ንግድ፣ እርዳታ፣ ፀጥታ፡ የትራምፕ ወደ ፕሬዝዳንትነት መመለስ ለአፍሪካ ምን ማለት ነው?

ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት መሆናቸው ዕውን ሲሆን፣ በርካታ የአፍሪካ አገራት መሪዎች እንኳን ደስ አለዎት የሚሉ መልዕክቶች እና ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ፍላጎታቸውን ገልጸዋል።
ትራምፕ ከአራት ዓመታት በፊት ሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ በአፍሪካ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ያለመ ዕቅድን ተግባራዊ አድርገዋል። ይህም እሳቸው ሥልጣን ከለቀቁ ከሦስት ዓመታት በኋላ በሥራ ላይ ይኛል።
ነገር ግን በርካታ አዲስ ነገሮች ባሉበት በአሁኑ ውቅት ትራምፕ ከአፍሪካ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በምን ዓይነት መልኩ ሊይዙት ይችላሉ?
ንግድ እና ኢንቨስትመንት
ተሰናባቹ የጆ ባይደን አስተዳደር “አፍሪካ መሰረታዊ እና ጠቃሚ አጋር እንደሆነች የሚያሳይ ስሜትን ለመፍጠር እጅጉን ሞክሯል” የሚሉት የግሎባል ልማት ማዕከል ባልደረባ እና የቀድሞው የላይቤሪያ ሚኒስትር ጂዩድ ሙር ናቸው።
ባይደን ይህንን ጽኑ ፍላጎታቸውን ዕውን ለማድረግ በርካታ ስምምነቶች እና አጋርነቶችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል፣ የሚሉት ሙር፣ ነገር ግን ይህ ለአፍሪካ የያዙት ዕቅድ ፍሬ አልባ ነበር ማለት አይቻልም።
ለምሳሌ አሜሪካ ወሳኝ ጥሬ ዕቃዎችን ለማጓጓዝ የሚውሉትን በአንጎላ፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በዛምቢያ ለተዘረጉ የባቡር መስመር ግንባታዎች መዋዕለ ነዋይ ማፍሰሷ የሚወደስ አስተዋጽኦዋ ነው።
ጆ ባይደን ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ አሜሪካ በአፍሪካ ከ22 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ማድረጓን ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት አስታውቃለች።
ነገር ግን ትራምፕ እንዲህ ዓይነቶቹን ኢንቨስትመንቶች እና የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ አሜሪካ የምታፈሰውን ገንዘብ ሊያቋርጡ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ።
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ከባይደን የበለጠ ለአገራቸው ምርቶች ከለላ የመስጠት እና ገለልተኛ አመለካከት ያለው ነው። ትራምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተመረጡባቸው መፈክሮች አንዱ አሜሪካንን ማስቀደም [አሜሪካ ፈርስት] እንደነበር አይዘነጋም።
በተለይ ከ20 ዓመታት በፊት ተግባራዊ የሆነው እና አሜሪካ ያስቀመጠቻቸውን መስፈርቶችን ያሟሉ የአፍሪካ አገራት የተወሰነውን ምርቶቻቸውን ከቀረጥ ነጻ ወደ አሜሪካ እንዲያስገቡ ያስቻለው የአፍሪካ ዕድገት እና ዕድል ደንብ (አጎዋ) ጉዳይ በትራምፕ እንዲቀጥል የመደረጉ ጉዳይ አጠያያቂ ነው።
ትራምፕ ከአራት ዓመት በፊት ሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ በአውሮፓውያኑ 2025 የአግልግሎት ዘመኑ የሚያበቃው የአጎዋ የንግድ ሥርዓት በሥራ ላይ እንዲቀጥል እንደማያራዝሙት ገልጸው ነበር።
አሁን ለተመረጡበት የሥልጣን ዘመን ቅስቀሳ ሲያካሂዱ የነበሩት ትራምፕ በሁሉም ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦች ላይ የ10 በመቶ የገቢ ቀረጥ እንደሚያስከፍሉ ተናግረዋል።
ይህም ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦችን በአሜሪካ የበለጠ ውድ ያደርጋቸዋል፣ ስለዚህም አፍሪካውያን ላኪዎች በአሜሪካ ሰፊ ገበያ የሚሸጧቸው ምርቶች መጠን ይቀንሳል ማለት ነው።
በአጎዋ ስምምነት መሠረት ወደ አሜሪካ ምርቶቿን በመላክ ቀዳሚዋ በሆነችው ደቡብ አፍሪካ ያሉ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች አጎዋ የሚቋረጥ ከሆነ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል ብለው ይሰጋሉ።
