ባሕር ዳር የተወለዱት ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሪፐብሊካን እጩ በኮሎራዶ ግዛት የከተማ ምክር ቤት ምርጫ አሸነፉ

ትውልደ ኢትዮጵያዊ-አሜሪካዊው አቶ አምሳሉ ፀጋዬ ካሳው በኮሎራዶ አገረ ግዛት፣ የአውሮራ ከተማ ምክር ቤት ምርጫን ከትላንት በስትያ አሸንፈዋል።
ይህም በኮሎራዶ አገረ ግዛት የመጀመርያው ትውልደ ኢትዮጵያዊያዊ ተመራጭ እንዲሁም የመጀመሪያው አፍሪካዊ ስደተኛ የምክር ቤት አባል ያደርጋቸዋል።
የተካሄደው ምርጫ የማሟያ ሲሆን አቶ አምሳሉ ለአንድ ዓመት የሚያገለግሉ ይሆናል።
የተመረጡበትን አራት ዓመት ሳያጠናቅቁ ከኃላፊነት የለቀቁት የምክር ቤት አባል ፕሮ ተም ደስተን ዘፋነክን ተክተው ይሠራሉ።
የአውሮራ ከተማ ምክር ቤት ከ37 ተወዳዳሪዎች መካከል ሦስት እጩዎችን ለመጨረሻ ዙር ውድድር አቅርቧል።
ሦስቱ እጩዎች ዳንኤል ሌሞን፣ ጆናታን መክሚለን እና አምሳሉ ካሳው በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ቃለ ምልልስ ተደርጎላቸዋል።
የአውሮራ ከተማ ከንቲባ ማይክ ኮፍማን ካቀረቧቸው እጩዎች መካከል እንደሆኑ አቶ አምሳሉ ተናግረዋል።
ቃለ ምልልሱን ጨምሮ ከማኅበረሰቡ አስተያየት የመቀበልና ሌሎችም ሂደቶች ሁለት ወር ገደማ ወስደዋል። ድምጽ ሰጥተው አሸናፊውን የለዩትም የከተማዋ ምክር ቤት አባላት ናቸው።
'ዘ ዴንቨር ጋዜት' ባወጣው ዘገባ መሠረት፣ ከ10 የምክር ቤቱ አባላት 6ቱ በሰጡት ድጋፍ አቶ አምሳሉ አሸናፊ ሆነዋል።
የተመረጡበትን አራት ዓመት ሳያጠናቅቁ ከኃላፊነት የለቀቁትን የምክር ቤት አባል ተክተው ለአንድ ዓመት ከሠሩ በኋላ በቀጣይ ምርጫ እንደሚወዳደሩ አቶ አምሳሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Amsalu Kassaw
አቶ አምሳሉ የተወለዱት ባሕር ዳር ነው። ለ17 ዓመታት በኮሎራዶ ኖረዋል።
በኮሎራዶ አገረ ግዛት ከ40 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን እንደሚኖሩ ይገመታል።
አቶ አምሳሉ የሦስት ልጆች አባት ናቸው።
በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት "ጉዞዬ በጽናት፣ በማኅበረሰብና በተስፋ የተቃኘ ነው" ብለዋል።
ውልደታቸው ባሕር ዳር ይሁን እንጂ ስፓኒሽን ጨምሮ 4 ቋንቋዎችን ይናገራሉ። ይህም በርካታ ስፓኒሽ ተናጋሪዎች በሚገኙበት ከተማ ቅስቀሳ ለማድረግና ምርጫ ለማሸነፍም ረድቷቸዋል።
"እስካሁን ልብ ካላላችሁ 'አክሰንት' አለኝ። በአውሮራ ያለነው አብዛኞቻችን እንደዛ ነን። በዚህች ታላቅ ከተማ አቀባበል የተደረገልኝ ስደተኛ ነኝ። ስፓኒሽን ጨምሮ 4 ቋንቋዎች እናገራለሁ" ብለዋል።
'አውሮራ ለእኔ ከከተማ በላይ ናት'
ሦስቱም ልጆቻቸው አውሮራ ከተማ ነው የተወለዱት። አውሮራ የኮሎራዶ ሦስተኛ ትልቅ ከተማ ናት።
ከተለያዩ አገሮች የሄዱ ነዋሪዎች ስለሚኖሩባት 'ቅይጥ' ከሚባሉ ከተሞች አንዷ ናት።
"በ2007 በፖለቲካ ጥገኝነት አውሮራ ስመጣ ከተማዋ እጇን ዘርግታ ነው የተቀበለችኝ። ስለዚህም አውሮራ ለእኔ ከከተማ በላይ ናት። የዕድልና ብዝሀነት ተምሳሌት ናት" ሲሉ አቶ አምሳሉ ይገልጻሉ።
