የቀድሞው የፎክስ ኒውስ አቅራቢ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ለመሆን የሚያስችላቸውን ድምጽ አገኙ

በዶናልድ ትራምፕ ለአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትርነት በእጩነት ቀርበው የነበሩት ፔት ሄግሴት አርብ ምሽት ላይ ሚኒስትር ለመሆን የሚያስችላቸውን የምክር ቤት ድምጽ አገኙ።
ፔት ቀደም ብሎ በቀረበባቸው የሥነ ምግባር ጉድለት የተነሳ ይህንን እድል ሊያጡት ተቃርበው ነበር።
ሆኖም የቀድሞው የምክር ቤት መሪ ሚቺ ማክኮንልን ጨምሮ ሦስት ሪፐብሊካን የምክር ቤት አባላት ምርጫውን ከተቃወሙ በኋላ ምክትል ፕሬዚደንቱ ጄዲ ቫንስ አብላጫ ያስገኘችውን ድምጽ በመስጠታቸው ሄግሴት ሚኒስትር የመሆን እድላቸውን ማረጋገጥ ችለዋል።
ምርጫው በተካሄደበት ወቅት ምንም እንኳን እርሳቸው ቢያስተባብሉም ወሲባዊ ትንኮሳን፣ እምነት ማጉደልን እና ከልክ ያለፈ መጠጥ መጠጣትን የተመለከቱ በርካታ ጥያቄዎች ተነስተውባቸው ነበር።
ሄግሴት እንዳይመረጡ ለማድረግም ድምጽ ከሰጡ 47 ዲሞክራት እና ገለልተኛ ሴናተሮች በተጨማሪ አራት የሪፐብሊካኖች ድምጽ ያስፈልግ ነበር።
የማክኮንል ያልተጠበቀ የተቃውሞ ድምጽ የምክር ቤቱ ድምጽ እኩል 50-50 እንዲሆን ያደረገ ሲሆን፣ምክትል ፕሬዚደንቱ ቫንስ በመጨረሻ አብላጫ ያመጣውን የድጋፍ ድምጽ ሰጥተዋል።
ማክኮንል ለምን ድምጻቸውን ለሄግሴት እንደነፈጉት ሲገልጹ "ሄግሴት ሦስት ሚሊዮን ሠራተኞች እና ከፍተኛ በጀት ያለውን መሥሪያ ቤት ለመምራት እንዲሁም ከዓለም አገራት ጋር ለመተባበር ዝግጁ አይደሉም" ብለዋል።
የመከላከያ ሚኒስትርነት ሚናው የአሜሪካ ሕዝቦችን ደኅንነት ለማስጠበቅ ሲባል በየእለቱ የሚገጥም ፈተናን መጋፈጥ ነው" ብለዋል ማክኮኔል።
ሆኖም ሄግሴት ይህንን ፈተና እንዴት እንደሚያልፉት እስካሁን እንዳላሳዩ ተናግረዋል።
የቀድሞ የጦሩ አባል እና የአንድ ወቅት የፎክስ ኒውስ ቴሌቪዥን አቅራቢ የነበሩት ሄግሴት ሦስት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰራተኞችን እና 849 ቢሊዮን ዶላር በጀትን የመቆጣጠር ኃላፊነት ይኖራቸዋል።
የሄግሴትን ሹመት ለማረጋገጥ ምክንያት የሆነችውን ድምጽ የሰጡት ቫንስ በአሜሪካ ታሪክ የካቢኔ እጩን ያፀደቁ ሁለተኛው ምክትል ፕሬዚደንት ሆነዋል።
እንደ አውሮፓውያን 2017 ቤትስይ ዲቮስ የትምህርት ሚኒስትር እንዲሆኑ የውሳኔ ድምጽ የሰጡ የመጀመሪያው ምክትል ፕሬዚደንት፣ የትራምፕ የቀድሞው ምክትል ፕሬዚደንት ማይክ ፔንስ ነበሩ።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ሄግሴት በሰጡት የማረጋገጫ ድምጽ " ጦርነትን መዋጋት ፣ ገዳይነት፣ ሥልጣን መያዝ ፣ ብቃት እና ዝግጁነት! ይኸው ነው ። ይህ ነው ሥራዬ" ብለው ነበር።
