ኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍን ለውጭ ባለሐብቶች ክፍት ለማድረግ ወሰነች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ

የፎቶው ባለመብት, NBE/fb

የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ

የኢትዮጵያ መንግሥት ካቢኔ ለአስርታት ለውጭ ባለሐብቶች ዝግ ሆኖ የቆየውን የባንክ ሥራ ዘርፍ ክፍት ለማድረግ የቀረበለትን ረቂቅ ፖሊሲ አጸደቀ።

በአገሪቱ ብሔራዊ ባንክ አማካይነት ተዘጋጅቶ የቀረበው ረቂቅ ለዘመናት ለኢትዮጵያውያን ብቻ ተትቶ የነበረውን የፋይናንስ ዘርፍ ለውጭ ባንኮችም ክፍት እንዲሆን የሚፈቅድ ነው።

ይህም በዘርፉ ታዋቂ የሆኑ ዓለም አቀፍ ባንኮች በአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ላይ እንዳይሰማሩ አድርጎ የቆየውን የአገሪቱን የፋይናንስ ፖሊሲ የቀየረው ውሳኔ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ይፋ ሆኗል።

በዚህም ዓለም አቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያ ለአገር ውስጥ ባለሐብቶች ብቻ ክፍት አድርጋው በቆየችው ዘርፍ ለመሳተፍ እድል ይፈጥርላቸዋል።

የፋይናንስ ዘርፉ ዝግ ሆኖ በቆየባቸው ዓመታት ውስጥ የአገሪቱን ምጣኔ ሐብት በተለያዩ መስኮች ሲደግፉ የቆዩት ዓለም አቀፍ ተቋማት እና አገራት ዘርፉን እንድትከፍት ሲወተውቱ ቆይተዋል።

ዛሬ ቅዳሜ ነሐሴ 28/2014 ዓ.ም. የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 13ኛ መደበኛ ስብሰባው የባንክ ዘርፍን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት ለማድረግ የቀረበውን ረቂቅ ፖሊሲ አጽድቆ በሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔውን ይፋ ባደረገበት መግለጫው እንዳለው የባንክ ዘርፍን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት ማድረግ “አገልግሎቶች በእውቀት እና በቴክኖሎጂ ለመደገፍ፣ የአገሪቱን ምጣኔ ሐብት ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር የበለጠ እንዲተሳሰር ለማድረግ ያስችላል።” ብሏል።

በተጨማሪም ይህ እርምጃ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን በማቀላጠፍ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን በማጎልበት ለምጣኔ ሐብት ዕድገት አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል።

ለረጅም ዘመናት በመንግሥት እና በአገር ውስጥ ባለሐብቶች ተሳትፎ ብቻ ተይዘው የቆዩ ዘርፎችን የመክፈት ፍላጎት እንዳለው ሲገልጽ የቆየው መንግሥት አሁን የባንኩን ዘርፍ ክፍት አድርጎታል።

ይህ ዘርፍ ለውጭ ባለሐብቶች ክፍት ሊሆን እንደሚችል እና ዝግጅትም እየተደረገ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተለያዩ አጋጣሚዎች ፍንጭ ሲሰጡ ቆይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በተለይ በመንግሥት ተይዘው የሚገኙ ዘርፎችን ከፍት ለማድረግ ፍላጎት እንዳለ የተነገረ ሲሆን ተግባራዊነቱ ግን አዝጋሚ ሆኖ ነበር።

ከ120 ዓመት በላይ በመንግሥታዊው ኢትዮ ቴሌኮም ተይዞ የነበረው የቴሌኮም ዘርፍ ለውድድር ክፍት ሆኖ፣ ከአንድ ዓመት በፊት በተካሄደ ጨረታ ሳፋሪኮም ተመራጭ ሆኖ በዚህ ወር በተወሰኑ የአገሪቱ ክፍሎች የቴሌኮም አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።