አቶ አምሳሉ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፣ በኮሎራዶ ያለውን የኢትዮጵያን ማኅበረሰብ በማጠናከር ረገድ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠትን ጨምሮ በሌሎችም መንገዶች ንቁ ተሳትፎ ያደርጋሉ።
የማኅበረሰብ ተወካይ በመሆን "ንቃተ ሕሊና የመፍጠር፣ የልምድ፣ የመረጃና የባህል ልውውጥ የማድረግ፣ አዳዲስ ኢትዮጵያውያን ሲመጡ የማደራጀትና ሲቸገሩ የመደገፍ ሥራ" እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Amsalu Kassaw
"ላለፉት 17 ዓመታት የኖርኩት አውሮራ ነው። ራሴን አሜሪካዊና የአውሮራ ነዋሪ ብዬ ስጠራ በበኩራት ነው" ሲሉ በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት ተናግረዋል።
"እናንተም እኔም የምናውቀውን የአሜሪካ ሕልም (American dream) በተመለከተ ልዩ ዕይታ አለኝ። በየዓመቱ እኔና ልጆቼ ለጎዳና ተዳዳሪዎች የገና በዓል እራት እናበላለን። በቤተ ክርስቲያን በኩል የተሰባሰበ ልብስ እናከፋፍላለን" ሲሉም አቶ አምሳሉ ተናግረዋል።
በዚህ ማኅበራዊ አገልግሎት አማካይነት ለልጆቻቸው ደግነትን፣ መልሶ መስጠትንና ሌሎችን መንከባከብን እንደሚያስተምሩ ይገልጻሉ።
ከአመራሮችና የማኅበረሰብ መሪዎች ጋር በመሆን አነስተኛና ጥቃቅን ንግድን እንዲሁም ማኅበራዊ ተሳትፎን እንደሚያበረታቱ ተናግረዋል።
"ዓላማዬ የሚያስተሳስሩንን ገመዶች ማጠንከርና ለሁሉም ሰዎች ዕድል መፍጠር ነው" ሲሉም አቋማቸውን ይገልጻሉ።
ከዚህ ቀደም የኮንግረስ አባሉ ማይክ ኮፍማን አማካሪ ኮሚቴ ውስጥ ሠርተዋል። ማይክ ኮፍማን እአአ ከ2019 ጀምሮ የአውሮራ ከተማ ከንቲባ ናቸው።
አቶ አምሳሉ፣ አውሮራ እና አዳማ እህትማማች ከተሞች እንዲሆኑ መሥራታቸውንም ተናግረዋል።
በአውሮራ ከተማ ማኅበረሰባዊ አገልግሎት ለሚሰጡ በጎ ፈቃደኞች የሚሰጠው 'Spirit Award' የ2024 ተሸላሚ ናቸው።
በ2023 ደግሞ በአሜሪካ ምክር ቤት ውስጥ ስለ ኢትዮጵያ ማብራሪያ በማቅረብ ዕውቅና አግኝተዋል።
አቶ አምሳሉ የኢትዮጵያን አሜሪካን ሲቪክ ካውንስል የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተርም ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Amsalu Kassaw
ከዲያቆንነት እስከ ምክር ቤት አባልነት
"በልጅነቴ ቤተ ክህነት ነው ያደግኩት" የሚሉት አቶ አምሳሉ ባሕር ዳር ሳሉ ዲያቆን እንደነበሩና በኮሎራዶም በቅድስተ ማርያም ቤተ ክርስቲያን እንደሚያገለግሉ ተናግረዋል።
"ለኢትዮጵያውያን ምልክት የሆነች፣ የተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች የሚካሄዱባት፣ አፍሪካውያን እንደ መገናኛ የምንጠቀምባትም ናት" ሲሉ ገልጸዋል።
ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ባሻገር 11 አባላት ያሉት የከተማ ምክር ቤት አባል ሆነዋል።