በአፍጋኒስታን እና ኢራቅ በነበሩ ጦርነቶች ተዋጊ የነበሩት የ44 ዓመቱ ሄግሴት በኋላ ላይ በፎክስ ኒውስ በአቅራቢነት ሰርተዋል።
ለብሔራዊ ጸጥታ ካቢኔ ኃላፊነትም ከሚጠበቀው ያነሰ ልምድ ነው ያላቸው።
እርሳቸው የሚሾሙበት መሥሪያ ቤትም በከፍተኛ የሲቪል ሰራተኞች ፣ ልምድ ባላቸው ፖለቲከኞች ፣ ጀኔራሎች እና ከፍተኛ ሥራ አስፈፃሚዎች የተሞላ ነው።
በዚህም የዴሞክራት ሴናተሮች በአገሪቷ ትልቅ ከሆኑ ተቋማት አንዱ የሆነውን መሥሪያ ቤት የመምራት ብቃታቸውን ላይ ጥያቄ አንስተዋል።
በምርጫው ወቅት ሄግሴት ከዚህ ቀደም ሴቶች በመከላከያ ሚና ላይ ማገልገል አይገባቸውም ሲሉ የሰጡትን አስተያየት በተመለከተም በተለይ በሴት ሴናተሮች ተጠይቀው ነበር።
ሄግሴት በሰጡት ምላሽም ትኩረታቸው ሴቶች በመከላከያ ማገልገልን የተመለከተ እንዳልነበር እና የአሜሪካ ጦር ስላለው ደረጃ እንደነበር ተናግረዋል።
የምርጫው ሒደትም ከዚህ ቀደም ቀርቦባቸው በነበሩ የሥነ ምግባር ጉድለቶች ያጠላበት ነበር።ሄግሴት እንደ አውሮፓውያኑ በ2017 በካሊፎርኒያ በአንድ የሆቴል ክፍል ውስጥ አንዲት ስሟ ያልተገለጸ ሴት ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ በመፈፀም ተከሰው ነበር። ነገር ግን የቀረበባቸውን ክስ በተደጋጋሚ ተቃውመዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በሥራ ፕሮግራሞች ላይ የአልኮል መጠጥን ከልክ በላይ በመጠጣት፣ ቀደም ሲል በነበሯቸው ሁለት ትዳራቸው ታማኝ ባለመሆን የተወነጀሉ ሲሆን " ፍጹም ሰው አይደለሁም፤ መታረም ግን ያለ ነው" ብለዋል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይም በአልኮል መጠጥ እና አጋራቸውን ላይ ጥቃት በመፈፀም ክስ ቀርቦባቸው የነበረ ሲሆን ጠበቃቸው ክሱን አስተባብለዋል።
ሆኖም ትራምፕን ጨምሮ በርካታ ሪፖብሊካኖች ለሄግሴት ያላቸውን ድጋፍ ጠብቀዋል።
አርብ ዕለት ሹመታቸውን በመቃወም ድምጽ የሰጡት ሪፐብሊካኗ የአላስካዋ ሴናተር ሊሳ ሙርኮውስኪ በሄግሴት ላይ የቀረቡ ያለፉ ውንጀላዎች ድምጽ ለመስጠት አወዛግቧቸው እንደነበር ተናግረዋል።
ሴናተሯ ከድምጽ መስጫው ቀን ቀናት ቀደም ብሎ ባወጡት መግለጫ ላይም የቀድሞ ባህርይ የእኛን ጦር የማይገባ እንደሆነ ያሳያል ብለዋል።
የተቃውሞ ድምጽ የሰጡት ሌላ ሪፐብሊካን የሜን ሴናተር ሱሳን ኮሊስ " ኃላፊነቱን ለመቀበል የሚያስችል ልምድ እና አመለካከት ስለሌለው አሳስቦኛል።" ብለዋል።












