የትራምፕ ማሸነፍን ተከትሎ የአክሲዮን ገበያ እና የቢትኮይን ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ አሻቀበ

በአሜሪካ ምርጫ የትራምፕ ደጋፊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዶናልድ ትራምፕ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸውን ተከትሎ የአክስዮን ገበያ ክብረ ወሰን በሆነ ዋጋ የጨመረ ሲሆን፣ የዶላር ዋጋም ከስምንት ዓመታት በኋላ ከሌሎች አገራት የመገበያያ ገንዘቦች ጋር ሲነጻጸር የመግዛት አቅሙ ከፍ ብሏል።

ትራምፕ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ ለክሪፕቶከረንሲ መገበያያዎች ‘ቅድሚያ እሰጣለሁ’ ማለታቸውን ተከትሎ ከምርጫው ውጤት በኋላ ቢትኮይን የምንጊዜም ከፍተኛ የተባለውን ዋጋ አስመዝግቧል።

በአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም የአሜሪካ ምርጫ ውጤት የገበያን እና የመገበያያ ገንዘቦች የመግዛት አቅም ላይ በእጅጉ ለውጥ አምጥቷል።

በአሜሪካ ዋና ዋና የሚባሉት የስቶክ ገበያዎች ለውጥ የተመዘገበባቸው ሲሆን ባንኮችም መነቃቃት ታይቶባቸዋል።

የብሪታኒያን ፓውንድ ጨምሮ ከዋና ዋና የመገበያያ ገንዘቦች ጋር ሲነጻጸር የአሜሪካን ዶላር በ1.65 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

የዩሮ የመግዛት አቅምም ከዶላር ጋር ሲነጻጸር በ1.89 በመቶ ቀንሷል። ይህም ከባለፈው ሰኔ ወር ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመዘገበ ቅናሽ ነው ተብሏል።

የቢትኮይን ዋጋ 6 ሺህ 6 መቶ ዶላር በመጨመር በታሪክ የመጀመሪያ የተባለውን ከፍተኛ ዋጋ ያስመዘገበ ሲሆን፣ የአንድ ቢትኮይን ዋጋም 75 ሺህ 999.04 ደርሷል።

የተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አቋም የክሪፕቶከረንሲ መገበያያን ቅድሚያ የሚሰጥ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአንጻሩ የጆ ባይደን አስተዳደር ለዘርፉ ትኩረት ካለመስጠትም ባሻገር በክሪፕቶ ዘርፍ ላይ የተለየ ጫና ያደርግ ነበር።

ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካን “የክሪፕቶ ልዕለ ኃያል” ማድረግ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት በክሪፕቶ መገበያያዎች ላይ እርምጃ ሲወስዱ የነበሩትን ጋሪ ጀንስለር የተባሉትን ተሿሚ ከስልጣን እንደሚያነሷቸው ተናግረው ነበር።

መንግሥት ያባከነውን ሃብት ኦዲት ለማድረግ ቢሊየነሩን ኤሎን መስክ እንደሚሾሙም አስታውቀው ነበር። ቢሊየነሩ ኤለን መስክ የክሪፕቶከረንሲ ዋና አቀንቃኝ ሲሆኑ፣ ከሦስት ዓመት በፊት የመኪና አምራች ኩባንያቸው ቴስላ የአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ቢትኮይን ገዝቷል።

የትራምፕን መመረጥ ተከትሎ የኤሎን መስኩ የቴስላ አክስዮን ዋጋ ረቡዕ፣ 27/02/17 ዕለት በ14 በመቶ አሻቅቧል።

መስክ በትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ዋነኛ ደጋፊያቸው ነበሩ።

አንዳንድ ተንታኞች እንደሚሉት የትራምፕ የኢኮኖሚ እቅድ ምናልባትም እንደ ዩናይትድ ኪንግደም እና የአውሮፓ ኅብረት አገራትን ጨምሮ በአንዳንድ አገራት ዘንድ አስደንጋጭ ውጤት ሊያስከትል ይችላል።

ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት በንግድ ላይ ከፍተኛ ታሪፍ እንደሚጨምሩ እና ጭማሪው በተለይ በቻይና ላይ የተጋነነ ሊሆን እንደሚችል ተናግረው ነበር።

አህመት ካያ የተባሉ አንድ የምጣኔ ኃብት ባለሙያ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በአዲሱ የትራምፕ የኢኮኖሚ ዕቅድ ዩናይትድ ኪንግደምም አንደኛዋ ተጎጅ ልትሆን እንደምትችል ተናግረዋል።

በዚህም ምክንያት የዩናይትድ ኪንግደም ዓመታዊ ዕድገት በ2025 ቀድሞ ተገምቶ ከነበረው 1.2 በመቶ ወደ 0.4 ሊወርድ እንደሚችል ተንብየዋል።

የትራምፕ ዓለም አቀፍ የንግድ ፖሊሲ በአመዛኙ ወደ አሜሪካ የሚገቡ የእስያ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠር መሆኑን ተንታኞች ይናገራሉ።

ትራምፕ ከንግዱ በተጨማሪ በፖለቲካውም እስያ ላይ ያላቸው ተጽዖኖ ይቀንሳል ተብሎ ስለሚገመት በትልልቅ አገራት የመወረር ስጋት ያለባቸው አገራት ከአሜሪካ እገዛ የማግኘታቸው ነገር አናሳ መሆኑን ተንታኞች ያነሳሉ።

ለአብነት ቻይና የግዛቷ አካል እንደሆነች የምትናገርላት ታይዋን የመወረር አደጋ ቢገጥማት አሜሪካ ላትከላከልላት ትችላለች ይላሉ።

ራስ ገዟ ደሴት ለዓለም ኢኮኖሚ ወሳኝ የሆነውን ኮምፒውተር ችፕ በማምረት ትልቅ ድርሻ አላት።