድር ወለድ መጠን ወደ ሰባት እና ስድስት በመቶ መውረድ አለበት ብለው የሚከራከሩት አየለ ገላን (ዶ/ር) ባንኮች ትርፋቸው ሊቀንስ ቢችልም፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከዚህ በፊት መበደር ያልቻሉ ሰዎች የብድር አቅርቦት ያገኛሉ ሲሉ ያስረዳሉ።

ባለሙያው መንግሥት የውጭ ባንኮች እንዲገቡ መፍቀዱ ከላይ ከተነሱት ሁለት አበይት ችግሮች ጋር “በፍፁም አይገናኝም” ይላሉ።

ተመራማሪው የውጭ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ይዘው ይመጣሉ የሚለውን ሐሳብ አጥብቀው ይተቻሉ። ይህንን ሲያብራሩም “ለዘላቂ ችግር ጊዜያዊ መፍትሔት ማበጀት ፋይዳ የለውም” የሚለውን የፈረንጅ አባባል በማውሳት ነው።

“ወደ ሃገር ቤት የሚመጣው ኩባንያ ሲገባ መጀመሪያ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ይዞ ሊመጣ ይችላል። ነገር ግን ሥራ ከጀመረ በኋላ በየወሩ ዶላር ወደ ውጭ ይልካል። ዶላር ወደ ሃገር ቤት የሚመጣ ምርት ወደ ውጭ ስንልክ ነው እንጂ፣ እነዚህ ባንኮች ዶላሩን ወደ አገር ቤት አምጥተው የሚለግሱበት ምንም ምክንያት የላቸውም።”

አየለ፤ የውጭ ባንኮች አዳዲስ ቴክኖሎጂ ያስተዋውቃሉ የሚለውን መከራከሪያም “ፎልስ ኢኮኖሚክስ” ነው በማለት ውድቅ ያደርጉታል።

“እነዚህ ባንኮች የሚያመጡት ቴክኖሎጂ የሮኬት ሳይንስ አይደለም። ቴክኖሎጂ በሰው አአምሮ ውስጥ እንጂ በባንኮች እጅ አይደለም ያለው። የመኪና መገጣጠሚያ አሊያም የማዳበሪያ ፋብሪካ እናስገባለን ቢሉ ያስማማል” በማለት።

ቁጥጥር

የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ሲገቡ ምን ዓይነት ቁጥጥር ሊደርግባቸው ይገባል? የሚለው ጥያቄ ሌላኛው መከራከሪያ ነው።

“ባፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ አንድም ባንክ አልከሰመም ሲሉ የሚናገሩት ዘመዴነህ ብሔራዊ ባንክ እስካሁን በቁጥጥር ረገድ መልካም ሥራ ሠርቷል ብለው ያምናሉ።

“ነገር ግን አሁን የውጭ ባንኮች እየመጡ ስለሆነ ብሔራዊ ባንክ የቁጥጥር አቅሙን ከፍ ማድረግ አለበት።

ምክንያቱም ሃገር በቀል ባንኮችን መቆጣጠር እና በጣም ውስብስብ የሆኑ ዓለም አቀፍ ባንኮችን መቆጣጠር በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው።”

ጥላሁንም ‘ኮርፖሬት’ ደንበኛ ላይ አተኩረው ለሚሠሩ ባንኮች የሚሆን አዲስ ቁጥጥር በቅርቡ ሊወጣ እንደሚችል ይገምታሉ።

ብሔራዊ ባንክ፤ የውጭ ሃገራት ወደ ሃገር ቤት ሲገቡ “የጤናማ ብድር መጠን ሕጉን ያስተካክላል” ብለው ያምናሉ።

ነገር ግን ይላሉ፤ “አሁን እንዲገቡ እንደተፈቀደላቸው ሁሉ ሲወጡ እንዴት ነው የሚለው ሊታሰብበት ይገባል።”

“ብሔራዊ ባንክ የሚያወጣቸውን መመሪያዎች መከታተል ይኖርብናል። በየዓመቱ ምን ያክል ገንዘብ ማስወጣት ይችላሉ የሚለው ነገር መመጠን ያለበት ይመስለኛል። ኢትዮጵያዊያን ድርሻ የሚገዙበትም አግባብ ሊኖር ይገባል።”