ይሁን እንጂ የአሜሪካ የባለሙያዎች ቡድን የሆነው ብሩኪንግስ ኢንስቲቲዩት አጎዋ የሚቆም ከሆነ በደቡብ አፍሪካ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ላይ የሚኖረው ተጽእኖ “0.06 በመቶ” ብቻ እንደሚሆን አመልክቷል።
ለዚህም ምክንያቱ ደቡብ አፍሪካ ወደ አሜሪካ የምትልካቸው እንደ ማዕድን እና ብረታ ብረት ያሉ አብዛኞቹ ምርቶች የአጎዋ ተጠቃሚ ስላልሆኑ ነው ብሏል።
ምንም እንኳን ትራምፕ የአጎዋ መቀጠልን ባይፈልጉት፣ አሜሪካ በአፍሪካ እያደገ ያለውን የቻይናን ኢኮኖሚ ተጽዕኖ ለመገዳደር የምትፈልግ ከሆነ ከአህጉሪቱ ጋር ያላትን አጋርነትን በተወሰነ ደረጃ ማስቀጠል እንዳለባት ይገነዘባሉ።
በአውሮፓውያኑ 2018 የቀደመው ትራምፕ አስተዳደር በአፍሪካ ኢንቨስት ለማድረግ የሚፈልጉ የአሜሪካ ኩባንያዎችን እና የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (ዲኤፍሲ) በአፍሪካ እና በዓለም ዙሪያ የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶችን የሚደግፍ ‘ፕሮስፐር አፍሪካ’ የተባለውን ፖሊሲ ይፋ አድርጓል።
እነዚህን ዕቅዶች ትራምፕ ሥልጣን ከለቀቁ በኋላም የባይደን አስተደደር ተረክቦ ያስቀጠላቸው ሲሆን፣ ዲኤፍሲ እንደሚለውም እስካሁን በአፍሪካ ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት አድርጓል።
ቻይና አሁንም በአፍሪካ ውስጥ ዋነኛ ኃይል መሆኗን እና ትራምፕ ደግሞ እነዚህን ፖሊሲዎች ራሳቸው ያመጧቸው ዕቅዶች ከመሆናቸው አንጻር እንዲቋረጡ ከመወሰናቸው በፊት ቆም ብለው ሊያስቡበት ይችላሉ።
እርዳታ
አፍሪካ አብዛኛውን እርዳታ የምታገኘው ከአሜሪካ ነው። ሊጠናቀቅ በተቃረበው የአውሮፓውያን ዓመትም 3.7 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ድጋፍ ከዩናይትድ ስቴትስ አግኝታለች።
ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ከአራት ዓመት በፊት ትራምፕ በሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ አስተዳደራቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን የውጭ እርዳታን እንዲቀንስ ተደጋጋሚ ምክረ ሃሳብ አቅርቦ ነበር። ነገር ግን በአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ የሁሉም ፓርቲ ድጋፍ ያለው የእርዳታ ጉዳይ ቅነሳው ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።
አሜሪካ ለአፍሪካ አገራት የምትሰጠው እርዳታ ቀንሶ ቢሆን ኖሮ “አሜሪካ የምትታወቅባቸው የጤና ፖሊሲዎች፣ የዲሞክራሲ ማስፋፋት እና የአፍሪካን የጸጥታ ድጋፍ ጉዳዮች እክል ይገጥማቸው ነበር” ሲል የዋሽንግተን የውጭ ግንኙነት ምክር ቤት የተባለው የባለሙያዎች ቡድን ገልጿል።
ምርጫውን ተከትሎ ግን ሪፐብሊካኖች በኮንግረስ ውስጥ ከፍተኛ ድምጽ ካገኙ የእርዳታ ቅነሳን በሚመለከት የሚገጥማቸው ተግዳሮች አነስተኛ ሊሆን ይችላል። ሪፐብሊካኖች አስቀድመው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱን (ሴኔት) እንዲሁም አብላጫውን የታችኛውን ምክር ቤት መቀመጫ ይዘዋል።
ለዓመታት በአፍሪካ ኤችአይቪን ለመዋጋት ከፍተኛ ገንዘብ ያፈሰሰውን የረዥም ጊዜ የአሜሪካ መርሃ ግብር ውጤት የሆነውን ፔፕፋርን ትራምፕ ሊዘጉት ይችላሉ የሚል ስጋት አለ።
ባለፈው ዓመት የሪፐብሊካን ሕግ አውጪዎች መርሃ ግብሩ የጽንስ ማቋረጥ አገልግሎትን እያስተዋወቀ ነው በሚል በፔፕፋር ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ አሰምተው ነበር።
ነገር ግን እስከሚቀጥለው ዓመት መጋቢት ድረስ የአጭር ጊዜ ማራዘሚያ ተፈቅዶለት ነበር። ቢሆንም ጽንስ ማቋረጥን በመቃወም የሚታወቁት ትራምፕ ፔፕፋርን ሊዘጉት ይችላሉ እየተባለ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ስደት
