ትራምፕ እና አፍሪካ፡ የሕዳሴ ግድብ፣ የሱዳን ጦርነት እና የሶማሊያ ጉዳይ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    • ፀሐፊ, አሌክስ ደ ዋል*
    • የሥራ ድርሻ, የአፍሪካ ተንታኝ

ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ ሲመለሱ ምን ዓይነት ውሳኔዎች እንደሚያሳልፉ መገመት ከባድ ነው።

ለሰከነ እና መርሆችን ለሚከተል የዲፕሎማሲ አካሄድ ያላቸው ጥላቻ የሚለወጥ ግን አይመስልም። ይህ አካሄድ ሰላም የሚያመጣ ቢሆንም እንኳ ትራምፕ ብዙም አይከተሉትም።

ትራምፕ የሚመርጡት ሰጥቶ የመቀበል ፖለቲካን እና ብዙኃኑን የሚያማልል (ፖፑሊስት) አካሄድ ነው።

ይህ አካሄድ በአፍሪካ ተስፋም ስጋትም ያመጣል ተብሎ ይታመናል።

ከስምንት ዓመታት በፊት፣ የተባበሩት መንግሥታት በክፍያ በአፍሪካ የሚያሠማራቸውን ሰላም አስከባሪዎች ሁኔታ ለመለወጥ የባራክ ኦባማ አስተዳደር ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በቅርበት እየሠራ ነበር።

‘አፍሪካዊ የሰላም እና ደኅንነት ጥበቃ’ ለመዘርጋት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ከተባበሩት መንግሥታት እንዲሁም ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ሠርቷል።

ይህም የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር እና የአፍሪካ ኅብረት ገዢ መርኅን መሠረት በማድረግ፣ የዲፕሎማሲ መንገድን መከተል፣ በድርድር ግጭትን ለመግታት መሞከር እና የሰላም አስከባሪ ኃይልን ማሰማራትን ያካትታል።

ከዚህ ቀደም በነበረው የትራምፕ አስተዳደር ጠንካራ የሰላም ማስከበር እንቅስቃሴ ማድረግ አልተቻለም።

ከዚያ ወዲህ ባሉት ጊዜያት አዲስ የተባበሩት መንግሥታት እና የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች አልታዩም።

በዳርፉር፣ በሱዳን እና በማሊ ያሉት ሰላም አስከባሪ ተልዕኮዎችም ተቋርጠዋል።

የጆ ባይደን አስተዳደር ሁኔታው እንዲለወጥ አላደረገም።

ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ፍትሕ እና ነጻ ገበያ የሚሉት ሐሳቦች ወይም በእንግሊዝኛው ‘liberal peace’ አብረው የሚራመዱ እና አሜሪካ ለዓመታት የዓለም አቀፍ ስትራቴጂዋ ማጠንጠኛ ያደረገቻቸው ናቸው።

የአፍሪካ ኅብረት ለኅብረ ብሔራዊነት ዕውቅና ቢሰጥም ስለ ሰብአዊ መብት እንዲሁም ለዴሞክራሲ መካሪ የሚሻ አይመስልም።

እንደ ሊቢያ ባሉ አገራት የምዕራባውያን ወታደሮች መሰማራታቸውን በተመለከተ የተከፋፈለ አቋም አለው።

አንዳንድ የአፍሪካ አገራት የትራምፕ ግልጽነት እና ውጤት ላይ የማተኮር አዝማሚያ ያስደስታቸዋል።

ትራምፕ በመካከለኛው ምሥራቅ እንዲሁም በአፍሪካ ያላቸው አካሄድ ኅብረ ብሔራዊነትን ገሸሽ አድርጎ፣ የአሜሪካ አጋር ከሆኑ አገራት ማለትም ከግብፅ፣ ከሞሮኮ፣ ከሳዑዲ አረቢያ፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና በዋናነት ከእስራኤል ጋር የንግድ ልውውጥ ላይ ያተኮረ ነው።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት መሐመድ ቢን ዛይድ ‘አብርሃም አኮርድስ’ የተባለውን ስምምነት በማርቀቅ ስማቸው ይነሳል።

