'ሙዚቃ የሚሰሙ ሰዎችን የሚገርፈው' አዲሱ የናይጄሪያ ታጣቂ ቡድን በሽብርተኝነት ተፈረጀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የናይጄሪያ ባለሥልጣናት ላኩራዋ የተሰኘውን ታጣቂ ቡድን በሽብርተኛ ድርጅትነት በመፈረጅ በመላ አገሪቱ እንዳይንቀሳቀስ አገዱ።
ላኩራዋ ታጣቂ ቡድን ሙዚቃ የሚሰሙ ሰዎችን የሚገርፍ፣ጥቃት የሚፈፅም እና በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ እና ከኒጀር አዋሳኝ ድንበር አካባቢ ያሉ ነዋሪዎችን ኢላማ የሚያደርግ አዲስ ታጣቂ ቡድን ነው።
የናይጄሪያ ባለሥልጣናት እንዳሉት ላኩራዋ በማሊ እና ኒጀር ካሉ 'ጂሃዲስት ቡድኖች' ጋር ግንኙነት ያለው ሲሆን ታጣቂዎቹ ለዓመታት በናይጄሪያ እና ኒጀር ድንበር ላይ ተቀምጠው የአካባቢውን ሴቶች ያገባሉ፤ወጣቶችን ይመለምላሉ።
ይህም ከእስላማዊ ታጣቂ ቡድን ቦኮ ሃራም እስከ አጋች ወንበዴዎች እንዲሁም ከሌሎች በርካታ ታጣቂ ቡድኖች ጋር እየተዋጋች ላለችው ናይጄሪያ ተጨማሪ የደኅንነት ስጋት ሆኖባታል።
በዚህም የናይጄሪያ መንግሥት ሐሙስ ዕለት የቡድኑን ተግባራት በመዘርዘር በዋና ከተማዋ አቡጃ ለሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት የክስ ሰነድ አስገብቶ ነበር።
ሰነዱ ላኩራዋ ከብቶችን መዝረፍ እና ለገንዘብ ሰዎችን ማገትን፣ ጠለፋን፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ጥቃት መፈፀምን ጨምሮ በሽብር ተግባራት ላይ ሲሳተፍ መቆየቱን ያስረዳል።
ከዚህም በተጨማሪ ቡድኑ በአካባቢው የሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት ያጠፋ፣ ጉዳት እና የንብረት ውድመትን ያስከተለ ጎጂ የሆነ ርዕዮተ ዓለምን በማሰራጨት እና ነዋሪው ባለሥልጣናትን እንዳያከብር በማበረታታት ተከሷል።
ቡድኑ የተፈጠረው በሶኮቶ እና ኬቢ ግዛቶች ውስጥ በሚገኙ መንደሮች ውስጥ ከጥቂት ዓመታት በፊት የነበረ ሲሆን የአካባቢው ሰዎች ለባለሥልጣናት ቢያሳውቁም የተሰራ ሥራ አልነበረም።
መጀመሪያ ላይ የላኩራዋ አባላት የአካባቢውን ማኅበረሰቦች ከታጣቂዎች እና ከከብት ዘራፊዎች እንደሚጠብቁ ቃል ገብተው ነበር።
ሆኖም የነዋሪዎችን ስልክ መፈተሽ እና በስልካቸው ላይ ሙዚቃ የጫኑ ሰዎች ሙዚቃውን ከማጥፋታቸው በፊት መግረፍ ሲጀምሩ ነገሮች እንደተባባሱ አንድ ግለሰብ ተናግሯል።
ለፍርድ ቤቱ በቀረበው ሰነድ ላይም የናይጄሪያ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ እና የፍትሕ ሚኒስትሩ ላቴፍ ፋግቤሚ፣ የቡድኑ ድርጊቶች ለብሔራዊ ደኅንነት ከፍተኛ ስጋት ሆኗል ብለዋል።
ባለፈው ዓመት የጦሩ ቃል አቀባይ ሜጄር ጀኔራል ኤድዋርድ ቡባ፣ የላኩራዋ ቡድን መፈጠር በጎረቤት አገራት ማሊ እና ኒጀር ካለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር በቀጥታ እንደሚያያዝ ተናግረው ነበር።
ጦሩ በእስላማዊ ሽምቅ ተዋጊዎች ግፊት ምክንያት በሁለቱም አገራት ተሰማርቶ ነበር።
ዳኛ ጀምስ ኦሞቶሾ ባሳለፉት ፈጣን ውሳኔም ቡድኑን የሽብርተኛ ድርጅት ብለው የፈረጁ ሲሆን ሌሎች ተመሳሳይ ቡድኖችም በመላ አገሪቱ በተለይም በሰሜን ምዕራብ እና ሰሜን ማዕከላዊ ክልሎች እንዳይንቀሳቀሱ የጣለውን እገዳ አራዝመዋል።
ይህ ውሳኔ የናይጄሪያ መንግሥት በቡድኑ ላይ ጠንካራ እርምጃ ለመውሰድ ሥልጣን ይሰጠዋል።
የጸጥታ ተቋማትም የቡድኑን እንቅስቃሴ የማደናቀፍ እና የማፍረስ ሰፊ ሥልጣን ያላቸው ሲሆን ይህም እስራትን፣ ክስ ማቅረብን፣ የንብረት እገዳን እና ክትትልን ይጨምራል።
ከዚህም በተጨማሪ በሽብር ከተፈረጀው ቡድኑ ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች ላይ መገለልን ሊያስከትል ይችላል።
በመላ አገሪቱ በተለይም በሰሜናዊ ናይጄሪያ በአውሮፓውያኑ 2000 መጨረሻ ላይ ብቅ ካለው ቦኮ ሃራም ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሁኔታ እንዳይፈጠር ነዋሪዎች ሰግተዋል።
ቦኮ ሃራም ማለት " የምዕራባውያን ትምህርት የተከለከለ ነው" ማለት ሲሆን በክልሉ እስላማዊ አገዛዝ ለመመስረት በተደጋጋሚ ዓለማዊ ትምህርት ቤቶችን ኢላማ ያደርጋል።
ቡድኑ እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 ከሰሜን ምሥራቃዊቷ ከተማ ቺቦክ ከ200 በላይ ሴት ተማሪዎችን አግቶ ከወሰደ በኋላ ስሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታውቋል።