ትራምፕ በሕገወጥ ስደት ላይ ያላቸው አመለካከት ግልፅ ነው አሁን ላሸነፉበት ምርጫ ባደረጉት ቅስቀሳ ወቅት ወደ አሜሪካ ለመግባት ሕጋዊ ፍቃድ የሌላቸውን አንድ ሚሊዮን ሰዎች እንደሚያባርሩ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
ይህ ደግሞ አፍሪካን የሚመለከት ጉዳይ ነው። በ2022 ወደ 13,000 የሚጠጉ አፍሪካውያን ስደተኞች በአሜሪካ እና ሜክሲኮ ድንበር በኩል ገብተው መመዝገባቸውን የአሜሪካ የጉምሩክ እና የድንበር ጥበቃ መረጃ ያሳያል። በ2023 ደግሞ ይህ አሃዝ በአራት እጥፍ ጨምሮ ወደ 58,000 ደርሷል። ከእነዚህ ስደተኞች አንዳንዶቹ ጦርነትን፣ ስደትን እና ድህነትን ስለመሸሽ ይናገራሉ።
ነገር ግን ትራምፕ በስደተኞች ጉዳይ ላይ የሚያራምዱት ይህ ፀረ-ስደት ፖሊሲ ብዙም አዲስ አይደለም። በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው ናይጄሪያን፣ ኤርትራን፣ ሱዳንን እና ታንዛኒያን ጨምሮ ከበርካታ የአፍሪካ አገራት የሚመጡ ስደተኞችን ለመግታት ያስችላል ያሉትን እርምጃ ይፋ ማድረጋቸው አይዘነጋም።
የትራምፕን ለምርጫ መቅረብ እና መመረጥን ተከትሎ በአሜሪካ ያሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ስደተኞች በአሜሪካ የሚኖራቸው ቀጣይ ሕይወት አሳሳቢ እንደሚሆንባቸው ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ፀጥታ እና ደኅንነት
ትራምፕ ከፕሬዝዳንትነት ተሰናብተው በቆዩባቸው ያለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ሩሲያ በአፍሪካ ያላትን ተጽዕኖ አጠናክራለች።
ይህን ካደረገበት መንገዶች መካከል ዋነኛው እንደ ማሊ፣ ኒጀር እና ቡርኪናፋሶ ላሉ በጂሃዲስት ታጣቂዎች ለሚታመሱ አገራት ወታደሮች እና የጦር መሳሪያ በማቅረብ ነው።
ይህ የሩሲያ በአፍሪካ ሥር መስደድ አሜሪካንን በእጅጉ አሳስቧታል። ታሪካዊ ተቀናቃኝ በሆኑት ሁለቱ አገራት መካከል ያለው ፉክክር ሌላ ገጽታ ሊይዝ ይችላል።
ትራምፕ ይህንን የሩሲያን ተጽእኖ ለመግታት ለአፍሪካ አገራት ድጋፍ ሊሰጡ ይችላሉ?
“ምንም እንኳን የአሜሪካ የብሔራዊ ደኅንነት አቋም ሩሲያን እንደ ስጋት ቢቆጥራትም፤ ትራምፕ ግን በግላቸው ሩሲያን እንደ ስጋት የሚቆጥሩትን ያህል የሚጠበቅባቸውን አላደረጉም” ሲሉ ሙር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ትራምፕ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላቸው የሚል ግምት አለ።
ይሁን እንጂ ትራምፕ ናይጄሪያን ለ15 ዓመታት ያህል ሲያምሳት የቆየውን እስላማዊ ታጣቂ ቡድን ቦኮ ሃራምን እንድትዋጋ ድጋፍ አድርገዋል።
“[በቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ] ኦባማ የሥልጣን ዘመን፣ ምንም እንኳን ናይጄሪያ-አሜሪካውያን ሳያሰልሱ ቢደግፉትም የናይጄሪያን የጦር መሳሪያ ጥያቄ ውድቅ አድርገዋል። በሰሜን ናይጄሪያ የሚገኙ ማኅበረሰቦች በቦኮ ሃራም ጥቃት ሲሰነዘርባቸው፣ በመጨረሻ የቱካኖ ጀቶች እንዲሸጡ የፈቀዱት ትራምፕ ነበሩ። ይህም መከላከያችንን እንድናጠናክር አስችሎናል” ሲሉ የቀድሞው የሕግ ባለሙያ የሆኑት ኢሂኦዙዋ ጆንሰን አጎናይንማ ለናይጄሪያ የዜና አውታር ተናግረዋል።
ለ18 ወራት ሲንከባለል የቆየው እና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የገደለው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ጉዳይም አለ።
“ትራምፕ የሚያደርጉት ነገር ሰጥቶ በመቀበል ላይ የተመሠረተ ነው” ሲል ሙር ተናግሯል። “የትራምፕ አስተዳደር የባይደን አስተዳደር አደረገ ከምንለው ይልቅ በሱዳን ለሚሆነው ነገር የበለጠ እንደሚያስብ እጠራጠራለሁ” በማለት የሚለወጥ ነገር ይኖራል ብለው አያስቡም።
በመጨረሻ ግን ትራምፕ የፕሬዝዳንትነት ሥልጣናቸውን ከያዙ በኋላ ምን ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ የሚያደርግ ምንም መንገድ የለም።
ሙር እንዳሉት “ትራምፕ ሁሉንም ነገር የሚያከናውኑበት መንገድ በጣም ያልተለመደ ነው። ስለዚህ አንድ ሰው ለአዳዲስ ነገሮች በጣም ክፍት መሆን አለበት፣ ለጥሩ ነገር ሳይሆን ለሚከሰቱ አዳዲስ ነገሮች።”












