የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ዕርዳታ እንዲቆም መወሰኑን ሾልኮ የወጣ ማስታወሻ አሳየ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ዕርዳታ እንዲቆም መወሰኑን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ለባለስልጣናት እና ለውጭ አገራት ለሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች የላከው የውስጥ ማስታወሻ አሳየ።
ሾልኮ የወጣው ይህ ማስታወሻ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የውጭ ፖሊሲያቸው ውጤታማነት እና ወጥነት እስኪገመገም ድረስ ለ90 ቀናት የውጭ የልማት ድጋፍ እንዲቆም ሰኞ ዕለት ያሳለፉትን የሥራ አስፈጻሚ ትዕዛዝን የተከተለ ነው።
አሜሪካ ከዓለማችን ትልቁ ዓለም አቀፍ እርዳታ ለጋሽ ስትሆን በአውሮፓውያኑ 2023፣ 68 ቢሊዮን ዶላር ማውጣቷን ከመንግሥት የተገኘ መረጃ ያስረዳል።
የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ያስተላለፈው ትዕዛዝ ከልማት ዕርዳታ እስከ ወታደራዊ ድጋፍ ድረስ የሚሸፍን ሊሆን እንደሚችል የጠቆመ ነው።
ለድንገተኛ የምግብ ዕርዳታ እንዲሁም ለእስራኤል እና ለግብጽ ወታደራዊ ድጋፍ በስተቀር ሁሉም የውጭ ልገሳዎች እንዲቆሙ የሚያዘው ይህ ሾልኮ የወጣውን የውስጥ ማስታወሻ ቢቢሲ ተመልክቶታል።
"እያንዳንዱ አዲስ የገንዘብ ድጋፍ ወይም ማራዘሚያ እስካልተገመገመ እና እስኪጸድቅ ድረስ አይለቀቅም" ሲል ይህ በውጭ አገራት ላሉ የአሜሪካ ኤምባሲዎች የተላከው የውስጥ ማስታወሻ ያትታል።
አክሎም የአሜሪካ ባለስልጣናት" ከእርዳታዎች ጋር በተያያዘ በአስቸኳይ የሥራ ማቆም ትዕዛዞችን እንዲያስተላልፉ እና ይህም ግምገማውን ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እስኪወስንበት ጊዜ ድረስ የሚቆይ ይሆናል" ይላል።
በተጨማሪም ዕርዳታዎች የፕሬዚዳንት ትራምፕን የውጭ ፖሊሲ ግቦች የተከተሉ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በሁሉም የውጭ ዕርዳታዎች ላይ ሰፋ ያለ ግምገማ በ85 ቀናት ውስጥ እንዲጠናቀቅ ያዛል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ አሜሪካ በውጭ አገራት ገንዘብ ማውጣት ያለባት አገሪቷን "ጠንካራ፣ ደኅንነቷ የተጠበቀ ወይም የምትበለጽግ" ካደረገ ብቻ ነው ሲሉ ከዚህ ቀደም ተናግረው ነበር።
ይህ ውሳኔ በአሜሪካ ልገሳ በሚደረግላቸው የውጭ ዕርዳታ ፕሮግራሞች ላይ "ከበድ ያለ ተጽዕኖ" እንዳለው አንድ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰብዓዊ የፈንጂ ማምከን ፕሮግራሞች በድንገት ሥራ አቁሙ ሲባሉ ሊፈጠር የሚችለውን ነገር ማሰብ ይቻላል። በጣም ከበድ ያለ ሁኔታ ነው" ሲሉ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የጦር መሳሪያ ዝውውርን ቁጥጥር ይመሩ የነበሩት ጆሽ ፓል አስረድተዋል።
በመካከለኛው ምስራቅ የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) ተልዕኮ ዳይሬክተር የነበሩት ዴቭ ሃርደን በበኩላቸው ግምገማው በሚካሄድበት ወቅት በዓለም ዙሪያ በአሜሪካ የሚደገፉ የሰብዓዊ እና የልማት መርሃ ግብሮች ወዲያውኑ እንዲታገድ ሊያደርግ እንደሚችል ጠቅሰዋል።
የውሃ፣ የአካባቢ ጽዳት እና መጠለያን ጨምሮ መሰረታዊ በሚባሉ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ሊያሳድር እንደሚችል ጠቅሰዋል።
የውስጥ ማስታወሻው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፍቃድ ያገኙት "ለእስራኤል እና ግብፅ የሚደረግ የውጭ ወታደራዊ ፋይናንስ እንዲሁም ደመወዝን ጨምሮ የውጭ ወታደራዊ ገንዘብን ለማስተዳደር የሚያስፈልግ አስተዳዳራዊ ወጪዎች" መሆናቸውን ጠቅሷል።