ከአባላቱ መካከል አንደኛው ከንቲባው ሲሆኑ ዓሥሩ የሚመረጡት በከተማዋ ነዋሪዎች ነው።
በአውሮራ ውስጥ ለሚደረጉ የሕዝብ አገልግሎቶች፣ የቤት አቅርቦት፣ የአነስተኛና ጥቃቅን ንግድ፣ የመጓጓዣ፣ የደኅንነት፣ የበጀትና ሌሎችም አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ ፖሊሲዎች በምክር ቤቱ ያሳልፋሉ።
የከተማዋ ምክር ቤት ሁለተኛ እርከን ሲሆን ከምክር ቤቱ ከፍ ብሎ የአገረ ግዛቱ ገዢ ሥልጣን አለው።
"አብዛኞቹ ፓለቲከኞች ከታች ከከተማ ተነስተው ጉዟቸውን ወደ ኮንግረስ ያደርጋሉ" ሲሉ አቶ አምሳሉ ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Amsalu Kassaw
'ዘ ዴንቨር ጋዜት' ባወጣው ዘገባ፣ አቶ አምሳሉን በመደገፍ የተናገሩት የምክር ቤት አባል ስቴፋኒ ሀንኮክ "በዚህ አገር ብቻ ሳይሆን በትውልድ አገሩም ጥሩ አመራር አሳይቷል። እዚህ መጥቶም ሁሉንም ነገር በትክክል ነው ያከናወነው። እሱን መምረጥ አውሮራ ዘረኛ ከተማ እንዳልሆነች ግልጽ መልዕክት ያስተላልፋል" ብለዋል።
"እሱን በምክር ቤቱ አባልነት ማካተት የማኅበረሰባችንን ታማኝነትና ጥንካሬ ያጎለብታል" ሲሉም አክለዋል።
ሌላው የምክር ቤት አባል ስቲቭ አንድበርግ "ኢትዮጵያውያን ይቺን ከተማ የሚወዱ ታላቅ ሕዝቦች ናቸው" ማለታቸውንም ዘገባው አትቷል።
ሌላ የምክር ቤት አባል ዳንኤሌ ጁሪንስክያርድ፣ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ "እጁን ዘርግቶ ነው የተቀበለኝ" ብለው ከአቶ አምሳሉ ጋር በፖለቲካ ባይስማሙም መመረጣቸውን እንደሚደግፉ ተናግረዋል።
"ሙሉ በሙሉ በይፋ እደግፈዋለሁ" ብለው በምክር ቤቱ መናገራቸው በዘገባው ተመልክቷል።
አቶ አምሳሉ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያውያን የማኅረሰብ መሪዎች ለምክር ቤቱ አባላት ደውለው ቅስቀሳ በማድረግ ድጋፍ ሰጥተዋቸዋል።
ከላቲን ማኅበረሰብ ቀጥሎ ኢትዮጵያውያን-አሜሪካውያን በኮሎራዶ ሁለተኛው ትልቁ የስደተኞች ማኅበረሰብ እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ አምሳሉ፣ ከኢትዮጵያውያን-አሜሪካውያን በተጨማሪ የኤርትራ፣ የሱዳን፣ የሴኔጋል፣ የሶማሊያ፣ የሩዋንዳ፣ የግብፅና ሌሎችም የአፍሪካ አገራት ስብስቦች "አፍሪካውያን በዚህ ምክር ቦታ መያዝ አለብን። አውሮራ የተለያዩ ሕዝቦች የሚኖሩባት ከተማ ነች ካልን ተወካይ መኖር አለበት" በሚል በምርጫ ቅስቀሳ እንዳገዟቸው ጠቅሰዋል።

የፎቶው ባለመብት, Amsalu Kassaw
አቶ አምሳሉ በአሜሪካ ፖለቲካ ሕልማቸው ምን እንደሆነ ከቢቢሲ ተጠይቀው፣የወደፊቱን ለወደፊት ትተው፣ "አሁን ግን እዚ ለምኖርበት ማኅበረሰብ በቅንነትና ታማኝነት ማገልገል ነው ሕልሜ። በስደተኞችና በሌላው ማኅበረሰብ መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት ጠንክሬ በመሥራ ስኬታማ መሆን ነው የምፈልገው" ብለዋል።
"የስደተኞችን ማኅበራዊ ደኅንነት፣ ቤት አልባነትን፣ ወንጀልንና ሌሎችም ችግሮች መዋጋት ነው ትልቁ ሕልሜ" ሲሉም አክለዋል።