የአረብ አገራት ስምምነቱን ሲፈርሙ ትራምፕ በድል አድራጊነት ስሜት ደስታቸውን ገልጸዋል።

ሌላው የትራምፕ አጀንዳ ቻይና በአፍሪካ ላይ እያሳደረች ያለችው ተጽዕኖ ነው። ይሄ ጉዳይ ትራምፕን ይጎረብጣቸዋል።

ትራምፕ ግብፅ ‘ግድቡን ልታፈርሰው ትችላለች’ ሲሉም ተደምጠዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ትራምፕ ግብፅ ‘ግድቡን ልታፈርሰው ትችላለች’ ሲሉ ተደምጠዋል።

ትራምፕ ‘የምወደው አምባገነን’ ሲሉ የገለጿቸው የግብፅ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል-ሲሲ ባቀረቡት ጥያቄ የቀድሞው የግምጃ ቤት ፀሐፊ ስቲቨን ምኑቺን ከዓባይ ወንዝ ጋር በተያያዘ ግብፅ እና ኢትዮጵያን እንዲያሸማግሉ ሰይመው ነበር።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምን ያህል ውሃ ይይዛል የሚይለው ዋነኛ ጉዳይ ነበር።

በኢትዮጵያ እና በግብፅ መካከል ነገሮች እየተካረሩ ሲሄዱ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትልከውን እርዳታ በማቆም ጫና ለማሳደር ወስናለች።

ትራምፕ ግብፅ ‘ግድቡን ልታፈርሰው ትችላለች’ ሲሉም ተደምጠው የነበረ ሲሆን፣ ይህም ኢትዮጵያን አስቆጥቶ ነበር።

ሞሮኮ በምሥራቃዊ ሳህል ያላትን ጥያቄ አሜሪካ ዕውቅና ሰጥታለች። በምላሹ ሞሮኮ አብርሃም አኮርድስን በመፈረም ለእስራኤል ዕውቅና ሰጥታለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

‘ሊበራል ፒስ’ በሚለው መርኅ መሠረት፣ የእርስ በእርስ ጦርነትን ለማስቆም ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት ማርቀቅ፣ ተቀናቃኝ ተዋጊ ኃይሎችን ትጥቅ ማስፈታት፣ የሽግግር ፍትሕ ማስፈን እና እርቅ አስፈላጊ ናቸው።

ሰላም ለማስፈን እንዲሁም በግጭት የተለያዩ ሕዝቦችን ለማቀራረብ እርዳታም ይሰጣል።

የቀድሞው የትራምፕ አስተዳደር በቀጥታ ስምምነት መፈረምን መርጧል። በዚህም አምባገነኖች ከመጋረጃ ጀርባ የግል ስምምነት ያደርጋሉ።

ምሑራን ይህንን አካሄድ ነጻ ያልሆነ ሰላም ወይም ‘በእንግሊዝኛው ‘illiberal peace’ ሲሉ ይጠሩታል።

የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ ሱዳንን የጎበኙት የአገሪቱ አብዮት ወታደራዊውን መሪ ኦማር አል-በሽር ከሥልጣን ካስወገደ በኋላ ነበር።

ሱዳን አብርሃም አኮርድስን ከፈረመች ማዕቀቦች እንደሚነሱ ገልጸው ነበር።

እአአ በጥቅምት 2020 ዋይት ሐውስ ባወጣው መግለጫ ትራምፕ በሱዳን እና በእስራኤል መካከል ‘ታሪካዊ የሰላም ስምምነት’ ማስፈናቸውን አስታውቋል።

በስምምነቱ ባሕሬን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችም ተካተዋል።

ትራምፕ ይህንን ውሳኔ ያሳወቁት ከፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጥቂት ቀድመው ነበር።

ስምምነቱ ሱዳን ከገባችበት የምጣኔ ሃብት ቀውስ አላዳናትም። በአሜሪካ ምርጫም ጆ ባይደን አሸነፉ።

ትራምፕ በሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸው የሚከተሉት መንገድ ተመሳሳይ እንደሚሆን መገመት ይቻላል።

በቀጣይ ምን ዓይነት ስምምነቶች እንደሚደረጉ መገመት ቀላል ባይሆንም ቁልፍ የአስተዳደር ቦታ በሚሰጣቸው ሰዎች የሚወሰን ይሆናል።

‘ሊበራል ፒስ’ ወይም ነጻ ሰላም የሚለው ሐሳብ ግን ያከተመለት ይመስላል።

በአፍሪካ ትልቁ ጦርነት እየተካሄደ ያለው በሱዳን ነው። በአሥርታት ያልታየ ረሃብም ተከስቷል። ትራምፕ ይህ እንደሚያስጨንቃቸው የሚጠቁም ነገር አልታየም።

ዋነኛው የሰላም እንቅፋት በአንድ ወገን የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መኖር፣ ግብፅ እና ሳዑዲ አረቢያ ከመሣሪያ ሽያጭ አትራፊ መሆናቸው ነው።

ሁኔታው ባለበት ከቀጠለ ሰላም ለማስፈን አይቻልም።

ለአረብ ኃያላን ሱዳን ከእስራኤል እና ፍልስጤም እንዲሁም ኢራን ቀጥላ ከአሜረካ ጋር ያላቸውን ግንኙነት የምትወስን ቀጠናዊ የስትራቴጂ ስሌት አካል ናት።

የሱዳን ጦርነት

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በሱዳን ዋነኛው የሰላም እንቅፋት በአንድ ወገን የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መኖርና ግብፅ እና ሳዑዲ አረቢያ ከመሣሪያ ሽያጭ አትራፊ መሆናቸው ነው።

የመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካዊ አሰላለፍ ከተለወጠ ሱዳንን በተመለከተ ስምምነት ላይ መድረስ ይቻል ይሆናል።

ትራምፕ ያልተጠበቁ እርቅ አውራጅ ሊሆኑም ይችላሉ።

ሆኖም ዴሞክራሲን ማምጣት ይቅርና ግጭቱን መግታትም ቀላል ባይሆንም ለሰላም ስምምነት በሮች ሊከፍት ይችላል።

ግብፅ፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ለገቡበት ቁርሾም የሚሠራ ስሌት ሊሆን ይችላል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኤምሬትስ ድጋፍ ይደረግላቸዋል።

ግብፅ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አሰላለፋቸውን ከለወጡ የአፍሪካ ቀንድ ውጥረት ይረግብ ይሆናል።

ባይደን በአፍሪካ ቀን የተከተሉት ፖሊሲ ኅብረ ብሔራዊነትን ያማከለ ወይም ከገልፍ አገራት ጋር ያለውን ግንኙነት የቃኘም አልነበረም።

አስተዳደራቸው ግጭቶችን በመግታት የእርዳታ መስመሮች መክፈት ላይ ያተኮረ የስኬት ታሪክ ነው ያለው።

በሱዳን እና በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ትራምፕ ለማስቆም ቢሞክሩም የሚያስከትለው አደጋም ቀላል አይሆንም።

በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአፍሪካ መሪዎች ያለውን ግጭት ዋይት ሐውስ ማስቆም አይችል ይሆናል። በቀጣይ ወራት ባለው የአመራር ክፍተት ምክንያት አሜሪካ ምላሽ ስለማትሰጥ የትኛውም አገር ጦርነት የሚጀምርበትም ዕድል አለ።

ትራምፕ ቀድሞ ፕሬዝዳንት ሳሉ የአሜሪካ ወታደሮች በአፍሪካ ያላቸው እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት አላደረጉም።

የአሜሪካ ወታደሮች ከሶማሊያ እንዲወጡ አዘዋል።

ወታደሮቹ ከጂሃዲስት ታጣቂው የአል-ሻባብ ቡድን ጋር ውጊያ ውስጥ ነበሩ።

ውሳኔውን የትራምፕ አስተዳደር ቀልብሶታል።

ትራምፕ፣ ፔንታገን በምዕራብ አፍሪካ ሳህል በጂሃዲስቶች ላይ የሚያደርገውን ኦፕሬሽን ላያስተውሉት ይችላሉ። ይህም አሜሪካውያን ሞተው መነጋገሪያ እስከሚሆን ድረስ ነው።

የአሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅ አጋሮች አገሪቱ በጂቡቲ ወታደራዊ መቀመጫዋን ይዛ እንደምትቆይ ይጠብቃሉ።

የየመን ሁቲ አማጽያን እና የአል-ሻባብ ታጣቂዎች ግጭት በምሥራቅ አፍሪካ ጥቃቶች እንዲባባሱ እና አሜሪካ ለወታደራዊ እንቅስቃሴ የምትፈልጋቸው መርከቦች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እንዲጨምሩ ያደርጋል ተብሎ ተሰግቷል።

አሜሪካ ለተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ወይም ለግል ወታደራዊ ተቋማት ኃላፊነቱን ልትሰጥ ትችላለች።

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ የባይደን ደጋፊ ሆነው መቆየታቸው እምብዛም አይጠቅማቸው ይሆናል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ የባይደን ደጋፊ ሆነው መቆየታቸው እምብዛም አይጠቅማቸው ይሆናል።

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ የባይደን ደጋፊ ሆነው መቆየታቸው እምብዛም አይጠቅማቸው ይሆናል።

ኬንያ በሄይቲ ሰላም አስከባሪዎች በማሰማራት ከኔቶ ውጪ ያለች ‘ዋነኛ አጋር አገር’ ሆና መቀጠሏ ግን የተሻለ ተቀባይነት ያስገኝላታል።

በምዕራብ አፍሪካ ያለው የጂሃዲስቶች እንቅስቃሴ በዓለም አሳሳቢ ከሆኑት መካከል ይጠቀሳል።

ከሩሲያው ቫግነር ቡድን ጋር ስምምነት የሚያደርጉ አገራት መብዛት ሌላው ጉዳይ ነው።

ትራምፕ ምዕራብ አፍሪካን ከሞስኮ ጋር ካላቸው ግንኙነት ጋር የሚያያዝና ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የሚደርሱበት ስምምት አካል አድገው ከተመለከቱ በቀጠናው ፖለቲካ ያልተጠበቀ እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ።

የትራምፕ አጋር ሞሮኮ በምዕራብ አፍሪካ የራሷ ፍላጎት ስላላት ነገሮች ሊካረሩ ይችላሉ።

ሩሲያ በአልጄሪያ፣ በሊቢያ እና በሳሃል እያሳደረች ያለችውን ጫና ሞሮኮ አትደግፍም።

ትራምፕ ከፑቲን ጋር ካልተስማሙ ይህ ሊባባስ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው።

ሰጥቶ የመቀበል ፖለቲካ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ከያዙ እና በወንጀል ስማቸው ከጠለሸ መሪዎች ጋር ስምምነት ማድረግን ያካትታል።

የአፍሪካ ኅብረት ሕገ መንግሥታዊ ለውጥን የሚነቅፍበት መርኅ ይጣሳል።

የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ የባይደን አስተዳደር ይቀርባቸዋል።

የትራምን ፖሊሲ ስለሚያውቁ ከጂሃዲስት ቡድኑ ቦኮ ሐራም ጋር በሚያደርጉት ውጊያ እንዴት አሜሪካን ማሳተፍ እንደሚችሉ ያስባሉ።

ትራምፕ በዓለ ሲመት ካደረጉ ከሳምንታት በኋላ የአፍሪካ መሪዎች በአዲስ አበባ ተገናኝተው አዲስ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበር ይመርጣሉ።

ተሰናባቹ ሊቀ መንበር የቻድ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙሳ ፋኪ ማህማት በባይደን እና በትራምፕም አስተዳደር ወቅት ሠርተዋል።

አዲስ ሊቀ መንበር ሲተኩ ለአፍሪካ ሰላም እና ደኅንነት የተሻለው ቀመር የትኛው ነው የሚለው ይወሰናል።

____

*አሌክስ ደ ዋል አሜሪካ ባለው ተፍትስ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በፍሌቸር ስኩል ኦፍ ሎው ኤንድ ዲፕሎማሲ የሚገኘው ወርልድ ፒስ ፋውንዴሽን ዋና ኃላፊ ናቸው።